የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በሁሉም የፌዴራል ተቋማት እየተተገበረ ያለው የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውስጥ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ቢያደርግም፣ የመጨረሻ ውሳኔዎችንም ሆነ ሕጋዊ ተጠያቂነት ግን በመንግሥት ኃላፊዎችና በባለሙያዎች ላይ እንደሚሆን የሚያደርግ የአሠራር ማኑዋል ማፅደቁ ታወቀ።
የአሠራር ማንዋሉ የመንግሥት ግዥ ሒደት ዲጂታል ቢሆንም፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት ምክረ ሐሳብና ትንታኔ የሚያቀርብ መሣሪያ እንጂ፣ የመጨረሻ ግዥና ንብረትን የተመለከተ ውሳኔ የሚሰጥ አካል እንዳልሆነ፣ የሕጋዊ ተጠያቂነትና የውሳኔ ሥልጣን በመንግሥት ኃላፊዎች እጅ እንደሚቀጥል ያስረዳል።
በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ተፈርሞ ሐምሌ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሁሉም የፌዴራልና መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተላከ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ የቀረበው ሪፖርተር የተመለከተው ማኑዋል፣ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ (e-GP) ሥርዓት ውስጥ የሚፈጠሩ መረጃዎችንና ሰነዶችን በትክክል ለመያዝና ለማስተዳደር የሚያስችል ስለመሆኑ ይገልጻል።
በሰነዱ ምዕራፍ ስምንት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዝግጁነትና የግዥ ትንተና በሚል አርዕስት ከተካተቱት አንቀጾች መካከል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥልታዊ የትግበራ መስኮች የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል።
በእነዚህ ድንጋጌዎች እንደተገለጸው፣ ሥርዓቱ በግዥ ዑደት ውስጥ ሥጋቶችን ለመቀነስና ሥልታዊ ውሳኔዎችን ለመደገፍ የሚያተኩርባቸው የትግበራ መስኮች መካከል የተናጠል ማጭበርበር ማወቂያ ማለትም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች በግዥ ዑደት ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ተከታትለው ያልተለመዱ ባህሪያትንና የሙስና አመላካቶችን (Red Flags) በራስ ሥር መለየት፣ የተቀናጀ የጨረታ ማጭበርበር ማወቂያ ማለትም በአቅራቢዎች መካከል የሚደረጉ ሚስጥራዊ የዋጋ ስምምነቶችንና የተቀናጁ የጨረታ ማጭበርበሮችን መለየት የሚያስችል የላቀ የባህሪ ትንተናም ማከናወን የሚሉት ይገኝበታል።
ከእነዚህ ባሻገር ሥርዓቱ ሁለንተናዊ የአቅራቢዎች ሥጋት ምዘናን አቅራቢዎች ጨረታ ላይ ከመሳተፋቸው ወይም ውል ከመፈረማቸው በፊት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቱ የአቅራቢዎችን አጠቃላይ የደኅንነትና የብቃት ደረጃ የአፈጻጸም ታሪካቸውን፣ የውል ማጠናቀቂያ መጠን (Contract Completition Rate)፣ የቅሬታና የሕግ ታሪክ፣ እንዲሁም የፋይናንስ ጤንነት መረጃዎችን በቁልፍነት በመያዝ ያሠላል ተብሏል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቱ ውል ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ደረጃ በመከታተል፣ ሊከሰቱ የሚችሉ መስተጓጎሎችን አስቀድሞ የመተንበይ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መረጃዎችን፣ የአየር ንብረት ሁኔታዎችንና የቀድሞ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ታሪክን በማቀናጀት፣ የትኞቹ ውሎች ሊዘገዩ እንደሚችሉ፣ የትኞቹ ላይ የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችልና የአፈጻጸም ችግሮች የየትኛዎቹ ጋር እንደሚከሰቱ ለገዥው ተቋም የበላይ አመራር አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥም በአሠራር ማንዋል ሰነዱ ተገልጿል።
From The Reporter Magazine
በተጨማሪም ሥልታዊ የግዥና የበጀት ትንበያ፣ የዋጋ ንፅፅርና ብልህ የገበያ ጥናት (Price Intelligence and Value for Money Assessment)፣ ሁለንተናዊ የአፈጻጸም ሥልታዊ ትንተና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቱ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ይሁንና የአሠራር ማኑዋል ሰነዱ እነዚህን ድንጋጌዎች ተከትሎ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሥነ ምግባር መርሆዎች በሚል አንቀጽ ሥር ካሠፈራቸው ንዑስ አንቀጾች በቀዳሚው ቀጣይነት ያለው የሰው ቁጥጥር እንደሚኖር ገልጿል።
ንዑስ አንቀጽ 8.4.1 ይህን ሲያብራራ፣ ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች በግዥ ሒደት ውስጥ የሚያመነጩት ማናቸውም ዓይነት የመረጃ ትንተና፣ የሥጋት ደረጃ ጠቋሚ ወይም የውሳኔ ምክረ ሐሳብ በራሱ ደረጃ የመጨረሻ ሕጋዊ ውሳኔ ሆኖ ሊያገልግል አይችልም፤›› ይላል።
From The Reporter Magazine
አያይዞም፣ ቴክኖሎጂው ሥልታዊ የውሳኔ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያ ብቻ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ ማናቸውንም ጨረታዎች የመሰረዝ፣ አቅራቢዎችን የማገድ፣ ውል የማፅደቅ ወይም የክፍያ ትዕዛዝ የመስጠት የመጨረሻ ሕጋዊ ውሳኔ ሁልጊዜም በሕግ በተፈቀደለት ተጠያቂነት ባለው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ወይም ባለሙያ አማካይነት እንደሚፈጸም ይገልጻል።
በተጨማሪም የአሠራር ማንዋል ሰነዱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች የሚጠቀሙባቸው ሥልተ ቀመሮች (Algorithms) ሚስጥራዊ ወይም ሊመረመሩ የማይችሉ (Black Box Systems) መሆን እንደሌለባቸው ይደነግጋል።
ሥርዓቱ ለምሳሌ የአንድን አቅራቢ ሥጋት ከፍተኛ አድርጎ መመደብ ወይም የተወሰነ የገበያ ዋጋን መጠቆም ሥራ ካከናወነ በምን ዓይነት መሥፈርቶች፣ የውሂብ ስብስቦችና አመክንዮዎች ላይ ተመሥርቶ እንደተወሰነ ለኦዲተሮች፣ ለሕግ አስከባሪዎችና ለባለሥልጣኑ የቁጥጥር ክፍል በግልጽ ሊያብራራና ሊመረመር የሚችል መሆን እንዳለበት ተገልጿል።
በሌላ በኩል የተቋማዊ ተጠያቂነት መርህ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት የቀረበ ማንኛውም ምክረ ሐሳብ ወይም ትንታኔ ሕጋዊ ተጠያቂነቱን ወደ ሥርዓቱ እንዳያዞር ያስቀምጣል። የግዥ ውሳኔ በማን እንደተሰጠ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነቱም ሕጋዊ ሥልጣን ባላቸው ኃላፊዎች ላይ እንደሚቆይ ተብራርቷል።
ድንጋጌው ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት ያመነጨው ውጤት፣ ሥሌት ወይም የትንበያ ምክረ ሐሳብ ስህተት ቢኖረው እንኳን ይህ ቴክኖሎጂያዊ ምክንያት ሰብዓዊና ተቋማዊ ተጠያቂነትን ፍፁም ሊተካ ወይም ሊያቃልል አይችልም። በኢ-ጂፒ ሥርዓት ውስጥ ለሚፈጸሙ ማናቸውም ሥልታዊ ተግባራት፣ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና የሕግ መጣስ ድርጊቶች ቀዳሚውንና የመጨረሻው ተጠያቂነት ውሳኔውን ያሳለፉትና ሒደቱን የመሩት የሚመለከታቸው የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የግዥ ኮሚቴዎችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ብቻ ይሆናሉ፤›› ይላል።
ማንዋሉ በተጨማሪ የግል መረጃ ጥበቃን በተመለከተ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች በአገሪቱ የመረጃ ጥበቃ ሕጎች መሠረት እንዲሠሩ ያስገድዳል። በተለይ የግል መለያ መረጃዎች (Personally Identifiable Information – PII) ከሕጋዊ ፈቃድ ውጪ እንዳይሰበሰቡ፣ እንዳይጋሩ ወይም ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ይደነግጋል።
ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት አጠቃቀም በተጨማሪ የአሠራር ማንዋሉ የሥርዓቱን አፈጻጸም በቀጣይነት ለመከታተል የክትትልና የአፈጻጸም ምዘና ሥርዓት እንደሚተገበር ያመለክታል። ይህ ሥርዓት የኢ-ጂፒ መድረኩ የሚያመነጨውን መረጃ በመጠቀም የግዥ ሒደቶችን፣ የሥርዓቱን ቅልጥፍናና ውጤታማነት በቀጣይነት እንደሚገመግም ይገልጻል።
ለዚህም ባለሥልጣኑ የቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎች (Key Performance Indicators – KPIs) እንደሚጠቀምና እነዚህ መለኪያዎች የሥርዓቱን አጠቃላይ አፈጻጸም ለመገምገም፣ የግዥ ሒደቶች በታቀደው መንገድ እየተፈጸሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች ለመለየት እንደሚውሉ ተገልጿል።
በሰነዱ የተዘረዘሩት ዋና ዋና የክትትል መለኪያዎች የመንግሥት ተቋማት የሥርዓቱን አጠቃቀም፣ የተጠቃሚዎች የሥርዓት ተሳትፎ፣ የመረጃ ጥራት፣ የመረጃ ደኅንነት፣ የተቋማት የአፈጻጸም ውጤትና የሥርዓቱን አጠቃላይ ብቃት እንደሚያካትቱም ተብራርቷል።
በተጨማሪም የክትትል ማዕቀፉ የውሂብ ትንተና (Data Analytics) በመጠቀም የግዥ ሒደቶችን በቀጣይነት እንደሚተነትንና የሚሰበሰበው መረጃ ለአስተዳደራዊ ውሳኔዎች፣ ለሥርዓት ማሻሻያና ለአፈጻጸም ምዘና እንደሚውል ይገልጻል፡፡