እ.ኤ.አ. በ2025 ዕዳው ወደ 122 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡ በገለልተኛ ኦዲተሮች ይፋ ተደርጎ የነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በ2018 በጀት ዓመት ለዘመናት ከተከማቸበት ዕዳ ወጥቶ 39.5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፣ 2018 በጀት ዓመት ተቋሙ ለዓመታት ከተከማቸበት ዕዳ ወጥቶ ወደ ትርፍ የተሸጋገረበት ዓመት እንደነበርም ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኦዲት ሰርቪስ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የተፈራረሙበትና በገለልተኛ ኦዲተሮች ተከናውኖ እ.ኤ.አ. በየካቲት 2026 የወጣው ሰነድ ኪሳራው እ.ኤ.አ. በ2025 122 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቆ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ሆኖም አቶ ሞገስ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ ለዓመታት ከነበረበት ኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፍ የተሸጋገረበትንና ያልተጣራ 39.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
ለተደጋጋሚ ጊዜ ይቀርብ የነበረውን የተቋሙ ከፍተኛ ዕዳ መንግሥት መሸከሙ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ፣ የአገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም እጥፍ በሚባል ደረጃ መጨመሩና የዳታ ማይኒንግ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሥራ መጀመራቸው ለተገኘው ውጤት ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል የነበረበት ዕዳና ወለድ ተከፍሎ ማለቁን፣ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ያለበትን ብድር በተመለከተ ደግሞ እስከ ኅዳር 2019 ዓ.ም. ያለውን ከፍሎ መጨረሱን፣ ለአብነትም የቻይናው ኤግዚም ባንክ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተቋሙ ትርፍ ውስጥ ለውጭ አገሮች ከሚቀርብ የኤሌክትሪክ ኃይልና ከዳታ ማይኒንግ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት የተሰበሰው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ475 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን አቶ ሞገስ አስረድተዋል። በሥራ ላይ የሚገኙት 25 የዳታ ማይኒንግ ተቋማት በሥራቸው እንደሚቀጥሉና አዲስ ተቋም የማስገባት ዕቅድ እንደሌለ ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
በበጀት ዓመቱ የፕሮጀክቶች አስተዳደር አቅም ማነስ፣ የፀጥታ ችግር፣ የቁሳቁሶች ስርቆት፣ የወሰን ማስከበር መዘግየት፣ የግዥ ሒደት መጓተት፣ የሎጂስቲክስና የነዳጅ እጥረት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ያደረጉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል።
ስርቆት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉንና ለአብነትም የባህር ዳር – ወልዲያና የአዘዞ – ጭልጋ መስመሮች አፈጻጸምን ወደኋላ እንዲጎተት ማድረጉን አቶ ሞገስ ገልጸዋል። ይህን በአግባቡ መቆጣጠር ካልተቻለ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ የሚፈለገውን አገልግሎት ካልሰጡ ደግሞ ኮንትራክተሮች የይገባኛል ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉና ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ ትልቅ ሥራ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።
መዘግየቶችን በማስቀረት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅ ሒደትን አጠናክሮ በማስቀጠል የተቋም ውጤታማነትን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
From The Reporter Magazine
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማኅበረሰቡ በአካባቢው የሚያልፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲወጣ በማድረግ በስርቆት ምክንያት ይከሰት የነበረ ጉዳትን በተሻለ መጠን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል።
ወደ ጤናማ ሁኔታ የገባውን የተቋሙን የፋይናንስ ሥርዓት ማስቀጠል የተቋሙ የ2019 በጀት ዓመት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን፣ ሆኖም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች ኤልኒኖ በምሥራቅ አፍሪካ ሊከሰት እንደሚችል መጠቆማቸውን ጠቅሰው፣ ጫና ካልፈጠረ በቀር የተገኘውን ትርፋማነት የማስቀጠል ቁርጠኝነት እንዳለ ገልጸዋል።
እየተገነባ የሚገኘውና የምዕራፍ አንድ ሥራው የተጠናቀቀውን የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅና 40 ጊጋዋት ኃይል ወደ ብሔራዊ ማከፋፈያ ቋት በማስገባት፣ አጠቃላይ አገራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን 9‚770 ሜጋ ዋት ለማድረስ መታቀዱን አስረድተዋል።
በ2019 በጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ፣ አንዳንዶቹም ከኮፕ 32 ጉባዔ ጋር በተገናኘ ከአዲስ አበባና እስከ አዳማ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚተገበሩ መሆናቸውን ገለጸዋል። የኮፕ ጉባዔን ተከትሎ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የመቆጣጠሪያዎችን አቅም ከማሳደግና ከማስፋፋት ሥራዎች በተጨማሪ፣ የአዳዲስ መስመሮችና ማከፋፊያዎች ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመከላከልና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን የመገምገም ዓላማ ያለው ጉባዔው፣ እ.ኤ.አ. በ2027 በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
በሌሎች አካባቢዎች የሚተገበሩ ፕሮጄክቶች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ሞገስ፣ የፕሮጀክቶቹ ዓይነትና የሚተገበሩበት አካባቢ የት ነው የሚለው ወደፊት ይገለጻል ብለዋል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ አዲስ የውጭ አገር የኤሌክትሪክ ሽያጭ የሚያደርግበት አገር እንደማይኖር፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሥርጭት ለማስቀጠል ዕቅድ መኖሩን ገልጸዋል።
በተለይ በሱዳን ያለው የኃይል አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡንና ወደፊት ምን ሊፈጠር እንደሚችል እንደማይታወቅ፣ የታንዛኒያም በሙከራ ደረጃ መሆኑንና ወደ ዋናው ሽያጭ አለመገባቱን፣ ወደ ውጭ የሚቀርብ የኃይል አቅርቦት ዕቅድ አፈጻጸም ባለበት ለመቀጠል መታሰቡን ጠቅሰዋል።
ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካመነጨው አጠቃላይ ኃይል ውስጥ 93 በመቶውን ለአገር ውስጥ፣ ቀሪ ሰባት በመቶውን ደግሞ ለጎረቤት አገሮች ማቅረቡን የተቋሙ መረጃ ያሳያል።