- የጥቅም ግጭት እንዳይከስት ይደረጋልም ተብሏል
በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ የተለያዩ ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፣ የድርጊት መርሐ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች አንፃር በኢትዮጵያ ያለው የሒሳብ አያያዝ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛና ለውድድር ሊቀርብ እንደማይችል፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ በውጭ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሙያቸው የሒሳብ አያያዝ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ መታቀዱን ለሪፖርተር ገልጸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሙያዊ የበጎ ፈቃደኛነት ፖሊሲ ከቀናት በፊት በቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ መፅደቁንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በፖሊሲው መሠረት የሒሳብ አያያዝ ልምድና ዕውቀት ላላቸው ባለሙያዎች ግልጽ ጥሪ በማድረግ፣ ተወዳድረው በሙያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ መታሰቡን ተናግረዋል።
የሒሳብ አያያዝ፣ የኦዲትና ሒሳብ ማረጋገጥ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት የያዙ ድርጅቶችን ኦዲት ማድረግ፣ የተቋማት ዘላቂነት ሪፖርት ማቅረብ፣ ዲጂታል አካውንቲንግና ሥነ ምግባራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ ሥጋት መከላከልና ሳይበር ሴኪዩሪቲ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከውድድሩ መሥፈርቶች መካከል ተጠቃሽ ተደርገዋል።
ፖሊሲው አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች ውል እንዲገቡ እንደሚያደርግና ሊወጡ የሚገቧቸው መብትና ግዴታዎችን ማካተቱን የጠቆሙት አቶ ውብሸት፣ ይህን ተከትለው በማይሠሩ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ጨምረው ጠቁመዋል። አገልግሎት ለመስጠት የሚመዘገቡ ባለሙያዎች መሥፈርት በፖሊሲው የተካተተ ሲሆን፣ በትንሹ ከታወቀ ዩኒቨርስቲ በአካውንቲግና ፋይናንስ ዘርፍ የመጀመሪ ዲግሪ እንደሚያስፈልግ ሠፍሯል።
ይህንን አገልግሎት መስጠት ከቦርዱ ዕውቅና፣ ሽልማትና ከዘርፉ ጋር በተገናኘ በሚከናወኑ ሥራዎች ቅድሚያ ዕድል የሚያስገኝ ጥቅም እንዳለው አቶ ውብሸት አብራርተዋል።
የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር የሚያስችሉ ጉዳዮች በፖሊሲው ውስጥ መኖራቸውንና አንድ ባለሙያ በፊርማው ግልጽ አድርጎ ወደ አገልግሎት እንዲገባ እንደሚደረግ የገለጹት ዋና ዳይሬከተሩ፣ ቦርዱም ክትትልና ቁጥጥር የሚያክናውን ባለሙያ ይመድባል ብለዋል።
From The Reporter Magazine
ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑንና ሥልጠና መስጠት ሊያስፈልግ እንደሚችል ጠቅሰው፣ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሙከራ ደረጃ እንዲጀመር እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የሙከራ አገልግሎቱን ከአምስት እስከ አሥር በሚሆኑ ባለሙያዎች ይተገበራል ተብሎ እንደሚታሰብና ከዚህ የሚገኘውን ውጤት እየታየ ቁጥሩን የመጨመር ተግባራት እንደሚኖሩ፣ እየተዘጋጀ ያለው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር እንደተጠናቀቀ ለባለሙያዎች ጥሪ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ቁጥርን ለመጨመር የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋሙንና በተመጣጣኝ ክፍያ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን፣ ይህም ከአንድ ሺሕ የማይበልጠውን ደረጃውን የጠበቀ ባለሙያዎች ቁጥር እንደ አገር ለመጨመር ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል። ይህም ይበልጥ ክፍት እየሆነ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ባለሙያዎች እንዳይቆጣጠሩት ለማድረግ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።