- ጥናቱ እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2023 ድረስ 207.7 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን ያሳያል
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ያደረጉት ጥናት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በንግድ ማጭበርበርና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት እንደምታጣ አመላከተ፡፡
የሁለቱ ተቋማት ተመራማሪዎች በጋራ ያቀረቡትና ውይይት የተደረገበት ጥናት ከ2008 እስከ 2023 በአጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2025 ደግሞ የተመረጡ አስመጪዎች፣ ላኪዎችና አምራቾች በንግድ ማጭበርበር ላይ በማተኮር የተሠራ ነው ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2013 በነበሩት ዓመታት 207.7 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ማጭበርበር መፈጸሙን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ በአማካይ በየዓመቱ 12.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ማጭበርበር እንደተፈጸመ ያስረዳል፡፡ ይህም በዋነኝነት በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በደካማ የንግድ ሥርዓት፣ በአገር ውስጥ የሀብት አሰባሰብ ሥርዓት መበላሸት ምክንያት የተፈጠረ ነው የሚለው ጥናቱ፣ ከ85 በመቶ በላይ ለሚሆነው የንግድ ማጭበርበር ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦችን ዋጋ በማናር (Over Invoicing) ከ113.8 ቢሊዮን እስከ 119 ቢሊዮን ዶላር ሳይጠፋ እንዳልቀረ የሚያስረዳው ጥናቱ፣ የሸቀጦችን ዋጋ ማናር ወደ ውጭ የሚደረገውን የካፒታል ፍሰት ማፋጠኑን ያስረዳል፡፡
ዋጋቸው እንዲንር ከተደረጉት ገቢ ሸቀጦች መካከል ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ የምግብ ሸቀጦችና ከባድ ማሽነሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡ አብዛኞቹ ግዥዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት የተፈጸመ ነው የሚለው ጥናቱ፣ ለገቢና ለወጪ ንግድ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥርዓት አለመኖርን ያክላል፡፡
በሌላ በኩል በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከዋጋ በታች በመተመን (Under Invoicing) 25 ቢሊዮን ዶላር መታጣቱን የሚያብራራው ጥናቱ፣ ይህ ዓይነቱ የዋጋ ግምት ላኪዎች ከኤክስፖርት ምርቶች የተገኘን የውጭ ምንዛሪ በውጭ አገሮች እንዲያስቀምጡ ረድቷቸዋል ይላል፡፡ በወጪ ንግድ ዋጋን አሳንሶ የመግለጽ ድርጊት አገሪቱ ወደ ውጭ በዋነኝነት በምትልካቸው በቡናና በአበባ ምርቶች ላይ ያመዘነ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ከተሰማሩ ተዋንያን መካካል 57.9 በመቶ አስመጪዎችና 63.7 በመቶ ላኪዎች ትክክለኛ የንግድ መረጃ ባለመስጠት የማጭበርበር ተግባር እንደሚፈጽሙ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ የገቢ ንግድ ዋጋ አሳንሶ ማቅረብ በዋነኝነት በእስያ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ መዳረሻ አገሮች ጋር ካሉ የንግድ አጋሮች በሚደረገው ግንኙነት ያመዘነ እንደነበርም ያመለክታል፡፡
From The Reporter Magazine
በተጠቀሱት 16 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ታገኝ የነበረውን 11.1 ቢሊዮን ዶላር የታክስ ገቢ ማጣቷን የሚገልጸው ጥናቱ፣ ይህም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በካፒታል ሸቀጦች፣ እንዲሁም በከባድ ማሽነሪዎች ላይ መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ በንግድ ማጭበርበር ምክንያት የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር መቀጠሉን የሚያስረዳው ጥናቱ፣ ይህም በተለይ በንግድ አስተዳደር፣ በጉምሩክ አስተዳደርና በውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መዋቅራዊ ድክመት ምክንያት ነው ይላል፡፡ ጥናቱ የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ ደካማ የቁጥጥር ሥርዓትና ፍትሐዊ ያልሆነ የቅሬታ አፈታትን በምክንያትነት አቅርቧል፡፡
ጥናቱ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2023 በነበሩት ጊዜያት የወጪ ንግድ ዋጋን አሳንሶ በማቅረብና የገቢ ንግድን ዋጋ አጋኖ በማቅረብ ምክንያት፣ ከአገሪቱ በየዓመቱ የሚሰጠው ገንዘብ ቢያንስ ከ4.2 ቢሊዮን እስከ 6.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ያስረዳል፡፡
From The Reporter Magazine
የንግድ ማጭበርበር ድርጊት መጠነ ሰፊ የጉምሩክ ሕግ፣ የታክስ ሥርዓት፣ እንዲሁም የፋይናንስ አስተዳደሩን ማስተካከል እንደሚጠይቅ ያብራራል፡፡
መንግሥት ለዚህ ዓይነቱ የንግድ ሥርዓት ሊጋለጡ የሚችሉ ምርቶችን መለየት፣ ዓለም አቀፍ ትብብር ማሳደግ፣ የንግድ ማበረታቻን ከወጪ ንግድ ፖሊሲ አፈጻጸጸም ጋር ማቀናጀትና መተግበር፣ በዲጂታል ሥርዓት ላይ ኢንቨስት ማድረግና የመሳሰሉ ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡