የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአራት ሺሕ በላይ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት፣ ከ22 ቀናት እስከ አንድ ወር የሚቆይ ጉባዔ፣ ከዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ይጀመራል ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ታሪካዊ በሆነው በአገራዊ ምክክር ጉባዔ ለመሳተፍ ሲመጡ፣ የወከሉትን ማኅበረሰብ ድምፅና ምኞት ለማስተጋባት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር የጋራ ዕድልና የወደፊት ዕጣ ፈንታ መሠረት ለመጣል ጭምር በመሆኑ፣ ትከሻቸው ላይ የወደቀው ኃላፊነት ታላቅና ጥልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹በምክራችሁ የምትደርሱባቸው ውሳኔዎች፣ የምትፈጥሩት መግባባት፣ የምታፀኑት ስምምነት ከዚህ የታሪክ ወቅት ባለፈ ዘልቆ የሚቀጥልና ለሰላማዊት፣ ለዴሞክራሲያዊትና ለተግባባች ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥል ነው፤›› ብለዋል።
‹‹ምክክራችሁ በጥበብ፣ በጋራ መከባበርና ለሕዝብ ጥቅም ባላችሁ ፅኑ ቁርጠኝነት እንዲመራ፣ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ብሩህ ነገን የሚያሰናዳ እንዲሆን እመኛለሁ፤›› ሲሉም ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር)፣ በበኩላቸው የአገራዊ ምክክር ጉባዔው ለኢትዮጵያ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን በመመካከር ለአገራቸው ትልቅ ሥራ የሚሠሩበት መሆኑን አስረድተዋል።
አገራዊ የምክክር ጉባዔው የኢትዮጵያውን መድረክ መሆኑን፣ በዚህም ተመካካሪዎች የሚፈልጓት አገር እንድትሠራላቸው ሁሉም በእኩልነት ድምፃቸውን ማሰማት እንዳለባቸውና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ አጎ ደግሞ፣ በአገራዊ ምክክር ጉባዔው የተመረጡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ታዛቢዎች እንዲኖሩ የሚያስችል መመርያ በኮሚሽኑ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ መፅደቁን ለሪፖርተር ገልጸዋል። በጉባዔው ሕጋዊ ሰውነት ካላቸው የአገር ውስጥ ተቋማት፣ የአገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መሠረት ያደረገ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ አገሮችና ድርጅቶች የታዛቢነት ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የታዛቢነት ተሳትፎ ፈቃድ አሰጣጡ የአገርን ሉዓላዊነት ከግምት ያስገባና ጥንቃቄ የተደረገበት እንደሆነ አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኮሚሽኑ ጥሪ የሚቀርብላቸው ግለሰቦች የሚሳተፉበት ዕድል በመመርያው መካተቱን ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
በአራት ዓመታት የኮሚሽኑ ጉዞ ለዚህ ጉባዔ ከተመረጡ ተመካካሪዎች በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙት ለማሻሻል መተማመን የሰፈነባትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር የአገራዊ ምክክሩ ቀዳሚው ዓላማ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዜጎች፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዴምክራሲያዊ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ማዳበር፣ ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንንገድ ተፈትተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካና የማኅበራዊ መደላድል ማመቻቸት፣ ጠንካራ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት ፅኑ መሠረት መጣል፣ የአግራዊ ምክክሩ ሌሎች ዓላማዎችና ተጠባቂ ውጤቶች መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
From The Reporter Magazine
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ አገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚደረግባቸውን ስምንት ዋና ዋናና ንዑስ አጀንዳዎች ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህም የአገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርፅ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና፣ የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ ታሪካዊ ቅሬታዎችና ዕርቅን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ የሰብዓዊ መብቶች፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ጉዳዮች፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ሙስናና መልካም አስተዳደር፣ በተጨማሪም የሰላም ግንባታ በአገራዊ ጉባዔው ምክክር የሚደረግባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ሲሆኑ፣ በውስጣቸው ዝርዝር ንዑስ አጀንዳዎች ተካተውባቸዋል።