- አገር አቀፍ የስታትስቲክስ ጥናት ለማካሄድ ከተቋሙ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ሥርዓትን በበላይነት የሚመራ የብሔራዊ ስታትስቲክስ ቦርድ የሚያቋቁም ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ፡፡ ረቂቁ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በይፋ ስታትስቲክስ የማመንጨትና የማሠራጨት ኃላፊነት የተጣለበት፣ ራሱን የቻለ፣ ሙያዊ ነፃነት እንዲኖረው ተደርጎ እንዲቋቋም የሚያደርግ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ጉባዔ የስታትስቲክስ አገልግሎት ነፃ ሆኖ እንዲቋቋም የሚፈቅድ ረቂቅ ላይ ተወያይቷል፡፡
የሚቋቋመው ቦርድ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የስታትስቲክስ ሥራዎችን በአገር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የልማት አጀንዳዎች ጋር መጣጣሙን እንደሚያረጋግጥ፣ በሴክተር መሥሪያ ቤቶች መካከል በዘላቂነት መኖር ያለበትን ትብብር ያጠናክራል ይላል ረቂቅ ሕጉ፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ይፋዊ ስታስቲክስን የማመንጨትና የማሠራጨት ኃላፊነት የተጣለበት ራሱን የቻለ ሙያው ነፃነት ያለው ተቋም ሆኖ ዕውቅና እንዲኖረው ተገልጾ፣ ተጠሪነቱ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር መሆኑ ተደንግጓል፡፡
ለምክር ቤቱ ፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ የተመራው ረቂቅ፣ ዘጠኝ አባላት ያሉት ብሔራዊ የስታትስቲክስ ቦርድ እንደሚቋቋም ይጠይቃል፡፡ የቦርድ አባላቱ የመንግሥት አካላት፣ የአካዴሚክና የምርምር ተቋማት፣ የግል ዘርፍ ተወካዮች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦችን በአባልነት ይይዛል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢና ሌሎች የቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሾሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ስታትስቲክስን የተመለከቱ ጉዳዮች አሠራርና ሙያዊ ነፃነትን በማረጋገጥ አስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ይከላከላል ይላል ረቂቁ፡፡
ከ21 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል አስገዳጅ ምክንያቶች መኖራቸውን በሚያብራራው የረቂቁ ክፍል፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በተቋማዊ ግልጽነትና አስተዳደር ላይ ጉልህ የሆኑ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ያብራራል፡፡
የማሻሻያው ረቂቅ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፎችን የአፍሪካ የስታትስቲክስ ቻርተር፣ ምርጥ ተሞክሮና ልምድ ካላቸው አገሮች የተወሰዱ ሐሳቦችና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያጣጣመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
From The Reporter Magazine
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ቴክኒካዊ መሥሪያ ቤት በመሆኑ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ እንዲሠራ ሥልጣን እንደተሰጠው በረቂቁ የተመላከተ ሲሆን፣ ተቋሙ በመረጃ ምንጮች በሥነ ዘዴዎች በምደባዎችና ውጤቶችን ይፋ በማድረግ አሠራር ላይ አስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ሳይደረግበት ሥራውን ለማከናወን ሥልጣን እንደሚኖረው ተብራርቷል፡፡
የስታትስቲክስ አገልግሎት በዳታ አሰጣጥ መመርያ መሠረት፣ ከመንግሥታዊ ድርጅቶችና መረጃን በነፃ እንዲወስዱ ከተፈቀደላቸው በስተቀር የጥናትና የቆጠራ ጥሬ ዳታን ለመስጠት ክፍያዎችን ሊያስከፍል እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
ማንኛውም በአገር አቀፍ ደረጃ የስታትስቲክስ ጥናት ለማካሄድ ያቀደ አካል ጥናቱን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት፣ አገልግሎት ተቋሙን ማማከርና በስታትስቲክስ ጥናት ዘዴው ላይ የአገልግሎትን ተቋሙ ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት በረቂቁ አንቀጽ 20 ተደንግጓል፡፡ ዳታ ማመንጨትን ማቀናጀትና ዳታ ማረጋገጥን የሚመለከቱ ዝርዝር አሠራሮች በደንብ እንደሚገለጹ ተደንግጓል፡፡
From The Reporter Magazine
ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና የግልና የመንግሥት ድርጅቶች፣ እንዲሁም ሌሎች መልስ ሰጪዎች በስታትስቲክስ ጥናቶችና ቆጠራዎች ላይ የመተባበር ግዴታ አለባቸው የሚለው ረቂቁ፣ መልስ ሰጪዎች የመተባበር ግዴታ አለባቸው ይላል፡፡ መልስ ሰጪዎች የተሳሳተ መረጃ ከሰጡ ወይም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አስፈላጊውን መልስ ካልሰጡ በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ በረቂቁ ውስጥ ሠፍሯል፡፡
