ጉዞ ከሃያ ሁለት ወደ መርካቶ ተጀምሯል፡፡ በሥራም ሆነ በትምህርት ምክንያት በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ገባ ብሎ መውረድ አይቀርም፡፡ ይህ አባባል የሚመለከተው መኪና የሌላቸውን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ በታክሲ ሲሄዱ አፌ ቁርጥ ይበልላችሁ የሚባሉ፣ ወይም ደግሞ አፋችሁ ይቆረጥ መባል የሚገባቸው ወያላና ሾፌር ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ሥርዓተ አልባ ወያላዎች የተማረሩ ሰዎች፣ ‹‹እግዜር ይይላችሁ…›› ብለው ተራግመው ሲወርዱ፣ ሌሎች ደግሞ ‹ለመብቴ መንግሥትንም ሆነ እግዜርን መጥራት አይጠበቅብኝም› በሚመስል ስሜት የአፍ ጦርነት ይማዘዛሉ፣ ይጨቃጨቃሉ፣ የሚቧቀሱም አይጠፉም፡፡ እነሱ እንደሚሉት መብታቸውን ያስከብራሉ ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወያላዎች፣ ‹‹መብቴ ነው!›› የሚላቸው ሰው ጠላታቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹መብታችሁ ታክሲ ውስጥ ትዝ አይበላችሁ›› በማለት ታክሲያቸው ውስጥ በሰቀሉት ጥቅስ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ካሳፈሩት ሰው ጋር ይጨቃጨቃሉ፣ ይወዛገባሉ፡፡ በአንድ በትንሽዬ አጋጣሚ ሳይሆን በርስት ወይም በሌላ ንብረት የሚከራከሩ ነው የሚመስሉት፡፡ አንድ ሰው፣ ‹‹ወገኖቼ ኧረ በደህና ነገር እንጨቃጨቅ፡፡ ማን ይሙት አሁን ደህና ውይይት የሚሻ አገራዊ ጉዳይ ጠፍቶ ነው እንደዚህ በረባ ባልረባው የምንነታረከው?›› አለ፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹አየህ ሰው በርካታ ብሶቶች ሳይኖሩበት አይቀርም፡፡ ስለዚህ ትንሽ ነካ ስታደርገው በሆዱ ውስጥ አፍኖ ያቆየውን ሁሉ ይዘረግፈዋል፡፡ ወዶ አይደለም በሰው አትፍረድ…›› አለው፡፡ ምክር መሆኑ ነው!
የሁለቱ ሰዎች ክርክር ታክሲዋን በከፊል ተቆጣጠራት፡፡ የመጀመሪያው ወጣት፣ ‹‹ቢሆንም ለአገርም ለሕዝብም በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መከራከር ያዋጣል፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች ጊዜያችንን እያጠፋን አዕምሯችንን ከምናደንዘው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ይበጀናል…›› ሲል አንዲት ወጣት ደግሞ፣ ‹‹እውነት ነው፣ ለምን ሰሞኑን በፓርላማ ስለፀደቀው ተጨማሪ በጀት አናወራም? ለምን ስለኑሮ ክብደት አናወራም? ኧረ እንዲያውም ወሳኝ ስለሆነው ህልውናችን ጉዳይ ለምን አንነጋገርም?›› በማለት አስተያየቷን ሰነዘረች፡፡ ወሬውም እየጦፈ ሄደ፡፡ ወጣቱና ወጣቷ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ወግ ቀጠሉ፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች አፌን በዳቦ ያሉ ይመስል ጭጭ አሉ፡፡ አንድ ጎልማሳ በታፈነ ድምፅ፣ ‹‹አሁን የተጨማሪ በጀት ወሬ ምን ያደርጋል? ክፉ እያናገረን ለክፋት ይዳርገናል…›› አለ፡፡ ‹‹ከተነሳማ እንነጋገርበት እንጂ… አገር በምርት የሚያትረፈርፋት የልማት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ በጣም ብዙ ዜጎች አምራች መሆን ሲገባቸው፣ በየቦታው በተለኮሰ ግጭትና በኮሪደር ልማት ምክንያት አነስተኛና መካከለኛ ንግዶች ከሥራ ውጪ እየሆኑ እንዴት ተደርጎ ነው ኑሮን መቋቋም የሚቻለው… ምርታማነት ሳይኖር እንዴት ሆኖ ነው ለተጨማሪ በጀቱ ተጨማሪ ግብር የሚሰበሰበው…›› እያለ አንድ ምሁር መሳይ ጎልማሳ ሲተነትነው በፀጥታ አዳመጥነው፡፡ ከባድ ሚዛን በሉት!
መሀል ወንበር የተቀመጡ ሽበታም አዛውንት፣ ‹‹አንተ ግሩም የሆነ ነገር ነው የነገርከን… ለመሆኑ ኢኮኖሚክስ ነው ወይስ ምንድነው የምታስተምረው…›› እያሉ ሲጠይቁት፣ ‹‹እኔ በእርግጥ ድሮ የፊዚክስ መምህር ነበርኩ… ኢትዮጵያ ውስጥ በመምህርነት ኑሮን ማሸነፍ ስለማይቻል ነጋዴ ሆኛለሁ…›› ከማለቱ፣ ‹‹ወይ ጊዜ ድሮ በእኛ ወጣትነት ዘመን እኮ ‹የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ሊወስድሽ ነው አስተማሪ…› ይባል ነበር… ወይ ጊዜ ጭራሽ ከመምህርነት ወደ ነጋዴነት መዘዋወር እንደ ዋዛ ይጀመር…›› ብለው አንዲት እናት ሲናገሩ ትካዜ ውስጥ ገባን፡፡ አዛውንቱ ግን፣ ‹‹ቅድም ያነሳኸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድ አካል የሆነው የፊስካል ፖሊሲ ግን በመንግሥት ችላ የተባለ ይመስለኛል፡፡ ሞኒተሪ ፖሊሲው ላይ በርትቶ ፊስካሉን ያለ ምርታማነት አስቀጥላለሁ ብሎ ካሰበ ችግሩ ገፍቶ መመለሻ እንዳያጣ እሠጋለሁ…›› ሲሉ ብዙዎች ግራ ተጋብተው ሲያዩዋቸው ወያላው፣ ‹‹ፋዘር ታክሲያችንን ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አስመሰላችሁት እኮ…›› ብሎ ሲስቅ አብረን ሳቅን፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!
‹‹በአንድ አገር ውስጥ ሕዝብና መንግሥት የሚግባቡት የሚወጡ ፖሊሲዎች ለሕዝብ ኑሮ ዕድገት ፋይዳ ሲኖራቸው ነው…›› ጋቢና የተቀመጠ ወጣት መናገር ሲጀምር፣ ‹‹እነዚህ ወያኔዎች የትግራይ ሕዝብ ተሰቃዬ ብለው እዬዬ ሲሉ ከርመው ምን ሆነው ነው እርስ በርስ መባላት የጀመሩት… አራት ኪሎ ሥልጣን ላይ ሆነው ኢትዮጵያን እንደ ፈለጉ ሲዘውሩ ኖረው በተራቸው ሲባረሩ፣ ዞር ብለው ያላዩትን የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ለኩሰው አስፈጁት፡፡ ከጦርነት መልስ ሰላም ሠፈነ ብሎ ዕፎይ ከማለቱ እርስ በርስ ለዚያ ለፈረደበት ሥልጣን ጉሮሮ ለጉሮሮ ተያይዘው ሌላ መዘዝ እያመጡ ነው፡፡ ምን ዓይነት ጉዶች ናቸው?›› ብሎ አንድ ወጣት ከኋላ መቀመጫ ዱብ ዕዳ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ወጣቱን አሁንም በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹በጣም የሚገርመው እኮ በዚያ በሰለቸ ፖለቲካቸው ለሕዝብ ጥቅም እያሉ በሕዝብ ደም ሲነግዱ አለማፈራቸው ነው፡፡ ምን ያህል ሥልጣን እንደሚያባላቸው ለማወቅ በቀደም ለአንዲት ከተማ ሁለት ከንቲቦች መሾማቸው አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በሕዝቡ ላይ የጦርነት ደመና ማንዣበባቸው ነው…›› ሲል ብዙዎች ድጋፋቸውን ገለጹለት፡፡ አንዳንዱ እኮ ይናገረዋል!
የወጣቱ እንደዚያ መናገር ያስገረማቸው አዛውንቱ፣ ‹‹ልጄ አንተ ገና አንድ ፍሬ ብትሆንም ያነሳኸው ሐሳብ ግን ብስለት ያለው ነው…›› ብለው አሁንም በሰከነ አንደበት፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ወጣቱ በሰላም መኖር አይችልም ነበር፡፡ በልማት ስም ዝርፊያውን የቤተሰብና የዘመዳሞች ነበር ያደረጉት፡፡ ዴሞክራሲንም ቢሆን ስሙን እንጂ ግብሩን አያውቁትም፡፡ ሁሉም ፖለቲከኛ ዋና ግቡ ሥልጣን መሆኑ ቢታወቅም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ግን ያሳፍራሉ…›› አሉ፡፡ አንዲት ፊቷ ስልክክ ያለ ቀጭን ኑሮ የደቆሳት መሳይ ሴት፣ ‹‹ፖለቲከኞቹ ዋና ሥራቸው በእኛ ሕይወት መቀለድ እንደሆነ የገባቸው ከተረዱ እኮ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እኛ አልገባ እያለን እነሱ የሚናገሩትን ይዘን እንሮጣለን እንጂ፣ እነሱማ ለሥልጣናቸው መደላደል ሲሉ በላያችን ላይ ቢራመዱም ደንታቸው አይደለም፡፡ በልማት ስም ስንተባበራቸው ለእኛ ግን አዘኔታ የሚባል ነገር የላቸውም፡፡ እስኪ እናንተ ስለምትሻሉን ድምፃችንን እንሰጣችኋለን ብለን ቃላችንን የሰጠናቸው ተፎካካሪ ነው ተቃዋሚ የሚባሉትም ያው ናቸው፡፡ በስማችን እየተነገደ በድህነት ኖረን ወደ የማይቀርበት እንደ ከፋን እንሄዳለን…›› ብላ ዕንባ በጉንጮቿ ኮለል ሲል ደነገጥን፡፡ ‹‹አይ ልጄ አይዞሽ… ያልሽው ሁሉ ምንም ሐሰት የለውም፣ ነገር ግን የዘመኑ ፖለቲከኞች ብዙውን ነገር ረቀቅ እያደረጉት ስለሆነ ራስን መጠበቅ ነው የሚሻለው…›› ብለው እኚያ እናት ምክር ቢጤ ለገሱ፡፡ ሰሚ ካለ ጥሩ ነበር!
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው፡፡ መንገዱ እንደ ልብ አላላውስ ብሎ ጉዞው እንፉቅቅ ነበር፡፡ ‹‹ዕድሜ ለእነ ጆ ባይደንና የአውሮፓ ደንቆሮ መሪዎች ዓለም የኑክሌር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ በቀደም ዕለት ዩክሬንን ኑክሌር እናስታጥቃለን ብለው ጉራ ሲቸረችሩ፣ ቆፍጣናው ፑቲን አላርፍ ካሉ መላው የሩሲያ የኑክሌር ኃይል በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ማዘዙን ሰምተናል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የእነሱን ጉድ ሊዘረግፉ መሆኑ ያስበረገጋቸው ምድረ ወንበዴ ሁሉ፣ ከእነሱ ስም መጥፋት ይልቅ ዓለም እንድትጠፋ መርጠዋል…›› ብሎ ያ ምሁር መሳይ ጎልማሳ አጠገቡ ላለው ወጣት ሲያብራራለት፣ ‹‹አሁንማ ፈጣሪ የሰው ልጅ ጥፋት ስለሰለቸው መጨረሻችን ለመቃረቡ ወንድሜ ያልከው ነገር ጥሩ ማሳያ ነው…›› ብላ አንዲት ጠይም ወይዘሮ ተናገረች፡፡ የኑክሌር ወሬ ሲጀመር ብረት የሚያቀልጥ ሙቀት ወይም አጥንት የሚሰብር ብርቱ ቅዝቃዜ ዓይነት ስሜት የተፈጠረ ይመስል ሁላችንም ፀጥ አልን፡፡ ‹‹በዶሮ ፊት ፈንግል አይወራም›› እንደሚባለው ነው መሰል የኑክሌሩ ጉዳይ አስፈሪ ነበር፡፡ የፍርኃት ቆፈን ተለቆብን ‹‹መጨረሻ…›› ተብለን ወርደን ስንለያይ በቅጡ አልተሰነባበትንም ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!