በአብርሃም ተክሌ
ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቋን ባስታወቀች ማግሥት፣ ምርጫውን ለመጀመር ሁለት ቀናት ሲቀሩት የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ የጋሞ ሕዝብ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አርባ ምንጭ አመራ። ከፊል ፀሐያማ በሆነውና መጠነኛ ሙቀት ባለው የአየር ንብረት ከተማውን እየቃኘ በገባበት አንድ ምግብ ቤት፣ ሁለት የከተማዋን ነዋሪዎች ከሁለት ቀናት በኋላ ስለሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ጠይቆ ሁለት የተለያየ ግንዛቤዎችን አገኘ።
በሲቀላ ከተማ እንደተወለደ የተናገረው አንድ ወጣት ስለምርጫው ሲጠየቅ፣ ሒደቱ ምንም እንደማይመስለውና ግድ እንደማይሰጠው እንደሚከተለው ገለጸ። ‹‹ምርጫ ተደረገም አልተደረገም በዕለት ተዕለት ሕይወቴ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ አሁን ካለው የምግብ ዋጋ ንረትና ኢኮኖሚያዊ ጫና አንፃር የሚያሳስበኝ የኑሮ መወደድ እንጂ የፖለቲካ ካርድ አይደለም፤›› ብሏል። በተቃራኒው ደግሞ ባህሩ ሌመሶ የተባለው ነዋሪ ድምፁን ለመስጠት በጉጉት እንደሚጠባበቅ፣ ይህ ምርጫ ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ እንደሆነ በፅኑ እንደሚያምን ተናግሯል።


‹‹ይህ ምርጫ አገራችንን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መረጋጋት ለማሻገር ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓትና የተደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮች ሒደቱ ይበልጥ ግልጽና አካታች እንዲሆን መንገድ ከፍተዋል፤›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
በቅጽል ስሟ ‹‹ባርች›› በመባል የምትታወቀው የሆቴል እንስት አስተናጋጅ በበኩሏ፣ አገራዊ ምርጫውን በክልሉ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ በጉጉት የጠበቀው መሆኑን ጠቅሳ፣ ወጣት ሳይል በዕድሜ የገፉ አብዛኞቹ የከተማው ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጻለች። እንደ ባርች አባባል፣ በከተማው እየታየ ያለው ለውጥና የሥራ ዕድል በይበልጥ ወጣቱን አነሳስቶታል፡፡ እሷም ቀኑን በጉጉት እየጠበቀች እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡ ‹‹ባለፈው የ2013 ዓ.ም. ምርጫ አስተናባሪ ነበርኩ፡፡ አሁን ደግሞ መራጭ ሆኜ ቀኑን እየጠበቅኩ ነው፤›› ብላለች፡፡ ልክ እንደ ባርች ሁሉ፣ በሴቻ ከተማ ተወልዶ በባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ባህሩ ነጉ በበኩሉ፣ ምርጫው በጣም አስፈላጊ መሆኑንና በምርጫው ቀን ማልዶ በመነሳት ተወልዶ ባደገበት አካባቢ፣ በተለምዶ ጫሞ ካምፓስ አካባቢ በሚገኘው አንድ የምርጫ ጣቢያ ድምፁን እንደሚሰጥ ለሪፖርተር ተናግሮ ነበር፡፡
በማግሥቱ እሑድ ጠዋት ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ሪፖርተር በሁለቱ የአርባ ምንጭ ከተሞች ሲቀላ ቀበሌ 05 መሀል ከተማ ነጭ ሳር በተባለ አካባቢ የሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎችን፣ በሴቻ ከተማ ውስጥ ከኮይሳ ቀበሌ እስከ ጫሞ ካምፓስ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ አራት የምርጫ ጣቢያዎች ባደረገው ዳሰሳ፣ የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎች፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቅረባቸውን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ ሁኔታውን በማስመልከት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡና በኮይሳ ቀበሌ የሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ እንዳሉት ከሆነ፣ እሳቸው የሚያስተባብሩትን የምርጫ ጣቢያ ጨምሮ በአብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አብዛኛውን የምርጫ ቁሳቁስ አግኝተዋል፡፡
ሆኖም፣ በሁለቱም ከተሞችና በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት፣ በአብዛኛው የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የሆነውን የስንዴ ነዶ የሚያሳዩ ባነሮችና ወረቀቶች በመንገድ ዳር በሚገኙ አጥሮችና የመብራት ፖሎች ላይ በብቸኝነት ተለጥፈው ለማየት ችሏል፡፡ ሁኔታውን በማስመልከት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጫ ቦርድ ምክር ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አንጁሎ፣ ለሁሉም ፓርቲዎች ከፅሞና ቀን አስቀድሞ ዓርማዎችና ምልክቶቻቸውን እንዲያነሱ መመርያ መስጠታቸውንና በጽሑፍም ማሳወቃቸውን ገልጸው፣ ሆኖም እስካሁን ድረስ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ድረስ የብልፅግና ፓርቲ ምልክቶች ተሰቅለው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ አብርሃም በመቀጠል፣ የትኛውም ምልክት ከቅስቀሳ ጊዜ ማብቃት በኋላና በፅሞና ቀናት መታየት የለበትም ብለዋል፡፡ ‹‹የፅሞና ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሰቀሉትን እንዲያነሱ ተነግሯቸው አብዛኞቹ ሲያነሱ፣ ብልፅግና እስካሁን ግዴታውን አልተወጣም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የወቅቱ መሪ ፓርቲ ብቻ መሆኑ ሳይሆን በርካታ ዓርማዎችና ምልክቶችን በመለጠፉ አንስቶ ለመጨረስ ጊዜ ስለሚወስድበት ሊሆን ይችላል፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
From The Reporter Magazine
አቶ አብርሃም ከምርጫው በፊት ስለተደረጉት ዝግጅቶች ሲናገሩ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከምርጫ ቦርድ በተዋረድ የሚወርዱ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ፣ የምርጫ ማዕከላትንና ጣቢያዎችን ለአሠራር አመቺና አካታች (Inclusive) በማድረግ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በዚህም ዜጎች ምቹ በሆነ ሁኔታ ድምፅ መስጠት የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል። ‹‹አካታች በሆነ መንገድ ማለት አካል ጉዳተኞችንና ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ ለቦታው ምቹ የሆኑ የምርጫ ጣቢያዎችን የመምረጥና የማስተካከል (Rearrange) ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ ከዚያ በተረፈ ደግሞ ማንኛውም ሰው ወጥቶ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት መመዝገብ እንዳለበትና በምዝገባው ወቅትም ሁሉም ዜጋ መብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም የሚያስችል የመራጮች ትምህርት በሰፊው ተሰጥቷል፤›› ብለዋል። አቶ አብርሃም አክለውም፣ በምርጫው ቀን ኅብረተሰቡ የራሱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ያለ ምንም ተፅዕኖ ድምፁን መስጠት እንዲችል በተለያዩ አካላት፣ ማለትም በሲቪክ ማኅበራት፣ በበጎ ፈቃደኞች፣ ምርጫ ቦርድ ባደራጃቸው የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም ፈቃድ ባገኙ የወጣቶች ፌዴሬሽንና የመምህራን ማኅበራት አማካይነት የመራጮች ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱንና ከእነዚህ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ 56 የምርጫ ክልሎችና 3,941 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ድምፃቸውን ለመስጠት ወደ 3.4 ሚሊዮን ገደማ መራጮች ተመዝግበዋል። በክልሉ ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 18 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀጣዩ ምርጫ እንደሚሳተፉ የገለጹት የክልሉ ምርጫ ቦርድ ማዕከል ኃላፊ አቶ አብርሃም፣ አራት ፓርቲዎች ክልላዊ ውክልና ይዘው እንደሚወዳደሩና የተቀሩት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አስቀድሞ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሰኞ ጠዋት ከሌሊቱ 12፡00 ሰዓት የሚጀመረውን የ2018 ዓ.ም. 7ኛውን አገራዊ ምርጫ ለመዘገብ፣ ሪፖርተር ከንጋቱ 11፡30 ጀምሮ በተመረጡ የምርጫ ጣቢያዎች ለመድረስ ጉዞውን ጀመረ። በመጠኑ አነስተኛ በሆነ ነፋሻማ አየር ንብረት ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ቢጠብቅም፣ ከደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለባቸውን ባለሁለትና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን (ባጃጆችን) ማግኘት አልቻለም። ሆኖም ከደንብ አስከባሪዎች ዕይታ ውጭ በነበረች አንድ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሞተር ብስክሌት) በመታገዝ ሴቻ ከተማ በሚገኘው ጫሞ ቀበሌ ቀጣና ባይራ ምርጫ ጣቢያ ደረሰ። ሪፖርተር ይህንን ጣቢያ የመጀመሪያ መዳረሻው ያደረገው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ ከመሆኑም በላይ የትውልድ አካባቢያቸው በመሆኑ ነው።
From The Reporter Magazine
ምንም እንኳን የምርጫው ሰዓት ከመድረሱ በፊት በቦታው የተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ መራጮች በሠልፍ ሆነው የምርጫውን መጀመር ቢጠባበቁም፣ ከንጋቱ በ12፡01 ሰዓት የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ በወቅቱ ለነበሩት የፓርቲ ተወካዮች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና የብዙኃን መገናኛ አባላት ገለጻ ካደረጉ በኋላ፣ አሠራሩ በሚያዘው መሠረት ቃለ ጉባዔ ተይዞ ምርጫውን ለመጀመር ስምምነት ላይ ተደረሰ። በዚህም መሠረት የምርጫ ኮሮጆዎች ተከፍተው በአንዷ የአርባምንጭ ከተማ ሴቻ በጫሞ ቀበሌ ቀጣና ባይራ ምርጫ ጣቢያ 7ኛው አገራዊ ምርጫ ተጀመረ። ወደ 1,283 መራጮች በተመዘገቡበት በዚህ የምርጫ ጣቢያ፣ ከተወዳዳሪው የብልፅግና ፓርቲ ተወካዮች በስተቀር የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ሳይገኙ ምርጫው የተጀመረ ቢሆንም፣ ሒደቱ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመቀጠል ከወጣት እስከ አዛውንት ያሉ የምርጫ ካርድ የያዙ ድምፅ ሰጪዎችን ማስተናገድ ቀጥሏል። የምርጫ ሒደቱ ያለምንም መስተጓጎል በቀጠለበት ወቅት፣ በግምት ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ገደማ ለአካባቢው እንግዳ ያልሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎና ሌሎች አራት የሚሆኑ የክልሉ፣ እንዲሁም የከተማው ከፍተኛ አመራሮች ወደ ምርጫ ጣቢያው ደረሱ።
ብልፅግና ፓርቲን ወክለው በክልሉ የሚወዳደሩት አቶ ታገሰ ጫፎ ቅድሚያውን ይዘው ድምፅ የመስጠት ሒደታቸውን አከናውነዋል። እሳቸውን በመከተል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና ሌሎቹም ባለሥልጣናት ድምፃቸውን በየተራ የሰጡ ሲሆን፣ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ምርጫ ጣቢያውን ለቀው ወጥተዋል። በመቀጠልም ተራውን እየተጠባበቀ የነበረው ድምፅ ሰጪ እንደ አመጣጡ መስተናገድ ጀመረ። ሪፖርተርም የጫሞ ቀበሌ ቀጣና ባይራ ምርጫ ጣቢያን ሰላማዊ ሒደት ተከታትሎ፣ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የሴቻ ኮንዶሚኒየም በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ ያለውን ሒደት ለመዘገብ አመራ። በዚህም ጣቢያ የምርጫ ሒደቱ ፍፁም ሰላማዊ ሲሆን፣ በአብዛኛው በዕድሜ ከፍ ያሉና ቁጥራቸው እስከ 250 የሚገመቱ ዜጎች ድምፅ መስጠት ጀምረዋል። ንጋት 12፡00 ሰዓት ላይ ታዛቢዎችና ምርጫ አስፈጻሚዎች በተገኙበት ምርጫው መጀመሩን የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚና ኃላፊ አቶ ያቤፅ ተሰማ ገልጸዋል። እንደ ምርጫ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ ምርጫው የተጀመረው ሁሉም አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተውለት ሲሆን፣ የብልፅግናና የኢዜማ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ከምርጫ ክልሉ የመጡ ታዛቢዎችም የምርጫውን ሒደት በቅርበት ተከታትለዋል።
የሪፖርተር ቀጣዩ መዳረሻ የኮይሳ መሠረተ ክርስቶስ ምርጫ ጣቢያ ሲሆን፣ በሥፍራው ሲደርስ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሆኖ ነበር። ለምርጫው ከተዘረጋው ረዘም ያለ ድንኳን ውጪ በአብዛኛው በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችና ወንዶች፣ እንዲሁም አዛውንቶች በጠቅላላው ከ200 እስከ 250 የሚደርሱ መራጮች ተሠልፈው ነበር። ለፀጥታ ጥበቃ ሲባል በአንድ የክልሉ ፖሊስ አባል በሚጠበቀው በዚህ የምርጫ ጣቢያ፣ የምርጫ ደንቡ በሚያዘው መሠረት ልክ በ12፡00 ሰዓት ላይ ሒደቱ መጀመሩን የጣቢያው ምርጫ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ጮዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ኃላፊው አክለውም ለመራጮች አስፈላጊው ገለጻ (Orientation) መሰጠቱንና ምርጫው የተጀመረው በአንድ የብልፅግና ፓርቲ ተወካይና በአንድ የወጣቶችና ሴቶች ፌዴሬሽን ታዛቢ ፊት መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹እኛ እነሱ ይገኛሉ ብለን በመጠበቅ ከሕግ ውጪ መሆን የለብንም፡፡ ተገኙም አልተገኙም እኛ በሰዓታችን ምርጫውን ጀምረናል፤›› ብለዋል አቶ ታሪኩ። ኃላፊው በመቀጠል 1,214 መራጮች ድምፅ ለመስጠት በተመዘገቡበት በዚህ የምርጫ ጣቢያ ሒደቱ ሰላማዊና የምርጫ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ የተሟሉለት መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም እሳቸው በሚመሩት ጣቢያ የትኛው ተፎካካሪ ፓርቲ እንደሚወዳደር እንደማያውቁና የተወዳዳሪዎችን ስምና ፎቶግራፍ ለመራጮች ይፋ አድርጉ የሚል መመርያ እንዳልደረሳቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል። የሴቶች ፌዴሬሽንን ወክለው በጣቢያው የተገኙት ወ/ሮ ዝናቧ ዋሴ በበኩላቸው፣ ምርጫው ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊውን ታዛቢነት (Observation) ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ሒደቱ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እየቀጠለ መሆኑንና በሥፍራው ሌሎች ታዛቢዎችና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ባለመገኘታቸው ግራ መጋባታቸውን ጠቁመዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች በየምርጫ ጣቢያው አለመኖራቸውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ምርጫ ቦርድ ማዕከል ኃላፊ አቶ አብርሃም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 18 ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩና ከእነሱም ውስጥ የ15ቱ ተወካዮች በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በርካታ ተወዳዳሪዎችን ስላቀረበ፣ ብዙ ታዛቢዎችን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች መድቧል ብለዋል። ‹‹የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች በየምርጫ ጣቢያው እንዲገኙ አስቀድሞ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ምናልባትም በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ያልተገኙት ተንቀሳቃሽ ስለሆኑና እየወጡ ስለሚነጋገሩ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ተገኙም አልተገኙም ኃላፊነቱን የሚወስዱት ራሳቸው ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል። አቶ አብርሃም ኃላፊነቱን ለተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ቢሰጡም፣ ሪፖርተር በሁለቱ ከተሞች ባሉ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ባደረገው ቅኝት፣ ከሁለቱ በስተቀር ማለትም በሴቻ ኮንዶሚኒየም በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ የኢዜማ ተወካይ፣ እንዲሁም በሲቀላ ዋርካ ቀበሌ 04 ምርጫ ጣቢያ አንድ የኅብር ፓርቲ ተወካይና ተወዳዳሪ ብቻ የምርጫ ሒደቱን ሲታዘቡ ተመልክቷል።
ሪፖርተር ዳሰሳ ባደረገባቸውና በሲቀላ ከተማ በሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ያለው ሁኔታ ከሴቻ ከተማ ጋር ተቀራራቢ ነበር። በሁለቱም ጣቢያዎች፣ ማለትም በዋርካ ቀበሌ 04 ምርጫ ጣቢያና በአቅራቢያው በሚገኘው መሀል ከተማ ገብርኤል ጀርባ በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ፣ አብዛኛው በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ መራጭ ተራው እስኪደርስ እየተጠባበቀ ነበር። ይህንን አካባቢ ከሴቻ ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ ሙቀትና ፀሐያማ የአየር ንብረት የበረታበት መሆኑ ሲሆን፣ ይህም ዕድሜያቸው ገፋ ላሉ መራጮች ቆይታውን አድካሚ አድርጎታል። ወይዘሪት ሃያት መሐመድ የመሀል ከተማ ገብርኤል ጀርባ በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ስትሆን፣ እሷ በምትመራው የምርጫ ጣቢያ 823 መራጮች መመዝገባቸውን ጠቅሳለች። ሆኖም የምርጫው ሒደት በፈለገችው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጻ፣ ከብልፅግና ፓርቲ ከተወከሉ ታዛቢዎች ውጪ ሌሎች ተወካዮች አለመኖራቸውን ተናግራለች። በኅብር ኢትዮጵያና በብልፅግና ፓርቲዎች ታዛቢነት ምርጫ በተጀመረበት በዋርካ ቀበሌ 04 ምርጫ ጣቢያ በዋና ኃላፊነት የምትመራው ፅዮን አድማሱ በበኩሏ፣ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልጻ፣ የመራጮች ቁጥር መብዛት ግን ሒደቱ ፈጣን እንዳይሆን ማድረጉን አስረድታለች።
እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ይጠናቀቃል ተብሎ በምርጫ ቦርድ ዕቅድ የተያዘለት 7ኛው አገራዊ ምርጫ፣ በመራጮች ቁጥር መብዛትና በአንዳንድ ባልተገለጹ ምክንያቶች መጀመሪያ እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት፣ በኋላም እስከ እኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት መራዘሙን ከሁለቱም ከተሞች ከሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሪፖርተር ሰምቷል። ይሁን እንጂ የምርጫው ሰዓት በመራጮች ቁጥር መብዛትና ከከተማ ውጪ በተፈጠሩ አነስተኛ ችግሮች ምክንያት ሊራዘም እንደሚችል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጫ ቦርድ ማዕከል ኃላፊ አቶ አብርሃም አስቀድመው ለሪፖርተር ጠቁመው ነበር። ሁኔታውን ለመታዘብ ሪፖርተር በሲቀላ አካባቢ የሚገኙ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎችን፣ ማለትም የዋርካ ቀበሌ 04 ምርጫ ጣቢያንና በአቅራቢያው የሚገኘውን መሀል ከተማ ገብርኤል ጀርባ በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያን በድጋሚ የጎበኘ ሲሆን፣ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ድምፅ ሰጪዎች ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን መመልከት ችሏል። ስለሁኔታው የተጠየቀ አንድ ወጣት የምርጫው ሰዓት መራዘሙን በመስማቱ መደሰቱን ገልጾ፣ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በጣቢያው ቢደርስም እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ተራ እንዳልደረሰውና ሆኖም ድምፁን ሳይሰጥ ወደ ቤቱ እንደማይመለስ ለሪፖርተር ተናግሯል። በተመሳሳይ በአካባቢው ቡናና ሻይ በመሸጥ የምትተዳደር አንዲት ወጣት የምርጫ ሰዓት መራዘሙ ለሥራዋ ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን በመግለጽ፣ የተራዘመው የምርጫው ሰዓት ከመጠናቀቁ በፊት ድምጿን እንደምትሰጥ ተናግራ ነበር፡፡
