ከዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጋፋሪነት፣ አራት ሺሕ ያህል ተሳታፊዎች በስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች ላይ መምከር ይጀምራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተቀምጠው የሚነጋገሩ የምክክሩ ተሳታፊዎች፣ ከኢትዮጵያ ህልውና በላይ የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡ በቆይታቸውም ለኢትዮጵያ ችግሮች ማብቂያ የሚያግዙ መፍትሔዎች ላይ ያተኩሩ፡፡ የደሃ አገር ከፍተኛ ሀብት ተከስክሶበት ዝግጅት የተደረገበት ምክክር ውጤቱ ሁሉንም ወገኖች እንዲያግባባ፣ በምክክሩ ወቅት የሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦች ኢትዮጵያን ያስቀድሙ፡፡ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ያለያዩን፣ ያቀያየሙንና ያኮራረፉንን ጉዳዮች በመመካከር እንፈታለን›› ተብሎ በአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነሩ የተነገረው ከቃል በላይ በተግባር እንዲገለጽ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበቡ ሥጋቶች ተጠራርገው እንዲወገዱ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ መፍትሔዎች ይፍለቁበት፡፡
የምክክሩ ዋና ዓላማ በፅኑ የታመመች አገርን ለማከም መሆኑን በመገንዘብ፣ ከጎራ ፍላጎቶችና ተፅዕኖዎች ራስን በማላቀቅ እውነተኛ መፍትሔ መፈለግ ይገባል፡፡ ይህ ታሪካዊ ወቅት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ መልካም አጋጣሚዎች ተሰነካክሎ እንዳይወድቅ፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት እጅና እግሯን አስረው ከያዟት ውስብስብ ችግሮች ማላቀቂያ ለማድረግ መትጋት ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እየመከረች ነው›› የሚለውን መሪ ቃል የሚመጥን ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አገር ወዳድነት፣ ቅንነት፣ ለመጪው ትውልድ አሳቢነትና ለዚህች አገር ህልውና ሲሉ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ሲከፍሉ የኖሩ ወገኖችን ጭምር ማሰብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አላባራ ካለው ግጭት ውስጥ መውጣት የምትችለው በቅንነት ለመነጋገር የሚያስችል መግባባት ሲኖር ነው፡፡ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የምታደርገው ጥረት የሚሳካው የጎሪጥ መተያየት ሲያበቃ ነው፡፡ ሰላማዊትና የተረጋጋች አገር ለማቆም ቁርጠኛ ፍላጎት ኖሮ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ተስፋ ይሰንቅ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እየመከረች ነው›› ሲባል የኢትዮጵያ ሕዝብ ምክክሩ በመሠረታዊና በአንገብጋቢ ፍላጎቶቹ ላይ ተመሥርቶ እየተካሄደ መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ ይህ ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰበት ምክክር ውጤታማ ሆኖ ኢትዮጵያን ወደፊት የምትራመድበትን ጥርጊያ እንዲያመቻች፣ ከዚህ በፊት ለሰላምና ለመረጋጋት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በቅጡ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ምክክሩ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው›› የሚለው ሐሳብ በተግባር የሚረጋገጠው፣ ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ፍላጎቶች ከኢትዮጵያ በታች ተደርገው መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ ይህ ታላቅ ጉባዔ በሰከነ መንገድ ተከናውኖ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት ለማምጣት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ ለመቀየር፣ በፖለቲካ ተዋንያን መሀል ለዓመታት የዘለቀውን የከፋ ግንኙነት ለማደስ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ምድር ግጭቶችን ጠራርጎ ለማስወገድ የሚያስችል ውጤት ማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ካለፉት ስህተቶች በመማር ብሩህ ተስፋ ይፈንጥቅ፡፡
እንደሚታወቀው በሁሉም ማዕዘናት የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችላቸውን መንገድ ቢፈልጉ፣ የጠባቸውም ሆነ የግጭታቸው ሰለባ የሆነው ሕዝብ ዕፎይታ ያገኝ ነበር፡፡ አሁንም በዚህ ምክክር አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የፖለቲካ ልሂቃኑ የተበላሸ ፖለቲካዊ ባህል ነው፡፡ የእነሱን ቁርሾና ቂም የሕዝብ አስመስለው መቆመር ማቆም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት ያሉ ልዩነቶችን መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ ተጋብቶና ተዋልዶ ጭምር አብሮ እንደሚኖር የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ድንቅ አብሮነቱ ተከብሮ አገሩ ኢትዮጵያ ከግጭትና ከድህነት ውስጥ እንድትወጣለት ነው ፍላጎቱ፡፡ ምክክሩም ይህንን ማዕከላዊ ነጥብ መሠረት አድርጎ መካሄድ ከተቻለ ውጤቱ የላቀ ይሆናል፡፡ ለዚህም ሲባል በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ በስክነት መነጋገር ተገቢ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያኮሩ ባህሎች መካከል አንዱ በመላ አገሪቱ የሚታወቁ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከበሬታ በተቸራቸው ሰዎች አማካይነት በሚደረጉ ሽምግልናዎች፣ ዕርቅ ከመፍጠርና ተበዳዮችን ከማስካስ አልፈው ለግድያ የሚፈላለጉ ወገኖችን ጭምር በጋብቻ በማዛመድ አስደናቂ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ እንዲህ ዓይነት ምሥጉን ተግባራት ማኅበረሰቦች በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች በሕግ ሳይቀር ዕውቅና እየተሰጣቸው ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ድንቅ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ መመካከር አያቅትም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በቅንነትና በሀቅ ላይ ተመሥርቶ ለመነጋገር ፈቃደኝነቱ መኖሩ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የኢትዮጵያውያንን ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች አብነት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮችም ሆኑ አሁን ያሉት ጭምር በቅደም ተከተል እንዲቀረፉ የጋራ ሐሳብና መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ የጋራ ሐሳብና መንፈስ በሁሉም ውሳኔዎች ላይ ሲንፀባረቅ የኢትዮጵያ ተስፋ ይለመልማል፡፡ ኢትዮጵያ ከግጭት፣ ከውድመት፣ ከመፈናቀል፣ ከዕገታ፣ ከረሃብና ከሌሎች አሉታዊ ገጽታዎች ወደ ብሩህ ተስፋ መሸጋገር ይኖርባታል፡፡ አገራዊ ምክክሩ በተስፋ ላይ ተመሥርቶ ሲካሄድ ውጤቱም አመርቂ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች ተስፋ ያላት አገር እንደሆነች ምንም የሚያጠራጥር ነገር አይኖርም፡፡ ተስፋ እንዲኖራት የሚያስችሉ ተግባራት በጋራ ሲከናወኑ ለመተማመን፣ ለመተባበርና በአንድነት ለመቆም እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡ በተለይ ልሂቃኑ የጎሪጥ ለመተያየት ምክንያት የሆኑ የተዛቡ ትርክቶቻቸውን ወደ ጎን ብለው በጋራ ለአገራቸው ለመቆም ይትጉ፡፡ ተስፋ ያላትን አገር ተስፋ ቢስ እያደረጉ በዓለም ፊት መዘባበቻ አያድርጓት፡፡ አገራዊ ምክክሩም ለኢትዮጵያ ተስፋ እንዲሰንቅ ያግዙ!