- የጦር መሣሪያ ጩኸት የማስቆም አኅጉራዊ ግብ አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል
በአፍሪካ ባለፉት አሥር ዓመታት የሚቀሰቀሱ ግጭቶች አኃዝ መጨመሩ ተነገረ፡፡ የግጭቶች ቁጥር ማሻቀብ ብቻ ሳይሆን ሥርጭታቸውም መስፋቱ ተገልጿል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት፣ የጠመንጃ ጩኸት የማይሰማባት አፍሪካ (Silencing the Guns in Africa) የተባለው አኅጉራዊ ግብን በማሳካት ሒደት የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚገመግም ስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡ ከዚሁ ስብሰባ ቀደም ብሎ የወጣው ሪፖርት ይህ አኅጉራዊ ግብ ከተቀመጠ ጀምሮ በነበሩት አሥር ዓመታት በአኅጉሩ የግጭት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ያመለከተ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት አኅጉራዊው ግብ የመሳካት ዕድሉ አደጋ እንደተጋረጠበት ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ አኅጉርን ከጠመንጃ ጩኸት የማላቀቅ ግብ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ብሎ ካወጣቸው መሠረታዊ አኅጉራዊ ግቦች አንዱ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁንና አማኒ አፍሪካ የጥናት ተቋም ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ ዕቅዱ መተግበር ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2023 በነበሩት አሥር ዓመታት በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ መፈናቀልና ስደትም በሦስት እጥፍ ማደጉን ጠቁሟል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው እ.ኤ.አ. በ2013 ብቻ 1,671 ግጭቶች በአፍሪካ ሲመዘገቡ ሆኖም ይህ አኃዝ ከመቀነስ ይልቅ በ2025 አሻቅቦ ወደ 6,124 ደርሷል፡፡
የአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው በአኅጉሩ የግጭቶች መበራከትና ሥርጭት መስፋፋት የደቀነውን አደጋ እንዲያተኩርበት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አኅጉራዊውን የጠመንጃ ጩኸት የማስቆም ግብ ከዳር እንዳይደርስ የገጠመውን እንቅፋት እንዲመረምርና መፍትሔ እንዲያስቀምጥ አሳስቧል፡፡ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ እ.ኤ.አ. በ2024 ባካሄደው 1252ኛ ጉባዔ ስለዚሁ ግብ አፈጻጸም በዋናነት መምከሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በጊዜው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ምክክር በማድረግ ግቡን ለማሳካት የሚያስችሉ የተከለሱ ሥልቶችን እንዲያስቀምጥ ጠይቆም ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. ጁን 2025 የኅብረቱ ኮሚሽን የአኅጉራዊው ግብ የመካከለኛ ጊዜ የትግበራ ሒደት የሚገመግም ስብሰባ አድርጎ ነበር፡፡ ከእነዚህ በኋላ የሚደረገው የአሁኑ ስብሰባ የአፍሪካ አኅጉርን ከጥይት ጩኸት የመታደጉ ዕቅድ ምን ደረጃ እንዳለ በጥልቀት የሚገመገምበት፣ ግቡም የገጠሙት እንቅፋቶች ተመርምረው ለትግበራው አዳዲስ መፍትሔዎች የሚገኙበት ነው ተብሎ እንደሚጠበቅ አማኒ አፍሪካ ገልጿል፡፡
በአፍሪካ የመሣሪያ ጩኸትን በማስቆም ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የተቀመጠው አኅጉራዊ ግብ አልተሳካም የሚል ድምዳሜ ተቋማቸው በሪፖርቱ ይዞ ስለመቅረቡ የተጠየቁት በአማኒ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ትፍስህት ኃይሉ፣ አኅጉራዊው ግብ ትልልቅ እንቅፋቶች እንደገጠሙት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹የአፍሪካ ኅብረት በእጁ ያሉትን በአኅጉሩ ሰላምና ፀጥታ የመፍጠሪያ መሣሪያዎች በአግባቡ እንዲጠቀም የሚጎተጉት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህ ውስጥ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አለ፣ የአፍሪካ ተጠባባቂ ሠራዊት አለ፣ የአፍሪካ ሰላም ፈንድ አለ፣ የሽማግሌዎች ፓናልን ጨምሮ ሌሎችም መዋቅሮች አሉት፡፡ እነዚህን ሁሉ መሣሪያዎች ኅብረቱ በአኅጉሩ የጥይት ጩኸት የማይሰማበት ሁኔታን ለመፍጠር ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመናል፡፡ ከመሣሪያ ጩኸት የፀዳች አፍሪካን የመፍጠሪያው ፍኖተ ካርታ እነዚህን መሣሪያዎች ተጠቅሞ ግጭትን የማድረቅ፣ ግጭትን የማስወገድና ግጭትን በማስቆም መልሶ የመገንባት ሥራ የማካሄድ ሥራዎችን ለማስተግበር በሚያስችል ሥልት ነው ዕቅዱ የተቀረፀው፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ የጠመንጃ አፈሙዝን የመዝጋቱ ግብ አልተሳካም ብሎ ለመደምደም ሳይሆን፣ ዕቅዱ የገጠሙትን መሰናክሎችና ምክር ቤቱ አተኩሮ መፍትሔ ሊያፈላልግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም ላይ ያተኮረ ነው ሪፖርታችን፤›› ብለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ተመራማሪዋ እንደተናገሩት በአፍሪካ የመሣሪያ ጩኸትን ለማድረቅ እጅግ የተደራጁና በዝርዝር የተቀመጡ ዕቅዶች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር የመከወኑና ሥራ ላይ የማዋል ችግር ስላለ አኅጉራዊው ግብ በታለመለት ጊዜ እንዳይሳካ እንቅፋት መሆኑን አውስተዋል፡፡ በአኅጉሩ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችሉ መዋቅሮችና ዕቅዶችን ለማበጀት የተሰጠውን ትኩረት ያህል አኅጉሩን በተግባር ከግጭት ለማላቀቅ፣ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱን ሪፖርታቸው በአጠቃላይ እንደሚጠቁም ገልጸዋል፡፡
ትፍስህት አክለው፣ ‹‹በአፍሪካ የግጭት ቁጥርንም ሆነ ጂኦግራፊያዊ ሥርጭትን እየጨመረው ያለው አንደኛ የሽብር ጥቃት መበራከቱ ነው፡፡ በሁለተኝነት ሕጋዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጦች ከ2020 ወዲህ መጨመራቸው ነው፡፡ ሌላኛውና ብዙ ጊዜ የማይወራው ደግሞ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መጨመር ነው ችግሩን ያባብሰዋል፤›› ብለዋል፡፡ በአኅጉሩ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዳከም ሌላው ከፍተኛ ችግር የሆነና በአሁኑ ስብሰባ እንዲተኮርበት የሚፈልጉት ቁልፍ ነጥብ መሆኑን ያወሱት ተመራማሪዋ፣ ግጭትን በተመለከተ በአፍሪካ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በአግባቡ የመጠቀምና በተግባር የማዋል ችግር ሥር የሰደደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጦር መሣሪያ ጩኸት የማይሰማባት አፍሪካ (Silencing the Guns in Africa) ግብ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በአል ሲከበር እ.ኤ.አ. በ2013 ነበር የተጀመረው፡፡ እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ከግጭት እንዲሁም ከጦር መሣሪያ ጩኸት የፀዳች አፍሪካን የመፍጠር ህልም የኅብረቱ አባል አገሮች ሰንቀው ነበር፡፡ ይሁንና ይህ አኅጉራዊ ግብ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ባለመሳካቱ የአፍሪካ መንግሥታት የጊዜ ሰሌዳውን በመከለስ ወደ 2030 እንዲራዘም ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
From The Reporter Magazine
የአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የጠመንጃ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን የመፍጠሩ ግብን ለማሳካት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ተግባራዊ ዕርምጃዎች የሚዘረዝር የሉሳካ ዋነኛ ፍኖተ ካርታ (The Lusaka Master Roadmap-2016) የተባለ ዕቅድ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህንኑ የተከለሰ ዕቅድ ደግሞ ኅብረቱ እ.ኤ.አ. በ2017 ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አፅድቆት ነበር፡፡ ዕቅዱ በአፍሪካ ለሚፈጠሩ ግጭቶች መሠረታዊ ምንጮችን የመረመረ ነበር፡፡ ፖለቲካዊ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት፣ የአካባቢ ደኅንነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት የመሳሰሉ እርስ በእርስ የተሳሰሩ ጉዳዮችን በመመርመር የቀረበ ነበር፡፡