በቆንጂት ተሾመ
በሐረር ከተማ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የቆየውን የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዕውን ለማድረግ፣ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ለግንባታ ማስጀመሪያ የሚሆን 780 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት አፀደቀ።
የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዳስታወቀው፣ ለፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚውል በጀት በክልሉ ምክር ቤት ፀድቋል። በጀቱ በዋናነት ለቦታ ካሳ ክፍያና ለመሬት ዝግጅት ሥራዎች እንደሚውል፣ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ ወጪ ዝርዝር እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት በራስ አቅም ለመገንባት ላቀደው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የቦታ መረጣ መካሄዱን፣ በዚህም መሠረት የግንባታው ቦታ በሐረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ ቂሌ ቀበሌ 03 ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ እንዲሆን መመረጡ ታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችና መላው የክልሉ ተወላጆች ንቁ ተሳትፎና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ግንባታው ከፍተኛ ገንዘብና ዕውቀት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በቀጣይ በሚዘጋጁ የተሳትፎ ጥሪዎች ላይ ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ተጠይቋል።
የሐረር ከተማ ከቀድሞ ጀምሮ በአጎራባች አገሮች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የምታደርግ መሆኗን የጠቆሙት የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳሚ አብዱልዋሴ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ለከተማዋ ገቢ ማደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ የሚታይባት መሆኗን ገልጸው፣ ኤርፖርቱ ሲጠናቀቅ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ፍሰት በእጅጉ እንደሚያሳድገው አስረድተዋል።
From The Reporter Magazine
ከተማዋ ከድሬዳዋ አቅራቢያ የምትገኝ መሆኗን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ‹‹የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ምን ያህል አስፈላጊ ነው?›› ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
‹‹መጠየቅ ካለበት እንዲያውም ለምን ይገነባል ሳይሆን ለምን ዘገየ ነው። አስፈላጊነቱ ፍፁም ስለማያጠራጥር እንደ ክልል ከተማነቷ፣ እንደ አንድ የአገሪቱ የንግድና የጉብኝት መዳረሻነቷም ጭምር አውሮፕላን ማረፊያው በጣም ያስፈልጋታል፤›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ በረራ ወደ ድሬዳዋ ኤርፖርት ከሚደርሱ ተጓዦች ውስጥ 45 በመቶ ያህሉ የሐረር ከተማ ሕዝብ እንደሆነና በመኪና ወደ ከተማዋ እንደሚጓዝ ጠቅሰው፣ ይህንን የነዋሪዎች ፍላጎት ለማሟላት ግንባታው መሠረታዊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
From The Reporter Magazine
በተጨማሪም ሐረር በዩኔስኮ የተመዘገበች የዓለም ቅርስ ከተማ መሆኗን፣ በቅርቡ አባል የምትሆንባቸው ትልልቅ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ፕላትፎርሞች የአውሮፕላን ማረፊያ መኖርን እንደ መሥፈርት እንደሚጠይቁ ተገልጿል።
በሆቴልና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች የሚሰማሩ ባለሀብቶችም የኤርፖርት መኖርን ቅድመ ሁኔታ እንደሚያደርጉ፣ በአጠቃላይ ለክልሉ ነዋሪዎችና ለጎብኝዎች የረጅም ጊዜ አማራጭ የትራንስፖርት ጥያቄ በመሆኑ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አስፈላጊነት መሠረታዊ መሆኑን ነው አቶ ሳሚ ያብራሩት።