- የዲጂታል መታወቂያ 6.6 ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል ተብሏል
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር እንደ አንድ ንግድ ተቋም በመንግሥት የልማት ድርጅትነት እንደገና የተደራጀው ፋይዳቨርስ፣ ወደፊት ገቢ ከሚያመነጭባቸው ዋና ዋና የሥራ መስኮች መካከል፣ ለባንኮችና ለሌሎች ተቋማት የደንበኞችን ማንነት በኤሌክትሮኒክ የማረጋገጥ (e-KYC) አገልግሎቶች እንደሚገኙበት ተገለጸ።
ተቋሙ ለሪፖርተር በሰጠው ማብራሪያ፣ ፋይዳቨርስ ገቢ የሚያመነጨው በባንኮችና በተለያዩ ተቋማት የደንበኛ ማንነትን በኤሌክትሮኒክስ በማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የመንጃ ፈቃዶች፣ ከዲጂታል የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶችና ሌሎች መንግሥታዊ ሰነዶችን በዲጂታል ክሬደንሽያል መልክ በማቅረብ፣ በማረጋገጥና በማሻሻል በሚሰጠው የአገልግሎት ክፍሉና በተጨማሪም በዲጂታል ዋሌት ሥርዓትም በኩል ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም ፋይዳቨርስ ከአገር ውስጥ ባለፈ በሌሎች አገሮች የዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት (DPI) እና የዲጂታል ሕዝባዊ ሀብቶች (DPG) ዘርፍ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የማማከርና የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የፋይዳቨርስ ምሥረታ ይፋ በተደረገበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ተቋሙ እ.ኤ.አ. 2030 ድረስ የአገሪቱን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት (GDP) በስድስት በመቶ ያሳድጋል፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢም ያስገኛል ብለዋል፡፡
ይህንን አስመልክቶ ሪፖርተር ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን፣ ተቋሙም የተጠቀሰው መረጃ ዓለም አቀፉ ማኬንዚና ኩባንያው (McKinsey & Company) ያጠናውን የምርምር ውጤት መሠረት ያደረገ መሆኑ ተብራርቷል።
ጥናቱ አገሮች የዲጂታል ማንነት (Digital ID) ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲያደርጉና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶችን ማስተሳሰር ሲችሉ፣ በኢኮኖሚያቸው ላይ የሚኖረውን በጎ ተፅዕኖ ያመላከተ እንጂ፣ የፋይዳቨርስ ተቋም ብቻውን በቀጥታ የሚያስገባውን የንግድ ገቢ እንደማያሳይ ተገልጿል።
ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንደ ጠቀሰው የማኬንዚ ጥናት ከሆነ፣ እንደ ቻይናና ብራዚል ያሉ አገሮች የዲጂታል ማንነት ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ በመተግበራቸው ምክንያት፣ በኢኮኖሚያቸው ላይ ከአምስት እስከ ስድስት በመቶ የሚደርስ የጂዲፒ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል ተብሏል።
From The Reporter Magazine
ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. 2030 ድረስ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራዋን መቶ በመቶ ስታደርስ፣ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዘግባለች በሚል የቀረበው የጥናት ውጤት በንግግሩ ወቅት በጥቅል መቅረቡን፣ ይህም በተቋሙ ቀጥተኛ ገቢና በጠቅላላ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መካከል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉ ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ከፋይዳቨርስ አገልግሎት ትግበራ ጋር ተያይዞ ሊገኝ ይችላል የተባለው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ኢኮኖሚያዊ እሴት፣ አጠቃላይ አገራዊ ፋይዳውን የሚያሳይ እንጂ የፋይዳ ቨርስ ተቋም ቀጥተኛ የሽያጭ ገቢ ትንበያ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ንግድ ተቋም የተቋቋመው ፋይዳ ቨርስ የራሱን ገቢ የሚያመነጨው ለባንኮችና ለሌሎች ተቋማት ከሚሰጠው የደንበኞች ማንነት ማረጋገጫ (e-KYC)፣ ሰነዶችን በዲጂታል መንገድ ከሚያረጋግጥበት አገልግሎትና ከዲጂታል ዋሌት (Wallet) አገልግሎት፣ እንዲሁም በሞዛምቢክና ዛምቢያ እንደሚደረገው ለውጭ አገሮች ከሚሰጠው የዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት (DPI) የማማከርና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ሥራዎች መሆኑ ተነግሯል፡፡
From The Reporter Magazine
ሪፖርተር የተመለከተው የፋይዳቨርስን ሥራዎችን የተመለከተ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ›› የተሰኘ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ 6.6 ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ ጥቅም ያስገኘል ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የፋይዳቨርስን እንደ መንግሥት የልማት ድርጅት መቋቋም አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እስካሁን ወደ 50 ሚሊዮን ነዋሪዎች ጋር የደረሰ ሲሆን፣ ከ150 በላይ ተቋማት ጋርም ቅንጅት መፍሩ ተጠቅሷል፡፡ 190 ሚሊዮን ደኅንነታቸው የተጠበቁ ማረጋገጫዎችን በማከናወን፣ 12 ሺሕ የሕዝብ ምዝገባ ጣቢያዎችን በማሠማራትና ከ15 ሚሊዮን በላይ የማንነት ማረጋገጫዎችን መስጠቱም ተገልጿል።