ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዩ ዝግጅት የተገኘውን አገራዊ የምክክር ዕድል በኃላፊነት ስሜት በመጠቀም፣ ግጭትና ስቃይ ማብቃት አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲጀመር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ይህ ምክክር በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የገዘፈ ዓላማ ያለውና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። አገራዊ ጉባዔው የትላንትን ችግር ፈትቶ ለነገ መሠረት ለማኖር የሚያስችል መሆኑን፣ ታሪክን ለመፃፍ ደግሞ ብዕርና ብራና የሚሰጥ በመሆኑ፣ አጋጣሚውን በአግባቡ በኃላፊነት ስሜት መጠቀም ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።


ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሰላም፣ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችል ነው ሲሉ ተናግረዋል። እንደ አገር ይቅርታን፣ እርቅን፣ ምክክርን እንትከል ሲሉም አክለዋል።
ተመካካሪዎች ለዛሬ ሳይሆን ለነገ፣ ለራሳቸው ሳይሆን ለልጆቻቸው እንዲመክሩም አሳስበዋል። ውይይቱ የሚሳካው ተመካካሪዎች ለእኔ ሳይሆን ለእኛ፣ ለሰፈሬ ሳይሆን ለአገሬ ካሉ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም አንዱ ሌላኛው የሚያነሳውን ሐሳብ ሊያከብር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
“አገርን ስንገነባ ያልነበሩ፣ ስንጣላ የሚኖሩ አሞራዎችን በቃ ልንላቸው ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚያንዣብቡ አሞራዎች ያለ ኢትዮጵያ ፈቃድ አንድ ኪሎ ሥጋ መውሰድ አይችሉም ሲሉም ተናግረዋል።
አራት ሺሕ የምክክሩ ተመካካሪዎች ሁሉን ወገን የሚሰበስብ ምክክር ካደረጉ፣ በቀጣይ አገሪቱ የሚኖራት ሕገመንግሥት ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ያለምክክር የመጣው ሁሉ የሚቀደውና የሚቀይረው እንደማይሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ይህ ጉባዔ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አቅጣጫን የሚያቀና፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራና አስተማማኝ አገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
From The Reporter Magazine


በኢትዮጵያ ሥር የሰደዱ ችግሮች መኖራቸውን ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ መሠረታዊ ጉዳይ ምክክር መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውስብስብ የዝግጅት ሒደቶችን አልፎ እዚህ መድረሱንና ከዚህም በኋላ ምክክሩ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የጸጥታ ኃላፊና ተወካይ ባንኮሌ አዶዬ (አምባሳደር)፣ የአፍሪካ ኅብረት የዚህ ታሪካዊ ዕድል አካል መሆኑን ገልጸዋል። ለአገራዊ ዕድገት አገራዊ መልሶችን የሚያመጣውን ይህን ሒደት የአፍሪካ ኅብረት እንደሚደግፍም ይፋ አድርገዋል። ኅብረቱ በኢትዮጵያ፣ በቀጠናውና በአፍሪካ ሰላምን የማስረጽ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ “ዛሬ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ቀን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በዓለም በግጭት ያተረፈ አገር የለም፣ ብዙ ችግሮች የሚፈቱት በውይይት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ምክክሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት የለውጥ ነጥብ መሆኑን፣ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት የሚችሉበትና ለዓለም የሚያሳዩበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ግጭትና ስቃይ ኢትዮጵያ ውስጥ ማብቃት አለበት፣ ስለሆነም ሁሉም ጉዳዮች በውይይትና በንግግር ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ዋና ጸሐፊው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ የሚሰራው በውይይትና በንግግር በመሆኑ፣ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ጉባዔ የአፍሪካን ቀንድ ወደ ተስፋ የሚመራ እንደሚሆንም ዋና ጸሐፊው ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሰንጎን ኦባሳንጆ ፣ ምክክሩ ኢትዮጵያን እንደ አገር ትልቅና የአፍሪካ መሪ አገር የማድረግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም ዓላማ ከተሳካ በዓለም መሪ መሆን የሚያስችል ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የምክክር ጉባዔው ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ጥቅም አልባና ውይይት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት የሚያስችል ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።