በስደተኝነትና በጥገኝነት ጠያቂነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ፍላጎት ለማሟላት፣ ከሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ የልማት ፋይናንስ እንደሚያስፈልግ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጥሪው የቀረበው የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ኤጀንሲ፣ እንዲሁም ከአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀውን ‹‹ማካተት›› የተሰኘ ፍኖተ ካርታ ይፋ ሲደረግ ነው፡፡
ፍኖተ ካርታው ስደተኞችንና ስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰቦችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግና ከሰብዓዊ ዕርዳታ ባለፈ፣ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የልማት ፋይናንስ አማራጮችን ለማፈላለግ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በጦርነትና በሚደርስባቸው ሥቃይ ምክንያት ከአገራቸው ተሰደው የሚመጡ ስደተኞችን በንቃት ተቀብላ እያስተናገደች ነው ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ከሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ባሻገር፣ ተገማችና ለበርካታ ዓመታት የሚያገለግል የልማት ፋይናንስ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ‹‹አገራዊ ልምድን በመያዝ ከባድ የሚባል ሰብዓዊ ቀውስን ወደ ጋራ ቀጣናዊ ልማት መለወጥ እንችላለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ማካተት›› የተሰኘው ፍኖተ ካርታ፣ ‹‹መደመር በተሰኘው ፍልስፍና ውስጥ ያለ ዕሳቤ ነው›› ያሉት አፈ ጉባዔው፣ ስለሰብዓዊ ፍላጎት ሲታሰብ ከመሠረታዊ ፍላጎት ባለፈ ሰዎች በሕይወት ሲኖሩ የሚያስፈልጋቸውን አካላዊ ደኅንነት፣ ክብርና ራስን መቻል ማመጣጠን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
‹‹ማካተት›› የተሰኘው ፍኖተ ካርታ እንደሚለው በኢትዮጵያ ተጠልለለው ከሚገኙት አጠቃላይ 1.2 ሚሊዮን ስደተኞች 15 በመቶ የሚሆኑት በከተሞች ሲገኙ፣ 80 በመቶ የሚሆኑት በኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት ቁመናቸው ወደኋላ በቀሩ ክልሎችና መሠረተ ልማት ባልተሟላላቸው የድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም 80 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞች ሴቶችና ሕፃናት ናቸው ይላል፡፡
ለረዥም ጊዜ የተለመደው የስደተኞች አያያዝ ሥርዓት የስደተኞችን ሁኔታ የረሳ፣ ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎችን በመጠለያ ለይቶ በማስቀመጥ ብቻ የዕርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል ያሉት አፈ ጉባዔው፣ የማካተት ፍኖተ ካርታ ግን ምቹ ካልሆነ አዙሪትና ከጊዜያዊ የመጠለያ ኑሮ ዘላቂ ወደ ሆነ አገራዊ የልማት ስትራቴጂ ምሰሶ ውስጥ እንዲካተቱ ያደርጋል ብለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹1.2 ሚሊዮን ስደተኞች ያለ ፍላጎታችን የመጡብን ግዴታዎች ሳይሆኑ፣ ሰብዓዊ ኃላፊነትና ለቀጣናዊ ሰላም፣ አብሮ መኖርና መረጋጋት ያለንን ቁርጠኝነትና ስትራቴጂካዊ ሚናችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ከለላ በመስጠትና ትርጉም ያለው ዕድል በማመቻቸት፣ በቀጣናው በተፈናቀሉ ሕዝቦች ምክንያት የሚፈጠረውን አለመረጋጋት ለመቀልበስ የበኩሏን ኃላፊነት ትወጣለች በማለት አስረድተዋል፡፡
የስደተኞች ጉዳይ በሰብዓዊ ዕርዳታ ብቻ የማይሸፈን በመሆኑ ቀጣይነት ባለውና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል የልማት ፋይናንስ፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትና እውነተኛ ዓለም አቀፍ የልማት ግዴታዎችን መወጣት ይጠይቃል በማለት አክለዋል፡፡
የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የሁለትዮሽ ግንኙነት አጋሮችና ሌሎች ወዳጆች ያደረጉትን ድጋፍ ኢትዮጵያ ታመስግናለች ብለው፣ ‹‹ነገር ግን የአሁኑና የወደፊቱ የመፈናቀል ፈተናዎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይፈልጋሉ፤›› በማለት ጥሪ አድርገዋል፡፡ ሚኒስትሩ ለልማት አጋሮችና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አካባቢዎች አገራዊ የልማት ቀዳሚ አጀንዳዎች እንጂ የመድረክ ዕሳቤዎች አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
From The Reporter Magazine
ስደተኞችን በሚያስተናግዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች የበጎ አድራጎት ተግባራት ሳይሆኑ ለመቋቋሚያ፣ ለሰላም፣ ለብልፅግና፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያና ለቀጣናው አንድነትና መረጋጋት የሚያገለግል ነው በማለት ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አህመድ ፍኖተ ካርታው ከሌሎች አገሮች ሞዴል ከመቀበል ይልቅ፣ በአኅጉራዊና በአገራዊ ፈጠራ የሚመራ ስትራቴጂና ሥልት የዘየደ በመሆኑ በጋራ በመሆን መፈናቀልን ወደ ልማታዊ ዕድልና ቀጣናዊ ትብብር መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፍኖተ ካርታው ዓላማ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ቀውስን መቋቋም፣ ስደተኞችን ሕጋዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚና የፋይናንስ ተጠቃሚ ማድረግ፣ ከዕርዳታ ተቀባይነት ወደ ሀብት አመንጪነት እንዲሸጋገሩ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡
ለስደተኞች የደኅንነት ጥበቃና ቀጣይነት ያለው መፍትሔ በመስጠት ክብር ያለው ከለላ እንዲኖራቸው ማመቻቸት፣ መሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግና በልዩ መጠለያ የነበሩ ስደተኞችን አገራዊ የልማት ተጠቃሚ ማድረግን ያለመ መሆኑን ሰነዱ ብራራል፡፡ በተጨማሪም ተቋማዊ ቅንጅት በማድረግ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የተሰናሰለና ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት መተባበርን የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን፣ በግጭትና በሰላም ዕጦት እንዲሁም በአየር ንብረት ጫና ከቀጣናው የመጡ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ኢትዮጵያ እያስተናገደች መሆኗን ጠቅሰው፣ ፍኖተ ካርታው ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ያላቸውን ሕይወት ከብሔራዊ ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋርም ሆነ የዜግነት ሕጎች ጋር የማይጋጭ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ቅንጅትን በማጠናከር የሀብት ፍሰቱን ለመምራትና የተሻለ አገልግሎት በማቅረብ የስደተኞችን ሁኔታ ከአገራዊ ልማት ጋር የሚያጣጥም ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
በሰነዱ እንደተመላከተው በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ ስደተኛ የመቆያ ጊዜው በአማካይ 15 ዓመታት ቢሆንም፣ አንዳንድ አካባቢዎች ለ30 ዓመታትና ከዚያም በላይ ስደተኞችን ተቀብለው እያስተናገዱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ የፋይናንስ ምንጮች እያሽቆለቆሉ መሆኑን ገልጸው፣ 95 በመቶ ስደተኞች ለተራዘመ ጊዜ ባላደጉ ክልሎች ውስጥ ተጠጋግተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በኢትዮጵያ ለተራዘመ ጊዜ በመጠለያ በስደተኝነት የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎችን፣ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ቢያንስ በግማሽ ለመቀነስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የሀብት እጥረት፣ ውስን የኢኮኖሚ አማራጮችና ሰብዓዊ ዕድገት፣ እንዲሁም እየቀነሰ የመጣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድህነቱን እያሰፋና ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ አካባቢዎችን ሕይወት እያቃወሱ መሆናቸው በሰነዱ ተብራርቷል፡፡
በኢትዮጵያ ተጠልለው ከሚገኙ 1.2 ሚሊዮን ስደተኞች ውስጥ 35 በመቶ ያህሉ ምቹና በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ለመኖሪያነት በማይበቃ፣ በማይመች ምኅዳር ውስጥ የሚገኙ፣ በቂ ጥበቃ በሌላቸውና ስደተኞችን ለጤናና ለደኅንነት አደጋ ውስጥ በሚጥሉ መጠለያዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡
