በመረጃ ነፃነት አዋጅ ሙስናን ወይም ሌላ ሕገወጥ አሠራርን፣ የሥራ አፈጻጸም ብቃት ጉድለትን ወይም የግለሰብ ወይም የመንግሥት አካል ወይም የድርጅት ሕገወጥነት ለመሸፈን፣ መረጃና ሰነድ በሚስጥር እንዲያዝ ያደረገ ኃላፊ አምስት ዓመት እንዲቀጣ የሚያደርግ አዋጅ ፀደቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በእጃቸው ያለን መረጃ እንዲሰጡ የሚያስገድደውን የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ፣ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡
ፓርላማው መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ላይ የመጀመሪያ ንባብ አካሂዶ፣ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር ዕይታ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል፡፡ ከሁለት ወራት ውይይት በኋላ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያብራራው፣ የወንጀል ጥፋቱ በፍርድ የተረጋገጠበት የበላይ ኃላፊ፣ የመረጃ ኃላፊ ወይም ይህንን ያዘዘ ሌላ ኃላፊ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቶ ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ደንግጓል፡፡
በተመረጡ አንዳንድ ተወዳጅና የመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ በተጋበዙበት የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ የፀደቀው የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ፣ የመረጃ ነፃነት ለመጣስ በማሰብ ሆን ብሎ መረጃን ወይም ሰነድን ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ፣ የደለዘ፣ የደበቀ ወይም ያፋለሰ፣ በተንኮል የከለከለ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ የሠራ ከሆነ እስከ አምስት ዓመት እስር ያጋጥመዋል ይላል፡፡
ሆን ብሎ የተሳሳተ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ መረጃና ሰነድ ለመረጃ ጠያቂ የሰጠ፣ በተቋሙ የተሰጠን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ያለ በቂ ምክንያት ያልፈጸመ፣ በዚህ አዋጅ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ለመረጃ ጠያቂዎች ምልሽ ያልሰጠ፣ ወይም በሚስጥር መያዝ ያለበት መሆኑን እያወቀ የመከላከያና የአገር ደኅንነት መረጃን ለጠያቂ የሰጠ ወይም ይፋ ያደረገ የበላይ ኃላፊ፣ የመረጃ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ እንደ ጥፋቱ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ25,000 ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል ይላል፡፡
የመረጃ ጥያቄን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ፣ መረጃና ሰነድ አትሞ የማውጣት ግዴታ ያልተወጣ፣ በቃል የቀረበን የመረጃ ጥያቄ በመረጃ መጠየቂያ ቅጽ ላይ ለመሙላት ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም ግልባጩን ለመረጃ ጠያቂ ያልሰጠ፣ ለአካል ጉዳተኛ ሊነበብ፣ ሊታይ ወይም ሊደመጥ በሚችል አግባብ ተደራሽ ለማድረግ ምክንያታዊ ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታን ያልተወጣ፣ ወይም እያወቀ ሐሰተኛ ወይም የተዛባ ሰነድ ለተቋሙ የሰጠ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ25 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
የመረጃ ኃላፊ ወይም ባለሙያ ሊደርስበት ከሚችል አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነት ሕጋዊ ፍራቻና ሥጋት ነፃ ሆኖ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል ሕጋዊ ከለላ ለመስጠት ማስፈለጉን በሚያብራራው ድንጋጌ፣ በቅን ልቦና ለመፈጸም በተደረገ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት የመረጃ ኃላፊ ወይም ባለሙያና መረጃውን በቅን ልቦና ያሠራጨ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ከወንጀልና አስተዳደራዊ ተጠያቂነት ነፃ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
