ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia

[ክቡር ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ሳቢያ የዋጋ ንረት ሳይመጣና የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት ሳይከሰት እንዲያስፈጽም ያዘዙትን ጉዳይ በተመለከተ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ባዘዙት መሠረት መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ከውጭ ማስገባት ጀምረናል፡፡
- ጥሩ፣ አንገብጋቢ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ነው እያስገባችሁ ያላችሁት?
- በትክልል ክቡር ሚኒስትር፣ በዋናነት ትኩረት የሰጠነው ለምግብ ዘይት ነው።
- መልካም፣ ስለዚህ የምግብ ዘይት ግዥ ፈጽማችሁ አጠናቃችኋል?
- ኧረ እንዲያውም ለሸማቾች ማኅበራት እያሠራጨን ነው።
- ምርቱ አገር ውስጥ ገብቶ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት በዚህ ፍጥነት ማሳካት ቻላችሁ? ውሳኔውን ያሳለፍነው ከጥቂት ቀናት በፊት አይደል እንዴ?
- ልክ ነው፣ ወሳኔውን የሚገልጽ ደብዳቤ ከእርስዎ ጽሕፈት ቤት ከደረሰን አንድ ሳምንት አልሞላውም።
- ውሳኔው ከተወሰነ አንድ ሳምንት ሳይሞላው ግዥ ተፈጽሞ፣ በመርከብ ተጭኖና ተጓጉዞ አገር ውስጥ ገብቶ እየተሠራጨ ነው እያልከኝ ነው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት? ምርቱን በመርከብ ጭኖ ለማጓጓዝ ብቻ ከአንድ ሳምንት በላይ አይወስድም እንዴ?
- በፊት ይወስድብን ነበር፣ አሁን ግን…
- አሁን ግን ምን?
- ምርቱን በመርከብ ማጓጓዝ አይጠበቅብንም።
- ለምን? ከውጭ እንዲገዛ የተወሰነው አገር ውስጥ ስለሌለ አይደለም እንዴ?
- ነው።
- ታዲያ ለምንድነው በመርከብ ማጓጓዝ አይጠበቅብንም ያልከው?
- ምክንያቱም ምርቱን የገዛነው ከቅርባችን ነው።
- ከየት?
- ከጂቡቲ፡፡
- ምን አልክ?
- ከጂቡቲ።
- ከጂቡቲ ነው ያልከው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- ጂቡቲ እኮ አንድ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ የምታህል አገር ናት፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ እንዴ ሊሆን ቻለ?
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ጂቡቲ እኮ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ያላት አገር ናት።
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- እና ጂቡቲ ከራሷ አልፋ የመቶ ሚሊዮኖች አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ የሚበቃ የምግብ ዘይት ታመርታለች እያልከኝ ነው?
- ነገሩ በቁጭት የሚያንገበግብ ቢሆንም እውነታው እንደዚያ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ለምን በቁጭት ያንገበግባል?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር ቁጭት የተሰማዎት መስሎኝ ነው።
- ለምን ቁጭት ይሰማኛል?
- ደጋግመው ስለጠየቁኝ የተሰማዎት መስሎኝ ነው።
- ደጋግሜ የጠየቅኩህ ተገርሜ ነው።
- እኔ ደግሞ…
- እ…?
- እኛ ግዥውን ስንፈጽም በቁጭት እየተንገበገብን ስለነበር፣ እርስዎም እንደ እኛ ተሰምትዎት ይሆናል ብዬ ገምቼ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እናንተ ለምን ቁጭት ተሰማችሁ?
- ሁሉን ነገር ይዘን በአገራችን ማምረት እየቻልን ከጂቡቲ የምግብ ዘይት ማስገባታችን ያንገበግባል ክቡር ሚኒስትር። ነገር ግን…
- ግን ምን?
- አሁንም ቢሆን ወጪዎቻችንን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ለማዋል ወስነን በቁጭት ከተነሳን ማምረት እንችላለን፣ አይረፍድብንም።
- እስኪ አስረዳኝ ምን ማድረግ እንችላለን?
- ክቡር ሚኒስትር የምግብ ዘይት ለማስገበት በየዓመቱ 300 ሚሊዮን ዶላር እያወጣን ነው፡፡
- ስለዚህ?
- ይህ አካሄዳችን አዋጭ አይደለም፣ መቆም አለበት።
- እንዴት?
- ለምሳሌ በዋና ዋና ከተሞች የዘይት ፋብሪካዎችን ማቋቋም እንችላለን።
- ይህንን ብናደርግ ደግሞ የዘይት እጥረትን ከመፍታት ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን፣ በተጨማሪም ለዘይት የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ አስቀርተን ለሌላ ልማት ማዋል እንችላለን።
- ልክ ነው፣ ግን የፋብሪካ ማቋቋሚያ ወጪው ለከተሞች ከባድ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር በአስፈላጊነቱ ላይ ከተስማማን ወጪው ብዙ የሚከብድ አይመስለኝም።
- አስፈላጊነቱማ አያጠያይቅም፣ በብዙ ድካም ያገኘነውን የውጭ ምንዛሪ ለምግብ ዘይት እያወጣን መቀጠል የለብንም።
- አስፈላጊነቱ ላይ በዚህ ደረጃ ቁርጠኛ ከሆኑ ፋብሪካዎቹን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ወጪ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
- እንዴት ነው በቀላሉ ማግኘት የሚቻለው?
- ለምሳሌ የፓርኮች ግንባታን ለተወሰነ ጊዜ አዘግይቶ….
- እ…. ከዚያስ?
- በጀቱን የምግብ ዘይት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት ማዋል እንችላለን።
- አዘግይቶ ነው ያልከው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- ፓርኮችን?
- ምሳሌ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምሳሌ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- በፓርኮች ምሳሌ?
- ቆይ ላስረዳዎት ክቡር ሚኒስትር…
- ትንሽ እንደ ቆየህ አልተሰማህም?
- ከምኑ?
- እኔ ቢሮ ውስጥ…
- ይኸው ወጥቻለሁ…
- ይቅርታ ያድርጉልኝ ክቡር ሚኒስትር!
The post [ክቡር ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ሳቢያ የዋጋ ንረት ሳይመጣና የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት ሳይከሰት እንዲያስፈጽም ያዘዙትን ጉዳይ በተመለከተ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነው] first appear on ሪፖርተር – Ethiopian Reporter – #1 reliable news source in Ethiopia and is written by በጋዜጣው ሪፓርተር