የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አሠራር ለመወሰን ከወጣው ሕግ በተቃራኒ፣ የውጭ ዜጋን ወይም ድርጅትን የቤት ባለቤት በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይ ቅጣት የሚጥል መመርያ ወጣ፡፡
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት በፓርላማ የፀደቀው አዋጅ መሠረት፣ የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አሠራር ለመወሰን የሚያገለግል ማስፈጻሚያ መመርያ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡
በመመርያው መሠረት አንድ የውጭ አገር ዜጋ ወይም ድርጅት የሚፈለግበትን ቅድመ ሁኔታ አለመሟላቱን ወይም ፈቃድ አለመሰጠቱን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ወይም የመሥሪያ ቦታ ባለይዞታ እንዲሆን ያደረገ፣ የፈቀደ፣ የረዳ ወይም የተባበረ ማንኛውም ሰው ከ30 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ይቀጣል፡፡
አንድ የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስችል ፈቃድ ከሚኒስቴሩ ለማግኘት የፀና ፓስፖርት፣ ጥያቄው በአካል የሚቀርብ ከሆነ ደግሞ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ቪዛ ለሚያስፈልጋቸው አገሮች ዜጎች የፀና የመግቢያ ቪዛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ ካለ የፀና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ፣ እንደ አስፈላጊነቱ የጤና የምስክር ወረቀት፣ የቱሪስት ወይም የትራንዚት ቪዛ፣ የጉዞ ትኬትና የመዳረሻ አገር ቪዛ ማቅረብ ይጠይቃል፡፡
ፈቃድ ጠያቂው የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን ባንክ ያስገባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ያስመዘገበው ካፒታል ለአንድ መኖሪያ ቤት ብቻ የሚውል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የአንድ መኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በዝቅተኛ ሊያሟላ የሚገባው የገንዘብ መጠን፣ በአዲስ አበባ ከተማና በሸገር ከተማ ከሆነ ቢያንስ 150 ሺሕ ዶላር፣ ሸገር ከተማን ሳይጨምር በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ፣ በሐረሪ ክልሎች ወይም በድሬዳዋ ቢያንስ 120 ሺሕ ብር ዶላር ማስቀመጥ እንዳለበት በመመሪያው ተደንግጓል፡፡
የባለቤትነት ጥያቄው በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወይም በጋምቤላ ክልል ከሆነ ደግሞ ቢያንስ 100 ሺሕ ዶላር እንዲያስቀምጥ የሚስገድድ ሲሆን፣ ገንዘቡ ገቢ የተደረገለት ባንክ በዕለቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን መሠረት ወደ ብር በመቀየር በዝግ ሒሳብ በውጭ አገር ዜጋው ስም ማስቀመጥ አለበት ይላል፡፡
From The Reporter Magazine
የውጭ ዜጋው የመኖሪያ ቤት ሲገዛ ወይም መሬት በሊዝ ጨረታ ሲያገኝ ከተከፈተው ዝግ ሒሳብ ገንዘብ እንዲለቀቅለት የተፈቀደ መሆኑን የሚገልጽ በሚኒስቴሩ የተጻፈ የፈቃድ ደብዳቤ ለባንኩ ሲያቀርብ፣ ባንኩም ገንዘቡ ከዝግ ሒሳብ እንዲለቀቅ እንደሚደርግ መመርያው ያብራራል፡፡
በመንግሥት ቀጥተኛ ድጎማ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት ወይም ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ለትርፍ ላልሆነ ዓላማ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት ወይም በባለሀብት ወይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች በውጭ ዜጎች በባለቤትነት አይያዙም፡ ሲልም ያስረዳል፡፡
የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ ቤቱን ላልተፈቀደ ወይም ለሕገወጥ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ካደረገ እስከ ሦስት ሺሕ ዶላር፣ እንዲሁም ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ሳያገኝ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ወይም መሥሪያ ቦታ ባለይዞታ ሆኖ የተገኘ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ እስከ አምስት ሺሕ ዶላር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡