- ሥራ ሲጀምር ከነበረው 50 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ከግማሽ በላይ መቀነሱን ገለጸ
በመንግሥትና በግል ዘርፍ ትብብር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር፣ ባለፉት አሥር ዓመታት በፀጥታ ችግር ምክንያት ለደረሰ ጉዳት የከፈለውን ጨምሮ፣ 5.2 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የተቋቋመበትን አሥረኛ ዓመት በማስመልከት፣ ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ነው ይህንን ያስታወቀው፡፡
መንግሥታዊ የሆኑት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአክሲዮን ማኅበሩ 41 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዳላቸው፣ ቀሪው 59 በመቶ በግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተያዘ መሆኑን መግለጫውን የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ነፃነት ለሜሳ ገልጸዋል፡፡
የንብረትና የሕይወት የጠለፋ መድን እንዲሰጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቶት በ2008 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው አክሲዮን ማኅበሩ፣ በአሁኑ ወቅት ለ18 የአገር ውስጥና ለ21 የውጭ በድምሩ ለ39 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፣ ከ15 ዓለም አቀፍ ኢንሹራንስ ደላሎች (Brokers) ጋር አብሮ እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡
በየዓመቱ 300 የሚጠጉ የጠለፋ መድን ኮንትራቶችን በመዋዋልና በማደስ እያስተናገደ እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህ ቁጥር ታላቁን የህዳሴ ግድብና አዲስ እየተገነባ ያለውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት መሰል ትልልቅና በአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚሸከሙት አቅም በላይ በመሆናቸው፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በማነጋገር ሽፋን እንዲሰጡ የሚደረገውን ሳይጨምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ ሥራ ሲጀምር የተከፈለ ካፒታሉ 500 ሚሊዮን ብር እንደነበር፣ አሁን ወደ አምስት እጥፍ በማሳደግ 2.4 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉንና የጠለፋ ዋስትና በአብዛኛው በውጭ የጠለፋ ድርጅት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ለዚህም ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለሚሰጧቸው ሽፋኖች ሁሉ አክሲዮን ማኅበሩ የጠለፋ መድን ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ነፃነት፣ እነዚህም የሕይወት፣ የንብረት፣ የግብርና፣ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት፣ የአየር ትራንስፖርትና የባህር ላይ ጉዞ ሽፋን መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ለሚደርሱ የንብረት ጉዳቶችም ሽፋን ሲሰጥ መቆየቱን አክለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የውጭ ምንዛሪው ገበያ መር ከሆነ በኋላ የአክሲዮን ማኅበሩ ካፒታል መቀነሱን ገልጸው፣ ሥራ ሲጀምር በውጭ ምንዛሪ የነበረው ካፒታል 50 ሚሊዮን እነደነበርና በብር የሚታሰበው ካፒታሉ 2.4 ቢሊዮን ብር በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ግን 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ከሌሎች የውጭ ኢንቨስተሮች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንና ፍላጎቶችም መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የስትራቴጂና ቢዝነስ ዕድገት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ ባለፉት አሥር ዓመታት ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የጠለፋ አክሲዮን ለረዥም ዓመታት በአገሪቱ ያልነበረ፣ ነገር ግን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ መንግሥት ከግል ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራት ውጤታማ መሆን እንደሚችል ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
በዓለም አቀፍ ግምት ሰጪ ተቋማት ድርጅቱ አሁን ያለበት ደረጃ ‹‹ቢ ስትሮንግ›› መሆኑንና ይህንን የማሻሻል ዕቅድ በመያዝ እየተሠራ እንደሆነ፣ በተለይም በተለያዩ አገሮች ገብቶ ለመሥራት ይህንን ደረጃ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የመጀመሪያውን አምስት ዓመታት ትኩረት አድርገን ስንሠራ የነበረው አገር ውስጥ ነው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በመግባት መሥራት የጀመርነው ከሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ዓመት በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህም አምስት በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑንና ከተከፈለው 5.2 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ውስጥ ከአገር ውጪ ላለው የተከፈለው አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ለዚህም ምክንያት በሌሎች አገሮች የሚጻፈው ውል በጥንቃቄ ስለሚታይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ማኅበሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 አገሮች እንደሚሠራ ገልጸው፣ ‹‹በአገራችን ውስጥ ያለው ኢንሹራንስ ጥሩ የሚባል ሥጋት በመሆኑ፣ እዚህ ያገኘነውን ትርፍ ያላግባብ አውጥተን መስጠት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
የ2018 ዓ.ም. ዓረቦን ገቢ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ነገር ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚልኩትን ሪፖርት በመመልከት ትክክለኛ ገቢው እንደሚታወቅ ገልጸዋል፡፡