የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ25 ዓመታት በኋላ የአዲስ አበባና ሸገር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት፣ 2.81 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ በጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለመሸከምና የአገሪቱን የኃይል ማስተላለፍ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ አሠራር ለማሸጋገር ያስችላል ያለውን የ25 ዓመታት አገር አቀፍ የኃይል ማስተላለፍ ሥርዓት ማሻሻያና ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ጥናት፣ ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
አዲስ አበባና ሸገር ከተሞች ከሌሎች አካባቢዎች አኳያ ፈጣን የከተማ ዕድገት፣ የኤሌክትሪክ ፍላጎት መጨመርና የበርካታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመለዋወጫ አቅም ውስንነት እንዳለባቸው፣ በዚህም ምክንያት የረዥም ጊዜ የሰብስቴሽን ግንባታ ዕቅድ ማስፈለጉን የጥናቱ ግኝት ያመላክታል ብሏል፡፡
ለሁለቱ ከተሞች እ.ኤ.አ. እስከ 2049 በነባር ሰብስቴሽኖች ላይ 54 የተለያየ አቅም ያላቸው አዳዲስ የኃይል ትራንስፎርመሮችን ማስቀመጥ፣ ለ13 ትራንስፎርመሮች ደግሞ አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን ገልጿል፡፡ የኃይል ፍላጎቱን ለማሟላት በአጠቃላይ 207 ሰብስቴሽኖች ሊኖሩ እንደሚገባ የሚጠቁመው ጥናት፣ ይህን ለማሳካትም 2.81 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እንደተከናወነ የተገለጸው ጥናቱ፣ ሞኔንኮ ኢራን ኢንጂነሪንግ ኮንሰልቲንግ በተሰኘ የኢራን አማካሪ ድርጅት መጠናቱ ተገልጿል፡፡
የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የኔትወርክ ማሻሻያ፣ ማስፋፊያና የዲጂታል ኢንቨስትመንት ፍላጎቶች መኖራቸው በጥናቱ ግኝት ተካቷል፡፡
በጥናቱ ከታዩ 1‚100 መጋቢ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መካከል 271 የሚሆኑት የቮልቴጅ መጠናቸው ያልተመጣጠነ እንደሆነ፣ 182 ያህሉ ደግሞ የኃይል ጭነት የበዛባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
From The Reporter Magazine
በማሠራጫ መስመሮች ላይ በተደረገ ፍተሻ 6‚800 ትራንስፈርመሮች፣ 15‚800 የመካከለኛ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ 6‚833 በአየር ላይ የተዘረጉ መስመሮችና 638 መካከለኛ መስመር መቆጣጠሪያዎች የማስተካከያ ግኝት እንደተገኘባቸው ጥናቱ አካቷል፡፡ ማስተካከያውን ለማድረግ 71 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
በአገሪቱ ካሉ ጠቅላላ ሰብስቴሽኖች በተጨማሪ እ.ኤ.አ. እስከ 2049 ድረስ 128 ተጨማሪ ሰብስቴሽኖች መገንባት እንደሚኖርባቸው የሚገልጸው ጥናቱ፣ ግንባታውና ተያያዥ ሥራዎች 16.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠይቁ ይጠቁማል፡፡
በጥናቱ የተካተተው ሌላው ሥራ አሁን ያለውንና ዘመኑን ያልዋጀ ነው የተባለውን ኔትወርክ ማዘመን ሲሆን፣ ለዚህ ይረዳል በሚል የተዘጋጀው ስትራቴጂ ኔትወርኩን ተወዳዳሪ፣ ዘመናዊና ደንበኛ ተኮር ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ ከ516 እስከ 640 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተካቷል፡፡
From The Reporter Magazine
በነባር የኔትወርክ ዳሰሳ ወቅት ከተለዩ ችግሮች በመነሳት በአጭር ጊዜ ዕቅድ ይከናወናሉ ተብለው የተለዩ ሥራዎች መኖራቸውን፣ ለሥራዎቹም 1.33 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡
በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ 16‚511 ኪሎ ሜትር አዲስ መካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ 9‚676 ኪሎ ሜትር የነባር መስመር መልሶ ግንባታ፣ 10‚603 የተለያየ አቅም ያላቸው አዳዲስ ትራንስፎርመሮችን ማስቀመጥና ለ11‚174 ነባር ትራንስፎርመሮች አቅም ማሳደጊያ ሥራዎች ተካተዋል፡፡
በጥናቱ የተካተቱትን ሁሉንም ሥራዎች ሠርቶ ለማጠናቀቅ 30.65 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
ጥናቱ ከ25 ዓመታት በኋላ በአገሪቱ የሚኖረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያካተተ ሲሆን፣ ጠቅላላ ፍላጎቱ 39‚327 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡
በአገሪቱ የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ የከተሞችና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በከፍተኛ መጠን የሚያሳድግ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢንጂነር) ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከ25 ዓመታት በኋላ የአገሪቱ ጠቅላላ የኃይል ፍላጎት የሚደርስበት መጠን ከፍተኛ መሆኑን፣ ይህም በአዲስ አበባ ብቻ የሚከሰት ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሚፈጠሩ አዳዲስ ከተሞች፣ የነባር ከተሞች መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪዎች ዕድገትና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመር የሚጠይቀውን ፍላጎት በተናጠል ፕሮጀክት ወይም በዓመታዊ በጀት ብቻ ለማሟላት እንደሚያስቸግር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የረዥም ጊዜ ዕቅድ፣ ትክክለኛ መረጃና የተቀናጀ ኢንቨሰትመንት፣ እንዲሁም ጠንካራ አጋርነት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡