– ኮሚሽኑ ተመካካሪዎች በሚያቀርቡት ሐሳብ እንዳይጠየቁ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባሰማራቸው ምሁራን፣ ስለ መንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ ስለ ፖለቲካ ውክልናና የምርጫ ሥርዓት አጀንዳዎችን በሚመለከት ለአገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓም ገለጻ ተደረገ።
በኢትዮጵያ በቀጣይ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር፣ሕጎችን ለማውጣትና አስተዳደራዊ ሥራዎችን ለመምራት ሥልጣን የሚዋቀርበት የመንግሥት ሥርዓት (System of Government) ለመምረጥ ስለቀረበው አጀንዳ ምሁራን ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻው ለቀጣይ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት አማራጮች ተብለው ፓርላሜንታዊ ፕሬዚዳንታዊና ድብልቅ (Semi Presidential System) በዋናነት ቀርበዋል።
ፓርላሜንታዊ ስርዓት ሕዝብ የሚመርጥበትና አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትር) የሚመሠርትበት ሥርዓት መሆኑ ተነግሯል።
ፕሬዚዳንታዊ ደግሞ፣ ፕሬዚዳንቱ የአገርና የሥራ አስፈፃሚ መሪ የሚሆንበት፣ በምርጫ ወቅትም ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በሕዝብ የሚመረጥበት ስርዓት መሆኑ ተብራርቷል። በዚህ ሥርዓት ሕግ አውጪውና ፕሬዚዳንቱ ተለያይተው የየራሳቸው ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
ድብለቅ ሥርዓት ደግሞ፣ ሥልጣን በፕሬዚዳንትና በጠቅላይ ሚኒስትር የሚከፋፈልበት ስርዓት መሆኑ ተመላክቷል። በዚህ ሥርዓት ፕሬዚዳንቱ የአገር መሪ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የመንግሥት (የካቢኔ) መሪ እንደሚሆን ተብራርቷል። በምርጫ ወቅት ፕሬዚዳንቱ በሕዝብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በአብዛኛው በፓርላማ የሚመረጡ ወይም በፕሬዚዳንቱ የሚሾምና በፓርላማ የሚፀድቅ መሆኑ ተብራርቷል።

መንግሥት (ካቢኔው) ለፕሬዚዳንቱም ሆነ ለፓርላማው ተጠያቂ እንደሚሆንም ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት
እየተከተለችው የምትገኘው ፓርላሜንታዊ ስርዓት ሲሆን፣ በአራጭነት የቀረቡት ፕሬዚዳንታዊና የሁለቱ ድብልቅ የመንግሥት ሥርዓቶች ጠቀሜታና ጉዳትን የተመለከተ ገለጻ በዝርዝር ለተመካካሪዎች መቅረቡን ሪፖርተር ተመልክቷል።
From The Reporter Magazine
ገለጻ የሰጡ ምሁራን፣ ተመካካሪዎች የትኛው የመንግሥት ሥርዓት ግልጽ የሥልጣን ክፍፍል አለው፣ አባገነን ሥርዓት እንዳይኖር ሊያደርግ የሚችለው የትኛው ስርዓት ነው የሚለውን ትኩረት አድርገው መመካከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው የሥልጣን ክፍፍል ምን መሆን አለበት? ለክልል ከተሰጠ ሥልጣን የትኛው ወደ ፌዴራል መመለስ አለበት? ለፌዴራል ብቻ የሆነ፣ ነገር ግን ለክልል መሰጠት ያለበት ሥልጣን አለ?” በሚለው ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲመካከሩበት ምሁራኖቹ አስገንዝበዋል።
ገለጻ ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል የፌዴራል ከተሞች(አዲስ አበባና ድሬዳዋ)ን የተመለከተ ሌላኛው ጉዳይ ነው። በዚህ አጀንዳ ውስጥ በተለይ የአዲስ አበባ አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል አራት ሞዴሎች ቀርበው ገለጻ ተደርጎባቸዋል።
From The Reporter Magazine
በዚህም አዲስ አበባ ከተማ ራስገዝ ከተማ (City State)፣ የፌዴራል መዋቀር አካል የሆነች ከተማ፣ ራሷን የቻለች ክልልና የኦሮሚያ ክልል አካል የሆነች ከተማ የሚሉ አራቱ ሞዴሎች ቀርበዋል።
ድሬዳዋ ከተማንም በሚመለከት፣ ራስገዝ ከተማ፣ የፌዴራል አካልና ራሷን የቻለች ክልል የሚሉ ሦስት ሞዴል አማራጮች ቀርበዋል። ተመካካሪዎችም ይጠቅማል ብለው በሚያስቡት አማራጭ በትኩረት እንዲመካከሩ ምሁራኑ በገለጻቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ለመገናኛ ብዙኃን በዕለቱ በሰጡት መግለጫ፣ በአገረ መንግሥት ግንባታ፣ በታሪክ፣ በማንነት፣ በፌዴራሊዝም፣በግጭት ምንነትና አፈታትና ሌሎች አጀንዳዎችን በተመለከተ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን፣ 500 ሆነው በስምንት ቡድኖች ለተዋቀሩ ተመካካሪዎች ሙያዊ ገለጻ ማቅረባቸውንና ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ከዛሬ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በንዑስ ቡድን ተከፋፍለው አሥር ሆነው ውይይት ያደረጉ ተመካካሪዎች ያጠናከሩትን ሐሳብ በ50 ለተዋቀሩት ቡድኖች እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ከዚያም 50 ዎቹ የቀረቡትን ሐሳቦች በሚገባ እንዲብላሉ ካደረጉ በኋላ ለሚቀጥለውና 250 ተመካካሪዎች ለሚኖሩበት ቡድኖች ሐሳባቸዉን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
50 ሆነው የተዋቀሩ ቡድኖች ሥራቸውን ከጨረሹ በኋላ፣ በ250 የተደለደሉ 16 ቡድኖች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ምክክር ማድረግ እንደሚጀምሩ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ተመካካሪዎች በጉባዔው በነጻነት ሐሳብን ማቅረብ እንዳለባቸው፣ ሆኖም በሚያቀርቡት ሐሳብ ሳቢያ ወደ መጡበት ሲመለሱ እንዲጠየቁ እንደማይፈቅድ፣ ይህ ከሆነም ኃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ኮሚሽኑ እንደሚወስድ ተናግረዋል።