የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዋጋ ተመጣጣኝና ተወዳዳሪ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል የተባለለትን የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ በማፅደቅ ተግባራዊ እንዲሆን ወሰነ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማክሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ የብድር ስምምነቶችን፣ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦችን፣ እንዲሁም ፖሊሲዎችን በሚመለከት ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ፖሊሲዎች መካከል አንዱ የሆነውና ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ለረዥም ዓመታት ያገለገለውን ፖሊሲ ለማዘመን የተዘጋጀው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ የሚመለከት ነው፡፡ ፖሊሲው ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ፣ ከአረንጓዴ ግቦችና ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
የኢነርጂ ልማት ሥራዎች ላይ የግሉን ዘርፍና ክልሎችን ለማሳተፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው የተባለለት ፖሊሲው፣ አገሪቱ በቀጣናው ያላትን የኢነርጂ አቅም በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ይገለጻል፡፡
የኢነርጂ ሀብትን በአነስተኛ ዋጋ በማልማት ዘላቂ፣ አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲኖርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል የተዘጋጀ ነው የተባለው ረቂቅ ለምክር ቤቱ መቅረቡንና ውይይት ከተደረገበት በኋላ ግብዓቶችን በመጨመር፣ ከፀደቀበት ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ተመላክቷል፡፡
ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው ጉዳይ የታክስ አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ በሚለከት ሲሆን፣ አዋጁን ለማሻሻል ያስፈለገውም ተግባራዊ እየተረገ የሚገኘው አዋጅ 983/2008 ከወጣ በኋላ በአገሪቱ በርካታ የኢኮኖሚ ለውጦች በመደረጋቸው የታክስ ሥርዓቱን ለማዘመን መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የታክስ አለመግባባቶችን በፍትሐዊነት፣ በሰላማዊ መንገድና በቅልጥፍና ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ነው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁን በሚመለከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ከአንድ ሳምንት በፊት ውይይት ባደረገበት ወቅት ቅሬታ፣ ይግባኝ ወይም የውሳኔ ማስተካከያ ጥያቄን የሚያቀርብ ታክስ ከፋይ፣ በታክስ ውሳኔ ወቅት ካቀረበው የተለየ አዲስ ማስረጃን ማቅረብ የሚከለክለው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 2 ቅሬታ ማስነሳቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
From The Reporter Magazine
ሆኖም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ተነግሯል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል የተዘጋጀውን የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ፣ ከካርበን ንግድ የሚገኘውን ገቢ በመንግሥት፣ በአልሚዎች፣ በአካባቢው ማኅበረሰብና በባለድርሻ አካላት መካከል በፍትሐዊነት የሚከፋፈልበትን አሠራር ለመዘርጋት ይረዳል የተባለውን የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢንሹራንስ ረቂቅ አዋጅና የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ በመወሰን መላኩን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
በሙሉ ድምፅ ፀድቀው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተላኩ አዋጆች መካከል ከአፍሪካ ልማት ባንክ ለአርብቶ አደሩ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 46.3 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለስድስተኛ ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ146.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል፡፡
From The Reporter Magazine
ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከልና ጥበቃና ምላሽ ለመስጠት ይረዳል የተባለለት ብሔራዊ የሴቶች ማብቃትና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ረቂቅ ፖሊሲ፣ የምርት ደኅንነት መሥፈርቶችን ለማውጣትና ፍትሐዊ የንግድ አሠራርን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑ የተገለጸውን የኢትዮጵያ የንግድ ረቂቅ ፖሊሲ ሌላኛው ምክር ቤቱ ያፀደቀውና ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ያሳለፈባቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመንግሥት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸምን ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ ደንብ፣ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለቤቶችን መረጃ ግልጸኝነት ለመደንገግ የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡
