- የወርቅ ግዥን ወደ ንግድ ባንኮች ለማዘዋወር ጥናት እየተደረገ ነው ተብሏል
- የወርቅ ሻጮች ለንግድ ባንኮች ወርቅ እንዲያቀርቡ ግፊት እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የአገሪቱ የመጀመሪያው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ፣ በመጪው አንድ ወር ውስጥ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር አስታወቁ።
ገዥው ይህንን የገለጹት የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በሰባተኛ ስብሰባው የገመገማቸውን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሁኔታዎች፣ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦችና የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ያፀደቃቸውን የፖሊሲ ውሳኔዎች አስመልክቶ ሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሲሰጡ ነው።
ከአፍሪካ አልፎ ከዚያ በላይ በግዙፍነቱ የሚጠቀስ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ (ሪፋይነሪ) ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት እዮብ (ዶ/ር)፣ ፋብሪካው በመጪው አንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ለአገሪቱ የወርቅ ገበያ እጅግ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የአገር ውስጥ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ፣ ቀደም ሲል ወርቅ ወደ ውጭ በመላክ እንዲነጠር ተደርጎ ከዚያ በኋላ ለሌሎች ክምችት በዶላር የመሸጠን አሠራር ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ነው ብለዋል። በመሆኑም ፋብሪካው ለኢትዮጵያ የወርቅ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ቀጣናው ትልቅ አቅም ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።
ገዥው ይህንን ቢሉም ፋብሪካው የት አካባቢ እየተገነባ እንዳለና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የፋብሪካው ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ከአራት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በሚያዚያ 2018 ዓ.ም. ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
የብሔራዊ ባንክ ገዥው በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ የማጣሪያ ፋብሪካው በመጪው አንድ ወር ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ከማሳወቅ ባሻገር፣ የወርቅ ግብይትን የተመለከቱ ተያያዥ ጉዳዮችንም አውስተዋል።
From The Reporter Magazine
በዚህም ከወርቅ ግብይት ጋር በተያያዘ የቁጥጥርና የመሪነት ሚናው ከብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ወደ ሌሎች የንግድ ባንኮች የሚዘዋወርበትን ሁኔታ በተመለከተ፣ በዝርዝር ለማጥናት ባንኩ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ ነው ብለዋል።
እንደ ገዥው ማብራሪያ ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ የወርቅ ገበያ ሥርዓት እጅግ ስኬታማ በመሆኑ የበርካታ አገሮች ልዑካን ተሞክሮውን ለመቅሰምና ለማጥናት ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚህ የተሻለና ይበልጥ ውጤታማ አሠራር የሚገኝ ከሆነ አሠራሩን ለመቀየር ጥናቶች እየተካሄዱ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ አለመጠናቀቁን ጠቁመዋል።
From The Reporter Magazine
በተያያዥም ወርቅ ሻጮች ከሁሉም የንግድ ባንኮች ጋር በጋራ እንዲሠሩ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ መሆኑን እዮብ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
እስካሁን ባለው ሒደት ግን አብዛኞቹ ሻጮች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ብቻ የመቆየት አዝማሚያ እያሳዩ በመሆናቸው፣ ሒደቱ ሙሉ በሙሉ ባይሳካም በቀጣይ ግን ይህንን ጥረት ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም እዮብ (ዶ/ር) የገንዘብ ኮሚቴው ሰባተኛ ስብሰባና የቦርዱን ውሳኔ አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የባንኩ የተጣራ የውጭ አገር ሀብት (Net Foreign Asset) እና የወርቅ ኤክስፖርት ማደግ ለመሠረታዊ ገንዘብ (Base Money) ዕድገት በዋና ምንጭነት ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ዕድገት አዝማሚያን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የመሠረታዊ ገንዘብ (Base Money) ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢቆይም፣ በቅርብ ጊዜያት የመቀነስ አዝማሚያና የመረጋጋት ምልክት እያሳየ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለዚህም በማስረጃነት በ2018 በጀት ዓመት የመሠረታዊ ገንዘብ ዓመታዊ ዕድገት በ43 በመቶ እንደነበረ፣ ይህም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 66.4 በመቶ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
‹‹ለመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገት ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በመጨመሩና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ባንኮች የገባው ጥሬ ገንዘብ መጨመሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፤›› ብለዋል፡፡
ማብራሪያቸውን ተከትሎም ይህንን ሁኔታ ለማረጋጋትና የገንዘብ ፖሊሲው ውጫዊ አስደንጋጭ ክስተቶችን (External Shocks) የመቋቋም አቅምን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በሚገዛበት ወቅት ተቀማጭ ሒሳቡና የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ (Reserve) እያደገ ይሄዳል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ወርቁን ለመግዛት የአገር ውስጥ ገንዘብ (ብር) ጥቅም ላይ የሚውል በመሆኑ፣ ይህ ሒደት ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባው ገንዘብ እንዲጨምርና መሠረታዊ የገንዘብ አቅርቦት (Base Money) እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው መገምገሙን አስረድተዋል።
ይህንን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የገንዘብ መብዛትና የዋጋ ግሽበት ሥጋት ለማረጋጋት ኮሚቴው የነደፈውን ሥልት ያብራሩት ገዥው፣ ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የሚያካሂደው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ወደ ኢኮኖሚው የገባውን ገንዘብ መልሶ ለመሰብሰብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
‹‹ይህ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሁለት ዋና ዋና ግቦች አሉት፡፡ በአንድ በኩል አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በገበያ ውስጥ እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ባንኩ ክምችቱን ለማሳደግ ወርቅ ለመግዛት ያወጣውን ብር መልሶ ከኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሰበስብ ያስችለዋል፤›› ብለዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በአሁኑ ወቅት የገበያውን መረጋጋት እያስተዳደረ ያለው በዚህ መጣጣም ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ፣ ገዥው በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።