- በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ኢትዮጵያንና ሶማሌላንድን በኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ለማስተሳሰር ታቅዷል
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከዓለም ባንክና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚደረገው የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3.0) ፍኖተ ካርታ ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ተደረገ፡፡
እ.ኤ.አ በ2028 በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የኢትዮጵያንና የሶማሌላንድን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ፕሮጀክት ለማስጀመር ዕቅድ መኖሩም ተመላክቷል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው ፍኖተ ካርታ ፕሮግራሙ ቀጣናዊ ትስስርንና የኃይል ንግድ ለማሳደግ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፣ ዓመታዊ የኃይል ሽያጭ መጠን ከ1,500 ጊጋ ዋት በሰዓት ወደ 5,000 ጊጋ ዋት በላይ በሰዓት ለማሳደግ ውጥን መያዙን ያመለክታል። ለዚህም እ.ኤ.አ. በ2028 በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ወደ ሶማሌላንድ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ትስስር ፕሮጀክት ለማስጀመር ዕቅድ መኖሩንና ፕሮጀክቱ በመንግሥት ፈንድ እንደሚደረግ ፎኖተ ካርታው ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ታንዛኒያ የሚካሄደውን የኃይል ሽያጭ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግና ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር የሚደረጉ የኃይል ግዥ ስምምነቶችን (Power Purchase Agreements) በይፋ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም በፍኖተ ካርታው ተብራርቷል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማስፋፋትና የታዳሽ ኃይል ማመንጫ አቅሟን በማሳደግ ረገድ የሚደነቅ እመርታ ማሳየቷን፣ እ.ኤ.አ. በጥር 2025 ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በተካሄደው የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ ከአጠቃላይ አባወራዎች ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ የአንድ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው ተመላክቷል፡፡
ከብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር (Grid) ጋር የተገናኙ 29.3 በመቶ፣ ከዋናው መስመር ውጪ በሆኑ የፀሐይ ብርሃን (ሶላር) አማራጮች የሚጠቀሙ 35.7 በመቶ ዜጎችን ናቸው ተብሏል። ሆኖም መሠረታዊ የሆነውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት (ደረጃ 1 እና ከዚያ በላይ) ማግኘት የቻለው የአገሪቱ ሕዝብ 44 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ከታዳሽ የፀሐይ፣ የንፋስና የእንፋሎት የኃይል አማራጮች ጋር ተዳምረው ኢትዮጵያ በዘላቂ የኃይል ልማት ረገድ ያላትን መሪነት ቢያሳዩም፣ አሁንም ድረስ ወደ 56 በመቶ የሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ መሠረታዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኝ ተብራርቷል።
From The Reporter Magazine
ከዚህም በላይ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑት አባወራዎች (ቤተሰቦች) አሁንም ለማብሰያነት በባህላዊ እንጨትና ከእንሳሳት ተፈረ ምርቶች ከሚገኝ ኃይል ጥገኞች መሆናቸውና ይህም በጤና፣ በደኅንነት፣ በደን ጥበቃና በኢኮኖሚ ምርታማነት ላይ ከባድ አደጋዎችን መደቀኑ ተገልጿል። በፕሮግራሙ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2030 የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 75 በመቶ፣ የንፁህ ማብሰያ የኃይል አማራጮች ተደራሽነት ደግሞ አሁን ካለበት ስምንት በመቶ ወደ 57.7 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል።
ፕሮግራሙ ለተጨማሪ 9.23 ሚሊዮን አባወራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን እንዲቀርብ የሚያስችል መሆኑን፣ ብሔራዊ የተደራሽነት ምጣኔውንም ከ44 በመቶ ወደ 75 በመቶ እንደሚያሳድግ፣ ከዚህም ውስጥ ቢያንስ 70 በመቶ ከብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር (Grid)፣ እንዲሁም 30 በመቶ ከዋናው ውጪ (Off-Grid) በሚቀርብ የኃይል አማራጭ ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በኃይል ልማት እሴት ሰንሰለት ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ እንዲያድግ እንደምትፈልግ፣ በዚህም ኢንቨስትመንትን በማነቃቃትና ተቋማትን በማጠናከር እ.ኤ.አ. በ2030 ከግሉ ዘርፉ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለማሰባሰብ ዕቅድ እንዳላት ተገልጿል። በፕሮግራሙ የተቀመጡ ግቦች ለማሳካት እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ በአጠቃላይ ከ9.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 4.9 ቢሊዮን ዶላር ከአጋር ድርጅቶች በብድርና በዕርዳታ፣ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገቢ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም ከ163 ሺሕ ዶላር በላይ የሚሆነው ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ፍኖተ ካርታው ያሳያል።
From The Reporter Magazine
ከዚህም ውስጥ 4.9 ቢሊዮን ዶላር ለኃይል ማከፋፈልና ተደራሽነት እንደሚውል ተገልጿል። መንግሥት የግል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ መፍቀድን ጨምሮ የተሻሻለ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር የመለስተኛ ብድር (Concessional Finance)፣ የልማት ድርጅቶች (SOEs) መልካም አስተዳደር ሪፎርምን ጨምሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ፍኖተ ካርታው ያመላክታል።
የግሉ ዘርፍ በኃይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈልና ሌሎች ተግባራት ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው መታቀዱን የሚገልጸው ፍኖተ ካርታው፣ መንግሥት የፕሮጀክት ዝግጅት ማዕቀፍ እንደሚያመቻች፣ የንዑስና የባለብዙ ዘርፍ ማሻሻያዎች በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር፣ የዋስትና አሰጣጥና የአየር ንብረት ፋይናንስ ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራትን እንደሚፈጽም ያስረዳል።
የፕሮግራሙን ዕቅን ትግበራ ቅንጅት፣ አፈጻጸምና ቁጥጥር ለመምራት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የስምምነት ትግበራና ክትትል ክፍል (Compact Delivery and Monitoring Unit – CDMU) እንደሚቋቋም ተገልጿል። የዚህ የሥራ ክፍል መቋቋምና ወደ ሥራ መግባት በሚገኝ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ እንደሚመሠረት ተጠቁሟል።
