የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ዜጎች የሚሰጥ የአሥር ሺሕ ዶላር ቪዛ ከመጪው ዓመት ጀምሮ እንደሚሰጥ ገለጸ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ የውጭ ዜጎች የሚሆንና ለአሥር ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ያዘጋጀው ወርቃማ ቪዛ፣ በ2019 ዓ.ም. መጀመሪያ መስጠት እንደሚጀምርና ቪዛውን ማግኘት የሚፈልግ የውጭ አገር ኢንቨስተር አሥር ሺሕ ዶላር መክፈል እንደሚጠበቅበት፣ የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አምቦ መቃሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹አሥር ሺሕ ዶላር ሲባል ትልቅ ገንዘብ ይመስለናል፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን ከኢሚግሬሽን አሠራሮችና ቪዛው ለውጭ ኢንቨስተሮች ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሠራቸው የሚገኙ ሥራዎች አካል መሆኑን፣ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ አገር ውስጥ በመግባት የመኖሪያ ጊዜ ፈቃዳቸው የተጠናቀቀ የውጭ አገር ዜጎች ሲያቀርቧቸው የነበሩ ቅሬታዎችን የሚፈታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቪዛውን ማግኘት የሚችሉ ኢንቨስተሮች ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ሆኖም የአምስት ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ኖሯቸው የተሰማሩበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ሊያስገኝ የሚችል ከሆነ ቪዛውን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ ቪዛውን እንዲያቀርብ የፈቀደው ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን የሚገልጹት አቶ አምቦ፣ በአገልግሎቱ በኩል ተግባራዊ ለማድረግ የሚቀረው ደንቡን ለማስፈጸም የሚያስችሉ መመርያዎችን ማዘጋጀት መሆኑንና ይህም እየተጠናቀቀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ስለቪዛው ዓይነት ዝርዝር ድንጋጌዎች በማካተት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውና ደንብ ቁጥር 114/1997ን ለማሻሻል የወጣው የኢሚግሬሽን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 581/2018 ሲሆን፣ ወርቃማ ቪዛው ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለሚያደርግ የውጭ አገር ዜጋ የሚሰጥ የቪዛ ዓይነት መሆኑን ይገልጻል፡፡ በየአሥር ዓመቱ የሚታደስ የመመላለሻ ቪዛ መሆኑ በደንቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ዝርዝር አፈጻጸሙ በመመርያ የሚወሰን መሆኑ ተመላክቷል፡፡
From The Reporter Magazine
ደንቡ ካካተታቸው ሌሎች ድንጋጌዎች መካከል ቤት ለሚገዛ የውጭ አገር ዜጋ የሚሰጥ ቪዛን የሚመለከተው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነ የውጭ አገር ዜጋ የሚሰጥ መሆኑን ተደንግጓል፡፡ ይህም በየአምስት ዓመቱ የሚታደስ የብዙ ጊዜ መመላለሻ ቪዛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለጊዜያዊ የሥራ ልምምድ ለሚመጣ የውጭ አገር ዜጋ የሚሰጥ ተግባራዊ የልምምድ ቪዛ፣ ከአገር ለሚወጣ የውጭ አገር ዜጋ የሚሰጥ የመውጫ ቪዛን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችም በደንቡ ተካተዋል፡፡