ሰሞኑን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል የአንድ ቀን ድንገተኛ ውጊያ መካሄዱ ተሰምቷል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ወታደራዊ ኃይሎች መካከል ተደረገ የተባለው ውጊያ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሁለት ዓመታት አውዳሚ ጦርነት አድማሱ ከሰፋ ሊከተል የሚችለው ዕልቂትና ውድመት ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከቷል፡፡ በኢትዮጵያ ከአራት ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት አገራዊ የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ባለበት ወቅት፣ በሌላ በኩል በአገር ላይ ትልቅ ችግር ሊያስከትል የሚችል የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም ከሥጋት ባለፈም ከፍተኛ ፍርኃት ይፈጠራል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ጦርነቶችም ሆነ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሥፍራዎች በሚካሄዱ ውጊያዎች፣ እየተጎዳ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከግጭቶች በመለስ ተቀምጦ በሥርዓት ለመነጋገር የሚያስችል ፍላጎት በመጥፋቱ ብቻ፣ አገር እየደማችና እየቆሰለች ህልውናዋ ለአደጋ ከመጋለጧ ባሻገር ሕዝቡም ሕይወቱ ለከፋ ችግር እየተዳረገ ነው፡፡ ጦርነት ግን በአገር ላይ የተጋረጡ ችግሮችን እንደማይፈታ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ጦርነትም ሆነ የጦርነት ወሬ እንዳንገሸገሸው፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በግልጽ ሲናገር በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡ በከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ ሆኖ ከከፋው ድህነት ለመገላገል የሚያስችሉ የልማት ዕቅዶች የሚያስፈልጉት ሕዝባችን፣ ከጦርነት አባዜ እንዲላቀቅ መፍትሔ ካልተፈለገለት የራሱም ሆነ የአገሩ ዕጣ ፈንታ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የጦርነት አገር አውዳሚነትና በሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ ከዚህ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ የመገላገያ ዘዴው ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን መንገር ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሕዝባችን በሚኖርባቸው ሁሉም አካባቢዎች ችግሮች ሲያጋጥሙት እንዴት እንደሚፈታቸው በቀላሉ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ግን ከዚህ መሠረታዊ አገር በቀል ዕውቀት ተምረው፣ እየገቡበት ያለውን አደገኛና አጥፊ ጉዞ ማቆም አለባቸው፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ልዩነቶች ሲያጋጥሙም ሆነ ችግሮች ሲፈጠሩ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ አገር በቀል ዕውቀቶች ባሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ያለ ማቋረጥ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ተንደርድሮ የመግባት አባዜ ተጠናክሮ መቀጠሉ ያሳዝናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማኅበረሰቦች ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሽምግልና የመፍታት ለዘመናት የኖረ አኩሪ እሴት አለው፡፡ ግጭቶች ሲያጋጥሙም በዚህ አኩሪ እሴት አማካይነት በዳይን ገስፆ ወይም ቀጥቶ፣ ተበዳይን ደግሞ በመካስ ዕርቅ እንዲፈጠር ማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ባህሉ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለግድያ የሚፈላለጉ ወገኖችን በማስታረቅ በጋብቻ ጭምር በማዛመድ ደም ማድረቅም የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አኩሪ የዳበረ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ምክንያት እየፈለጉ መፋጀት ያሳቅቃል፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች መፍቻ መልካም ባህል እያለ ጦርነት ውስጥ መገኘት ትርፉ ውድቀት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት በአንድነት ቆመው ተስፋፊዎችንና ወራሪዎችን ሲመክቱ እንጂ፣ እርስ በርስ እየተጋደሉ አገራቸውን ሲያፈርሱ አይደለም፡፡ ለተራዘመ ጊዜ ጦርነት ውስጥ መቆየት ታሪካዊ ጠላቶችን ከመጥቀም ውጪ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቡ የሚፈይደው የለም፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት የአፍሪካ ቀንድ ለውጭ ኃይሎች የውክልና ጦርነት ማራመጃ ከመሆን በስተቀር፣ በአገሮቹ ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች ሰላምና ዕድገት ማስገኘት አልቻለም፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ የመረጋጋት ምሳሌ ሆና አገሮችን በማስተባበር የልማት ፈር ቀዳጅ መሆን ሲገባት፣ ልጆቿ እርስ በርስ ያለ ማቋረጥ እየተዋጉ ለውጭ ኃይሎች ቀዳዳ ሲከፍቱ ለታሪካዊ ጠላቶች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጠር አለመገንዘብ ያሳዝናል፡፡ የብጥብጥና የትርምስ ቀጣና የሆነው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተሁኖ፣ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላው እንደ ዘበት እየገቡ መፋጀትን ማስቆም ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥ አልፋ እዚህኛው ትውልድ እጅ የገባች አገር ናት፡፡ ይህ ትውልድ ካለፉት ትውልዶች የተገኙ አኩሪ ተግባራትን አጠናክሮ የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከአኩሪ ታሪኮች መካከል የሚጠቀሰው ለአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ መሆን ነው፡፡ አፍሪካውያንን በአንድ ጥላ ሥር ያሰባሰበችን አገር በብሔር፣ በእምነትና በተለያዩ ምክንያቶች በመከፋፈል ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላው መክተት መቆም አለበት፡፡ ለዘመኑ ከማይመጥኑ ድርጊቶች ራስን በመግታት ወደ መነጋገሪያው ጠረጴዛ መምጣት የግድ መሆን አለበት፡፡ ለእውነተኛና ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚረዱ መፍትሔዎች ላይ ይተኮር፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው በአንድነት ቆመው አገራቸውን ሲያስከብሩና ለአፍሪካውያን ጭምር ትሩፋት የሚሆኑ ተግባራትን ሲያከናውኑ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ግን አድፍጠው ለሚጠባበቁ ታሪካዊ ጠላቶች ካልሆነ በስተቀር ለማንም አይጠቅምም፡፡ የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ ከማያባራ ጦርነት ውስጥ መውጣት ሊያቅታት አይገባም፡፡
ጦርነት ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው የሚደረግ እንቅስቃሴን ይገታል፣ በሰላም ወጥቶ መግባትን ያስቀራል፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የግብርና፣ እንዲሁም የተለያዩ የሥራ መስኮችን እንቅስቃሴ ያስቆማል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በላይ ደግሞ የንፁኃንን ሕይወት ይቀጥፋል፣ የወጣቶችን ተስፋ ያጨልማል፣ በሰላም የመኖር መብትን ይጋፋል፣ በተጨማሪም በአገር ህልውና ላይ ከባድ አደጋ ይደቅናል፡፡ በጦርነት ምክንያት ከሚደርሰው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር ለአገር ልማት መዋል ያለበትን ሀብት ይበላል፡፡ ኢትዮጵያ ከጦርነት ቀውስ ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ ልዩነቶች መፈታት ያለባቸው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ጦርነት የትኛውንም ዓይነት ችግር ሲፈታ ታይቶ አይታወቅም፡፡ የአገር ህልውና ጉዳይ የሚያሳስባቸው በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ጓዙን ይዞ እንዲወጣ በኃላፊነት ስሜት መነጋገር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚከበሩት ለጋራ ዓላማ በአንድነት ሲሠለፉ እንጂ ጎራ ለይተው ሲጠፋፉ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱትም በጦርነት አይደለም!