የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ቅድመ ምርጫ ሒደት ላይ አካሄድኩት ባለው ክትትል ተፈጸሙ ያላቸውን ጥሰቶች ይፋ አደረገ፡፡
ጥቂት ሳምንታት በቀረው ምርጫ ላይ ኮሚሽኑ 55 የክትትል ቡድኖችን በማሰማራት አሰባሰብኩት ባለው መረጃ፣ የደረሰባቸውን ግኝቶቸ ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በምልከታው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በርካታ አካላትን በማካተት፣ ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ ሁኔታዎችን ያካተተ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በ150 ምርጫ ክልሎችና በ1,007 የምርጫ ጣቢያዎች ከዚህ ቀደም ተሠርቶ በማያውቅ መጠን ክተትል አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
በክትትሉ ውጤት መሠረት የበይነ መረብና የተንቀሳቃሽ ስልክ ኔትወርክ መቆራረጥ በሁሉም ክልሎች የተከሰተ በመሆኑ፣ በቴክኖሎጂ የተደረገውን የዕጩዎች ምዝገባ መስተጓጎሉን ገልጿል፡፡
በዕጩነት ለመመዝገብ የተመለመሉ አካል ጉዳተኛ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ አካል ጉዳታቸውን የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ ከመንግሥት የጤና ተቋማት በአጭር ጊዜ እንዲያመጡ መጠየቅ፣ ማስረጃውን ለማግኘትም በመቸገራቸው የተመራጭነት ተሳትፏቸው ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን አስረድቷል፡፡
ከምርጫ ጣቢያዎች መካከል ቦርዱ በጂፒኤስ የለያቸው አዳዲስ የተለዩ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ በመግለጹ፣ ኢሰመኮ በጂፒኤስ የተለዩ ጣቢያዎች ተደራሽ ናቸው የሚለውን ለማረጋገጥ ሲሞክር በተባሉበት አቅጣጫ ያልተገኙ ጣቢያዎች አግኝቻለሁ ብሏል፡፡
በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተሰጠው ነፃ የአየር ሰዓት የክርክር መድረክ ህዳጣን (Minority) የሚወክሉ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንዳልነበሩ ገልጿል፡፡ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በምልክት ቋንቋ ሲተላለፍ ስላልነበረ፣ ኢሰመኮ ምክረ ሐሳብ በመስጠቱ ምክንያት በምልክት ቋንቋ መተላለፍ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
From The Reporter Magazine
በሚዛን ከተማ ገዥውን የብልፅግና ፓርቲ የሚደግፉ ትዕይንቶች ላይ ዜጎች በግዳጅ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲደረግ እንደነበር፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስብሰባና ሰላማዊ ሠልፍ ለማካሄድ ብንፈልግም ተከልክለናል የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
በሕግ በተከለከሉ ቦታዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተደራጅተው አግኝቻለሁ ያለው ኮሚሽኑ፣ በአንድ ሥፍራ ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያ መገኘቱን፣ በፖሊስ ጣቢያ የተደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች፣ በመከላከያ ካምፕና በመጠጥ ቤት ግቢ ውስጥ የተደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የተለያዩ ክልል ከተሞች የቅሬታ ሰሚዎች በተሟላ ሁኔታ ወደ ሥራ አለመግባትና በመደበኛ ፍርድ ቤት ችሎትና የምርጫ ጣቢያ ችሎት ያላደራጁ መሆናቸውን፣ የምርጫ ቁሳቁስ መዘግየትና የምርጫ ሒደቱ ዘግይቶ የጀመረባቸው ጣቢያዎችን ማግኘቱን አክሎ ገልጿል፡፡
From The Reporter Magazine
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጭን በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ማሟላቱ ተረጋግጦ ከ49 ሺሕ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያ መራጮችን መመዝገብ እጅግ ውስብስብና ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን መመደብ የሚጠይቅ በጣም ትልቅ ኦፕሬሸን ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ትልቅ አገራዊ ሥራ ውስጥ ክፍተቶችና ጉድለቶች መኖራቸው ተጠባቂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግኝቶች በመረጃና በማስረጃ የሚቀርቡ ከሆነ ለማስተካከል እንደሚቻል፣ ነገር ግን በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሠልፍ ጠይቀው የተከለከሉት የትና መቼ ነው የሚለው በግልጽ መቅረብ አለበት ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ቦርዱ ለሁሉም ፓርቲዎች ድጋፉን እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዕጩዎችና የመራጮች ዲጂታል ምዝገባ አዲስ በመሆኑ የኔትወርክ መቆራረጥ እንደነበር ቦርዱ ማረጋገጡን ገልጸው፣ ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት የዕጩዎችን ምዝገባ ቀን ለማራዘም ተሠርቷል ብለዋል፡፡ አክለውም ከመደበኛ ነዋሪነታቸው ርቀው ለሚገኙ ወታደሮች በወታደር ካምፖች ውስጥ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች መደራጀታቸውን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ ቢሮ የተወከሉት አቶ ካሳዬ ገመቹ በሰጡት አስተያያት፣ በኦሮሚያ ክልል ከ25 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውንና ምርጫው ያለ ምንም የሰላም ችግር እንዲካሄድ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ያለ ምንም ፍራቻ ምርጫውን እንዲያከናውን አስፈላጊ የሆነ ዝግጅት መደረጉን አክለዋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ፣ ‹‹የዳበረ ዴሞክራሲ አለን የሚሉ አንዳንድ አገሮች ከእኛ ያልተሻለ ምርጫ እንደሚያካሂዱ እናውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ብዙ እንከን የሌለበት ምርጫ አካሂደን ስናበቃ አንገታችን ቀና አድርገን፣ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ምርጫ አካሂደናል የሚል ዓላማ እንጂ፣ እንከን ከተፈጠረ በኋላ በእንከኖች ላይ መነጋገር ያለብን አይመስለኝም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹ሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ የተመለከተ መደበኛ (Formal) ቅሬታ እንዳልቀረበ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ እንዲህ አድርጎኛል፣ ገዥው ፓርቲ እንዲህ አድርጎኛል፣ የፀጥታ አካል እንዲህ አድርጎኛል የሚል ቅሬታ እስካሁን ለኮሚሽኑ አልቀረበም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህን ስናይ በዓውዱ ጫናዎችና ጥሰቶች ቢኖሩ ኖሮ አቤቱታ ይመጣ ነበር የሚል ዕሳቤ ይዘናል፤›› ብለው፣ ‹‹ምርጫው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንዳለ አንዱ ማረጋገጫችን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ የድጋፍ ሠልፍና የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርግ፣ የፖሊስ ሚና መሆን የነበረበት ርቀቱን ጠብቆ ረብሻ እንዳይፈጠር መከታተል ቢሆንም፣ አንድ ቦታ ላይ ነሸጥ ሲያደርገው ገብቶ ሲጨፍር የነበረ ፖሊስ ገጥሞናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
