ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስያሜ በሕገ መንግሥት መሠረት መጠራት ከጀመረችበት 1987 ዓ.ም. አንስቶ፣ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ሰባተኛ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተቋቋሙ የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አከናውናለች፡፡
በእርግጥ ለአገሪቱ ለሰባተኛ ጊዜ የተመዘገበና የተከናወነ ምርጫ ቢሆንም፣ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ግን ክልል ሆነው ከተቋቋሙ በኋላ እንደ ክልል ያደረጉት የመጀመሪያ የምርጫ ሒደታቸው ሆኖ በታሪክ ተከትቧል።


የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአራት ክልሎች ሲከፈል ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ ጠንባሮ፣ ሃላባና ሐዲያ ዞኖችንና የየም ልዩ ወረዳን በማካተት ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተቋቋመው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከእነዚህ በክልል ደረጃ ከተዋቀሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ ምርጫ እንደ ክልል ከተከናወነባቸው ክልሎች አንዱ ነው።
በክልሉ 32 የምርጫ ክልሎችና 2,998 የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ዜጎች ድምፃቸውን እንዲሰጡ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን ለሕዝቡ ክፍት መደረጋቸው ነው የተነገረው።
ሪፖርተር በክልሉ ዋና ከተማ ሆሳዕና ከምርጫው ቀን አስቀድሞ በመገኘት በመዲናዋና አካባቢው የነበሩ የምርጫ ዝግጅቶችን፣ የምርጫው ቀን የድምፅ አሰጣጥ ሒደቶችንና በማግሥቱም ማለትም ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. የጊዜያዊ የምርጫ ውጤት መግለጫዎችን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ለመታዘብና ከአስተባባሪዎች፣ ከታዛቢዎችና ከመራጩ ሕዝብ ጋር ለመነጋገርም ችሏል።
ከምርጫው ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት የማዕከላዊ ኢትዮጵያና በዙሪያዋ የሚገኙ አካባቢዎች ላይ ባደረግነው ቅኝት ከአካባቢው ቀዝቀዝ ያለ የአየር ንብረት ሁኔታ ጋር የተጋባ የሚመስል ጭርታ ይታይ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በነበሩት ቅዳሜና እሑድ የንግድ ቤቶች በብዛት ተዘግተው የከተማው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም እጅግ አልፎ አልፎ በዝግታ ከሚያልፉ ባለ12 ሰው ጫኝ ታክሲዎች ውጪ፣ እምብዛም እንቅስቃሴ የማይስተዋልበት ሁኔታ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል።
From The Reporter Magazine
በሆሳዕና ከተማ ዋና ዋና ሰፋፊ መንገዶችም በብዙኃን ዘንድ እንደሚገመተው ከዚህ ቀደም በነበሩ የምርጫ ዓመታት የሚስተዋሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶችንና የዕጩዎችን በጉልህ አድርገው የሚያሳዩ ትልልቅ የማስታወቂያ ምልክቶች (ባነሮች)፣ ምናልባትም ከተማዋ ውስጥ ከአምስት ቦታ በላይ አልተመለከትንም። እነዚህም ማስታወቂያዎች የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች እንደነበሩ፣ በሌላ በኩል አልፎ አልፎ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ በትንንሽ ምግብ ቤቶች አጠገብ፣ በተተከሉ በስልክ እንጨቶች ላይ ኤ ፎር በሚባል በሚታወቀው ወረቀት የዕጩዎች ስም ያልተካተተበት የመወዳደሪያ ምልክቱንና ስሙን ብቻ የያዙ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፖለቲካ ፓርቲ ስምን የሚያሳዩ የማስታወቂያ ወረቀቶች በዝናብ በስብሰው ተለጥፈው ታይተዋል።
ከከተማው ድባብ በተለየ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የሕዝብ መሰብሰቢያ አካባቢዎች ባነጋገራቸው ሰዎች ዘንድ ግን ከፍተኛ የምርጫ ጉጉት ተመልክቷል።
በረከት የተባለ ኑሮውን በሞተር ብስክሌት አገልግሎት ዕቃዎችን በማድረስና በምላሹም ክፍያ በመቀበል የሚያስተዳድር ወጣት፣ ‹‹ከትንሽ ዓመት በፊት ክልል የመሆን ጥያቄ በሕገ መንግሥት መሠረት አቅርበን ቀና ምላሽ አግኝተንበታል። ከምንም ነገር በላይ መምረጥ የምፈልገው ለዚያ ነው፣ አሁንም ያሉኝን ጥያቄዎች ይዤ በሕጉ መሠረት ብመርጥ የምፈልገውን የማግኘት ዕድል አለኝ ብዬ አስባለሁ፤›› ብሏል።
From The Reporter Magazine
የበረከትን ዕይታ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌሎች ነዋሪዎችም ተጋርተውታል። በከተማው የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች በስፋት ስላለመታየታቸው በተመለከተም ነዋሪዎችን ያነጋገርን ሲሆን፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ቢሆን ከሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ይልቅ በመኪና ላይ በድምፅ ማጉያ በመጠቀም የሚደረጉ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ይበዙ እንደነበር አሳውቀዋል።
ይሁንና እነዚህም ቅስቀሳዎች ቢሆኑም ብዙም የፓርቲዎች ስብጥር በስፋት ያልታየባቸው ስለመሆናቸውም ያነሱ ነበሩ፡፡ በሆሳዕና ሊሙ ወረዳ 01 በተባለ አካባቢ በሚገኝ አንድ መለስተኛ ሆቴል በአስተናጋጅነት ተቀጥራ የምትሠራ ትሁት የተባለች ወጣት፣ ‹‹አላጋጠመኝ ይሁን አላውቅም፣ ብዙ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ ሲባል ሰምተናል፡፡ ግን ከተማው ውስጥ ብዙም ተዟዙረው ሲያስተዋውቁ ያየኋቸው ግን ሦስት የሚሞሉ አይመስለኝም፤›› ብላለች።
በሰባተኛው አገራዊ ምርጫ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከግል ዕጩዎች ባሻገር ኢዜማ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ ብልፅግና፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ ህዳሴ ፓርቲና የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፓርቲዎች ዕጩዎች መወዳደራቸውን ሪፖርተር ከምርጫ ሰነዶች ለመገንዘብ ችሏል።
ከእነዚህ ፓርቲዎች ውጪ ለብቻቸው የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት የቀረቡ የግል ዕጩዎችም በተሰናዱበት ወቅት ነበር፣ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የምርጫ ጣቢያዎች ለሕዝብ ክፍት የተደረጉት።
ሪፖርተር በዚህ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ከተማ ሆሳዕናና አካባቢው ያለውን የምርጫ ሒደት ለመከታተል ከማለዳ 11:30 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን፣ ከማለዳ 11 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከባድ ዝናብ ሲዘንብ ቆይቷል። ይሁንና ሪፖርተር ተዘዋውሮ ከባዱ ዝናብ ወደ ስስ ካፊያ ተቀይሮ እስከቆየበት ረፋድ 4፡30 ሰዓት ድረስ በተመለከታቸው ጣቢያዎች ግን መራጮች ከሌሊት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ረዣዥም ሠልፎች ላይ ታይተዋል።
በሆሳዕና ከተማና አካባቢው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለምርጫ በመገደቡ፣ ዜጎች በዋና ዋና መንገዶች በእግር ውስጥ ለውስጥ በሚወስዱ መንገዶች ደግሞ በሞተር ሲንቀሳቀሱ ነበር።
ሪፖርተር ከተመለከታቸው ጣቢያዎች መካከል ሊሞ 01 ምርጫ ክልል ጀሎናሞራ ቀበሌ፣ አዳምስቴርማን በጎ አድራጎት ትምህርት ቤት ጎን ለጎን፣ ሆሳዕና ጎጊቾ ቀበሌ አጉሙራ ኪራይ ቤት አካባቢ ያለ የምርጫ ጣቢያ ናቸው፡፡ ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ በእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ስፖርት ሆቴል ጎን፣ መብራት ኃይል ፊት ለፊት፣ ጀሎናሞራ ቀበሌ፣ ሞቢል ጎን፣ ንአረሞ መንደር 2፣ ሄጦ ስታዲየም ፊትለፊት፣ ሄጦ ምርጫ ጣቢያ መስጊድ ሠፈር፣ አምቢቾ ጎዴ ምርጫ ጣቢያ ከጎሚስታ ጤና ኬላ፣ እንዲሁም ኮንቶብ 03 ሊሙ ወረዳ ከዲቅሳ ቀበሌ በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ ስም ከዲቅሳ ኪራይ ቤት የተባሉት ይገኙበታል።
በሊሞ 01 ምርጫ ክልል ጀሎናሞራ ቀበሌ አዳምስቴርማን በጎ አድራጎት ትምህርት ቤት ጎን ለጎን ባለው የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ 1,400 ሰው ለመምረጥ የተመዘገበ ሲሆን ምርጫው ጠዋት 12 ሰዓት መጀመሩን ለመታዘብ ተችሏል። በዚህ ጣቢያ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተወዳደሩ ቢሆንም አንድ የብልፅግና ታዛቢ ብቻ መኖራቸውንም ተመልክተናል።
ሆሳዕና ጎጊቾ ቀበሌ አጉሙራ ኪራይ ቤት አካባቢ ያለ የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስተባባሪው ለሪፖርተር እንዳሳወቁት 1,499 ሰዎች ለመራጭነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ በጣቢያው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ ዕጩዎች፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 33 ዕጩዎች መቅረባቸውም ታውቋል።
በጣቢያው ስድስት ታዛቢዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ታዛቢ ብቻ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሲወከሉ ሌሎቹ የብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች መሆናቸውንም ሪፖርተር መገንዘብ ችሏል።
ኮንቶብ 03 ሊሙ ወረዳ ከዲቅሳ ቀበሌ በኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ ስም ከዲቅሳ ኪራይ ቤት የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስተባባሪው 1,500 መራጮች መመዝገባቸውን፣ አራት ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልሉ ምክር ቤት በተመሳሳይ ሌሎች አራት ዕጩዎች መቅረባቸውን አሳውቀዋል።
በአምቢቾ ጎዴ ምርጫ ጣቢያ ከጎሚስታ ጤና ኬላ ምርጫ ጣቢያ 1,500 መራጮች መመዝገባቸውን የጣቢያው ምርጫ አስተባባሪ አቶ ከይረዲን ሳሎ አሳውቀው የነበረ ሲሆን፣ ለክልል ምክር ቤት 24 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቁጥራቸውን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኗቸው ዕጩዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሪፖርተር በእነዚህ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ረዣዥም የመራጮች ሠልፍ የነበረ አብዛኛው ሕዝብ ወጣትና ጎልማሳ ወንዶች መሆናቸውን አልፎ አልፎ ብቻ ሴቶች ለመምረጥ ተሠልፈውም ታይቷል። ሦስቱም የምርጫ ጣቢያዎች ሪፖርተር ያነጋገራቸው መራጮች ከሌሊት ጀምሮ ቢሠለፉም የመምረጥ ሒደቱ በዘገየ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ሲያሳውቁ፣ በወቅቱ ጉዳዩን በተመለከተ የየምርጫ ጣቢያው አስተባባሪዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም መሠረት አቶ ተመስገን ሀምቤ የተባሉ አስተባባሪ በኦንላይን የተመዘገቡ መራጮችን ስም ዝርዝር ከወረቀት መዝገብ ጋር አመሳክሮ ስማቸውን ቶሎ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ፣ መራጮችን ቶሎ ቶሎ ለማስተናገድ መቸገራቸውን ገልጸዋል።
በሌላ የምርጫ ጣቢያ አቶ ኢያሱ አበራ የተባሉ አስተባባሪ በበኩላቸው፣ ‹‹ሕዝቡ ሌሊት ዝናብ እየዘነበ ለምርጫ ሠልፍ ወጥቷል፣ ነገር ግን በኦንላይን የተመዘገበውን መራጭ በቀላሉ ለማግኘት የሞባይል ታብሌት ቢኖር ጥሩ ነበር፣ ሕዝቡን በቁጥር ቶሎ ለመድረስ ዕድል ይኖረን ነበር፣ አሁን ችግሩን እየፈታን ያለነው አስመራጮች ለሁለትና ለሦስት በመሆን ከመዝገብ ላይ የመራጮችን ድምፅ እንዲፈልጉ በማድረግ ነው፤›› ብለዋል።
አቶ ፀደቀ ብርሃኑ የተባሉ የሌላ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ በበኩላቸው፣ በተመደቡበት የምርጫ ጣቢያ በኦንላይንም በቀጥታ በአካልም የተመዘገቡ መራጮች መኖራቸውንና ከሌሎች ጣቢያዎች ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
ሪፖርተር ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ ረፋድ ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሁለቱ ጋ ብቻ ቁጥራቸው አነስተኛ የፀጥታ አባላት የተመለከተ ሲሆን፣ በተወሰኑት ጣቢያዎች ሚሊሻዎች የጦር መሣሪያ ሳይዙ ዩኒፎርም በመልበስ ብቻ ሲያስተባብሩ ተመልክቷል።
ይሁንና በሆሳዕና ሊሙ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በር ላይ በሚገኘው የአስፋልት መንገድ የፀጥታ አካላት ተሽከርካሪዎች ይዘው ወደ ከተማው መግባት እንደማይችሉ በመግለጽ፣ ነዋሪዎች በእግራቸው እንዲጓዙ በመንገር ሲመልሱ ታይተዋል።
እስከ ረፋድ የነበረው የምርጫ ሁኔታ ከሰዓት በኋላም በተመሳሳይ በረዥም ሠልፎች በተጨናነቁ የምርጫ ጣቢያዎች ዝግ ባለ የመስተንግዶ ፍጥነት መዝለቃቸውን ተመልክቷል። ሪፖርተር በጎጊቾ ቀበሌ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ያነጋገራቸው ነፍሰ ጡር እናት ለመምረጥ በሌሊት ባይሠለፉም፣ ቀድመው የመጡና የተሠለፉ ሰዎች ግን ለእናቶችና አዛውንት ቅድሚያ በመስጠት እየተባበሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጀሎናሞራ ቀበሌ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች በነበሩ ሠልፎች ደግሞ መራጮች ሠልፍ ጥሰው እየሄዱ ያላግባብ እንድንዘገይ እየተደረግን ነው የሚሉ ቅሬታዎችን የሚያቀርቡ ነዋሪዎችን ሪፖርተር ያነጋገረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አቅማችን ደካማ ስለሆነና የተለያየ የጤና እክል ስላለብንም ለረዥም ሰዓት መቆም አንችልም ያሉ ወደ አሥር የሚሆኑ እናቶች ከምርጫ ጣቢያው አቅራቢያ በነበረ በተዘጋ ሱቅ አጠገብ ዣንጥላዎቻቸውን ዘርግተው ተቀምጠው በመጠበቅ አስተባባሪዎች ቅድሚያ የመምረጥ ዕድል እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። ይሁንና በጣቢያው የነበሩት ዋና አስተባባሪ፣ ‹‹የተለያዩ ምክንያቶችን ለሚያቀርቡት ቅድሚያ መስጠት ከጀመርን በሌሊት መጥቶ የተሠለፈውን ሕዝብ መበደል ይሆናል፡፡ የሁሉም መራጭ ድምፅ እኩል ነው፣ እንደ ማናቸውም መራጮች ተራቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል።
በእነዚህ ሠልፎች ተደርድረው ተራቸውን ሲጠባበቁ የነበሩ ነዋሪዎችን ሪፖርተር የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ በአንዳንዶች ዘንድ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ተጠቅመን ለመምረጥ ጓጉተናል፤›› የሚል ምላሽ፣ በሌሎች የተወሰኑ ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱን በአግባቡ አለመረዳትና የፓርቲ ስም በመጥቀስ፣ ‹‹እሱን ብቻ መምረጥ እንዳለብን እናውቃለን፤›› የሚል በሌሎች የተወሰኑ በኩል ደግሞ፣ የምርጫ ካርዱን ይዘው በጣቢያው ቢገኙም አስተባባሪዎችን፣ ‹‹ቆይ አስረዱኝ እስኪ መምረጥ በሕግ ግዴታ ነው ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎችንም የጠየቁ መኖራቸውን ተመልክተናል።
ከእነዚህ ባለፈ ‹‹አስተባባሪዎች ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ይንገሩኝ፤›› የሚሉ፣ እንዲሁም በክልልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ወረቀቶች ላይ ስንት ዕጩ መምረጥ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መራጮች የተስተዋሉ ሲሆን፣ በዚህም መነሻነት አስተባባሪዎች በተደጋጋሚ በወንበሮች ላይ በመቆምና ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ የምርጫ ሒደት ሕጎችንና የመራጮች መብትና ግዴታዎችን ሲያስረዱም ሪፖርተር በተለያዩ ጣቢያዎች ተመልክቷል።
በሌላ በኩል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወልቂጤ ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ታዛቢዎች ተደብድበው ከምርጫ እንዲወጡ ተደርገዋል ሲል ጎጎት ፓርቲ፣ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አጭር ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር።
‹‹ፓርቲው ይንቀሳቀስበት የነበረው ሞተር ተነጥቋል። የምርጫ ወረቀት በፌስታል ይዘው ሲበትኑ ተመልክተናል። ለምርጫ ቦርድ ምርጫው እንዲቆም አሳውቀናል፤›› ብሎ፣ ከምርጫ ቦርድ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚፈልግም አስታውቆ ነበር፡፡
ሪፖርተር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ምርጫ አስተባባሪ አነጋግሯቸው በሰጡት ምላሽ፣ ጎጎት ፓርቲ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወልቂጤ ከተማ ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ታዛቢዎች ተደብድበው ከምርጫ እንዲወጡ ተደርገዋል በማለቱ ምክንያት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ጋርም ጉዳዩን ለማጣራት በስልክ መወያየታቸውን፣ እሳቸውም ወደ ቦታው አስተባባሪዎች ልከው እንዳጣሩ የተባሉት ድርጊቶች በፓርቲው ላይ እንዳልተፈጸሙ፣ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ወረቀትን መበተን የተባለውም እንዳልተደረገ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ይህ ሆኗል ባለበት የምርጫ ጣቢያ መግለጫውን ባወጣበት ወቅት ጭምር ሁለት ታዛቢዎቹ በጣቢያው እንዳሉም የገለጹት ዋና አስተባባሪው፣ ፓርቲው የተናገረው ከእውነት የራቀ መሆኑን አክለዋል። ሌላው ሱልካ በተባለ ጣቢያ አካባቢ የፓርቲው ታዛቢ ባጅ ስለተጠየቀ አኩርፎ ከመውጣቱ ውጪ ሌላ የተፈጠረ ነገር የለም ሲሉም አስረድተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሆሳዕና ከተማና አካባቢው እነዚህን የመሰሉ ጉዳዩች በታዩበትና ረዣዥም ሠልፎች ከሰዓቱን ሙሉ በዘለቁበት ሁኔታ፣ አስቀድሞ የተቀመጠው የምርጫ ሰዓት ገደብ ምሽት 12 ሰዓት መሙላቱንም አስተውለናል።
ምንም እንኳን የምርጫ ሰዓት ገደቡ ቢያልቅም ከተመዘገቡ መራጮች በጣቢያ ተገኝተው ድምፅ መስጠት ያልቻሉት በዝተው በመታየታቸው በሚል ሰዓቱ ሲሞላ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ የሰዓት ገደቡን ወደ እኩለ ሌሊት ማሻገሩን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህን ሰዓት ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ለመስጠት በሚጠባበቁ መራጮች ተጨናንቀው መቀጠላቸው ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች በዝናብ ምክንያት በድንኳን ውስጥ የተዘረጉ አምፖሎች ሊሠሩ ባለመቻላቸው አስመራጮች ስልካቸውን በማብራት የመራጭ ስም ሲፈልጉ፣ እንዲሁም ዜጎች መምረጣቸውን የሚያሳይ ምልክቶች ሲያሰምሩ፣ መራጮች ለብቻ በተከለሉ መምረጫ ቦታዎች እንዲሁ ስልክ አብርተው እየተጠቀሙ መሆኑን፣ በከተከለሉበት ነጭ ቀለም ያለው አንድ ሰውን ብቻ በሚከልል ድምፅ መስጫ ቦታ በስተውጪ በኩል በሚታየው ነፀብራቅ ተመልክተናል።
ይህ በዚህ እንዳለ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙን የሚገልጽ መግለጫ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ፣ ‹‹በቀጥታ ተደውሎ አልተነገረንም፣ ምሽት 12 ሰዓት አልፏል ስለዚህ ድንኳን ውስጥ ያለውን ብቻ ነው የምናስተናግደው፤›› የሚል ምላሽ ከአስተባባሪዎች ሲሰጥ በመራጮች ላይ ቅሬታ ፈጥሮ የነበረ መሆኑም ተስተውሏል።
ይሁንና መሰል ቅሬታ በተፈጠረባቸው እንደ ሊሙ 01 ምርጫ ክልል ጁሎናሞራ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ አዳምስቴርማልን በጎ አድራጎት ትምህር ቤት አጠገብ የነበረ ምርጫ ጣቢያን የመሰሉ ቦታዎች በመራጩ አነሳሽነት ጉዳዩን እንዲጣራላቸው በማድረግ ድምፅ መስጠት እንዲችሉ ማድረጋቸውን፣ ሪፖርተር ምሽት ሦስት ሰዓት በቦታው ካገኛቸው መራጮች መገንዘብ ችሏል።
በሌላ በኩል በሆሳዕና ጎጊቾ ቀበሌ አጉመራ ኪራይ ቤት ባለ የምርጫ ጣቢያ ደግሞ የቦርዱ የማራዘም መግለጫ በወቅቱ በመድረሱ፣ የጣቢያው አስተባባሪ በቦታው ዘግይተው ምሽት 1:30 ላይ ለደረሱ መራጮች እንዳይቻኮሉና ጊዜው ስለተራዘመ ተረጋግተው እንዲመርጡ ሲናገሩ ተስተውለዋል።
