የሰላምና ፀጥታ ችግር፣ የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የግብር ማሻሻያ ተዕፅኖዎች፣ የጉምሩክ ጉዳዮችና የፋይናንስ አቅርቦት አናሳ መሆን፣ ለግሉ ዘርፍ ዋነኛ ማነቆዎች ሆነው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ጥናት አመላከተ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ከሳይፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፣ ሦስተኛውን ብሔራዊ የቢዝነስ አጀንዳዎች የባለድርሻ አካላት የማሳወቂያና ተጨማሪ ግብዓት የማሳወቂያ ዓውደ ጥናት ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ተካሂዷል።
በዓውደ ጥናቱ የግሉ ንግድ ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች በጥናት ተለይተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የጥናትና አድቮኬሲ ተጠባባቂ ዳይሬከተር አቶ ታከለ አየለ፣ ሦስተኛውን ብሔራዊ የቢዝነስ አጀንዳ አስመልክቶ ባቀረቡት የጥናት ሰነድ በሕጋዊ፣ በመዋቅራዊና በአስተዳደራዊ ማነቆዎች ምክንያት የግሉ ዘርፍ በአገር ደረጃ ባለው አቅም እየተንቀሳቀሰ አይደለም ብለዋል።
ብሔራዊ የንግድ አጀንዳ በዘርፉ ያሉ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየትና ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲፈቱ ግፊት ለማድረግ ነው በማለት፣ የ569 ኢንተርፕራይዞች ሐሳብ የተካተተበት ጥናት ተደርጎ ከአሥር የሚበልጡና ለግሉ ዘርፍ ማነቆ የተባሉ ቁልፍ አጀንዳዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት 59.6 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከግብር ማሻሻያና ከጉምሩክ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በችግርነት ማቅረባቸውን፣ በአገር ደረጃ ባለፈው ዓመት የወጣው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017 በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንጋጌዎች መያዙን ገልጸዋል።
ከ30 በመቶ በላይ በሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች በተግዳሮትነት የቀረበው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ነው። ለንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ብድር በቂ አለመሆኑን መግለጻቸው በጥናቱ ተካቷል።
From The Reporter Magazine
የመሬትና የመሥሪያ ቦታ እጥረት ዋነኛ ተብለው ከቀረቡ ተግዳሮቶች አንዱ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቢሮክራሲ እንደሚስተዋልበት ገልጸዋል።
አንድ ንግድ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ መሠረታዊ መሆኑን፣ ሆኖም አሁን ያለው ችግር ዘርፉን እየፈተነው እንደሚገኝ በአብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች ተገልጿል ብለዋል። የመሠረተ ልማት ማለትም እንደ መንገድ፣ ኤሌክትሪክና ውኃ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት በተገዳሮትነት የቀረበ ሲሆን፣ በተለይ አምራች ዘርፉን በጉልህ እየፈተነው መሆኑ በጥናት መለየቱን አቶ ታከለ አብራርተዋል።
የመልካም አስተዳደር መጓደልና የመንግሥት ተቋማት በአንድ ቦታ አገልግሎት መስጠት አለመቻል እንደ ችግር መቅረቡን ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
የጥሬ ዕቃና የተኪ ምርቶች አቅርቦት እጥረት፣ የኢመደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ተጨማሪ ተግዳሮት ተብለው የተለዩ ሲሆኑ፣ በተለይ በስፋት የሚስተዋለውን ሕገወጥ ንግድ መከላከል ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን በተመለከተ በተለይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የትራንስፖርት ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉ በጥናቱ በተግዳሮትነት ቀርቧል። የክህሎት ክፍተት እንደ ችግር የቀረበ አንዱ ጉዳይ ሲሆን፣ የሥልጠና አማራጮችን በማስፋት ያለውን የአቅም ክፍተት እየሞሉ መሄድ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ መቀያየር እንደ ችግር የቀረበ ሌላው ጉዳይ ሲሆን፣ በተለይ በአስመጪዎች ዘንድ ተፅዕኖ መፍጠሩን አቶ ታከለ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ታከለ ገለጻ፣ ምክር ቤቱ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የገቢ ግብር ጉዳይን የተመለከተ ጥልቅ ጥናት አድርጎ ለገንዘብ ሚኒስቴር አስገብቶ ምላሽ እየጠበቀ ነው።
የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችም በጥናት ሰነዱ ቢካተቱ ባሏቸው ጉዳዮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህም የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በየነ ቶሌራ፣ በጦርነት የወደመው ኢኮኖሚ ጉዳይ በጥናቱ ቢካተት ሲሉ አሳስበዋል። በተለይ በጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚያቸው የወደመባቸው አካባቢዎች የተለየ የማገገሚያ ካፒታል የሚያገኙበት ሥርዓትን የሚያመላክት ሐሳብ በጥናቱ ማካተት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የንግድ ማበረታቻ የሚያገኙበት ሥርዓት በጥናቱ ማመላከት ቢቻል ሲሉም ጠይቀዋል። ከኢመደበኛ ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ የሚኖር ሽግግር እንዴት መሆን አለበት የሚለው ጉዳይም በጥናቱ ቢካተት ተብሎ ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል።
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አጋዚ ገብረየሱስ፣ የተሻሻለው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ የአምራች ኢንዱስትሪ ከገበያ እንዲወጣ የሚያደርግ ተግዳሮት ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል። በተለይ የኤክሳይዝና የንብረት ግብር አምራች ዘርፉን የሚያበረታቱ አይደሉም ብለዋል። የኢንሹራንስ ቀረጥ ምጣኔ መጨመሩንና ኮንትሮባንድ ለዘርፉ ትልቅ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ አጋዚ፣ ከላይ የጠቀሷቸው ጉዳዮች በጥናቱ በጥልቀት ሊታዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ቢተው፣ በአገር ደረጃ ያለው ሁኔታ ኢተገማች መሆኑንና ሕጎች በየቀኑ እንደሚወጡ፣ ነጋዴው ተረጋግቶ መሥራት አለመቻሉን ገልጸዋል። በየጊዜው እየወጡ ያሉ ሕጎች በአግባቡ እየተተገበሩ እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ታደሰ ይርዳው፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የሰላምና ፀጥታ ችግር መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። የሰላምና የደኅንነት ዋስትና የሌለባቸው ቦታዎች የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ከባድ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ችግሩ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አዲሱ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የሰላምና ፀጥታ ችግር፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምርቶች እንዳይንቀሳቅሱ ማድረጉን ገልጸዋል። ለአብነት ወደ ወለጋ ይሄድ የነበረ የማሽላና የበቆሎ ምርት በአብዛኛው መቆሙን ተናግረዋል። የግሉ ዘርፍ ጦርነት እንዲቆም የበኩሉን መወጣት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሔለን ረታ፣ ጥናቱ የንግድ ማኅበረሰቡን አላሠራ ያሉ ተግዳሮቶች በአጀንዳነት መለየቱን፣ በእነዚህ ተግዳሮቶች ላይ ሰፋፊ ጥናቶች በማድረግና ምክረ ሐሳቦችን ያካተተ የፖሊሲ ሰነድ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እንዲቀርብና ምክክር ተደርጎበት ምላሽ እንዲገኝ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በአጀንዳነት ከቀረቡ ተግዳሮቶች ሰፊ ጥናት ተደርጎባቸው የሚመረጡት ጉዳዮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት ብሔራዊ የንግድ ኮንፈረንስ ላይ ቀርበው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው እንደሚደረግ አስረድተዋል። ከአገራዊ የቢዝነስ አጀንዳ መድረክ የተገኙ ውጤቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡና ለአገራዊ ኢኮኖሚ መሻሻል የላቀ ሚና እንዲኖራቸው እንዲሠራ የመድረኩ ተሳታፊዎች አሳስበዋል።
