ትናንት ከምሽቱ 11:42 ሰዓት በኦሪገን በተካሄደው የሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ፍፃሜ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ ወጣቶች ተከታትለው በመግባት የወርቅና ብር ሜዳሊያ አጥልቀዋል። አትሌት አልማዝ ዮሐንስ ርቀቱን 9:15:81 ሰዓት አጠናቃ አንደኛ ሆና የፈጸመች ሲሆን ፤ የገባችበች ሰዓትም የውድድሩ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል።
ወሰኔ አሰፋ ደግሞ በ9:30: 50 ሰዓት ሁለተኛ ሆና የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች፤ የራሷን የአመቱን ምርጥ ሰአትም አስመዝግባለች።
ሻምፒዮናው ዛሬ ቅዳሜ በአኛ ቀን ውሎው ይቀጥልና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉበት ሶስት የፍፃሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ፤ ከሰዓት በኋላ ከ11:10 ጀምሮ በወንዶች 5000 ሜትር የእርምጃ ውድድር ነገሮ አዱኛ፥ ምሽት11:17 ሰዓት ደግሞ በሴቶች 800 ሜትር ፍፃሜ ደራርቱ ሽብሩና ሀብታም ገበየሁ፣ እንዲሁም 11:53 ሰዓት ላይ በሴቶች 3000 ሜትር ሽቶ ጉሚና ዮርዳኖስ ፅጋብ ለፍፃሜ ይሮጣሉ።
እስካሁን ኢትዮጵያ አንድ ወርቅ በአልማዝ ዮሐንስ፣ በ3000 ሜትር ሴቶች መሰናክል፥ ሁለት ብር በወሰኔ አሰፋ 3000 ሜትር መሰናክልና በሴቶች 5000 በሽቶ ጉሚ እንዲሁም አንድ ነሀስ በ5000 ሜትር ወንዶች በዳምጠው ከበደ የተገኘ ሲሆን፣ በጥቅሉ አራት ሜዳሊያዎች ማግኘት ተችሏል።