- በድርቁ 14 ሺሕ የቁም እንስሳት ሞተዋል ተብሏል
- ‹‹ጉዳቱን የሚያጠና ግብረ ኃይል አቋቁመን ወደ አካባቢው ልከናል›› የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ በሚገኙ አሥር ቀበሌዎች በተከሰተ ድርቅ 3,386 ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ወረዳዎች መፈናቀላቸውን የጠለምት ወረዳ አስታወቀ፡፡
ከሚያዝያ ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚገኙ 24 ቀበሌዎች ውስጥ በአሥሩ ዝናብ ባለመጣሉ 3,386 ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ለቀው መሰደዳቸውንና 14,089 የቁም እንስሳት መሞታቸውን፣ የጠለምት ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ እሸቴ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
እርን፣ በተል፣ በስቅያ፣ መረው ብላ፣ መረው ገብርኤል፣ አገጣ፣ ደረባ፣ ከረዋ፣ ነጋዴ መሻገሪያና አተባ የተባሉ ቀበሌዎች፣ እስካሁን ምንም ዝናብ ያላገኙ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አዳነ፣ ሌሎች ስድስት ቀበሌዎች ደግሞ ከሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን እያገኙ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ስምንት ወረዳዎች ዝናብ እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ክቡር አሰፋ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።
በጠለምት ወረዳ ብቻ ሳይሆን በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ድርቅ ያጋጠመ ቢሆንም፣ ከሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በኋላ አንዳንድ ወረዳዎች ዝናብ መጣል መጀመሩን አቶ አዳነ አክለዋል።
በድርቁ ምክንያት በጠለምት ወረዳ ደረሰ የተባለውን ጉዳት አጥንቶ መረጃ የሚያቀርብ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ወደ ወረዳው መላኩን የገለጹት አቶ ክቡር፣ እስካሁን በወረዳው ስለሞቱ እንስሳትም ሆነ ስለተፈናቀሉ ሰዎች የደረሳቸው መረጃ እንደሌለና የተጠና ነገር ባለመኖሩም የጉዳቱን መጠን ከመናገር ተቆጥበዋል።
በሰዎችና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩ በጥናት ከተረጋገጠ፣ መረጃውን መሠረት በማድረግ ከመንግሥትና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዕርዳታ ሊጠየቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።
From The Reporter Magazine
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ይህንን ይበሉ እንጂ የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ግን፣ በአካባቢው ለረዥም ጊዜ አጥጋቢ ዝናብ ባለመጣሉ በየወቅቱ የእንስሳት ሞትና የነዋሪዎች ስደት እንደሚያጋጥም ተናግረዋል።
አሁንም በርካታ እንስሳት በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ አዳነ፣ ከወረዳው በተገኘ የሁለት ሚሊዮን ብር የእንስሳት መድኃኒት መገዛቱን ጠቁመዋል። በአካባቢው ማሽላና ጤፍ በብዛት እንደሚመረት የተናገሩት አቶ አዳነ፣ አርሶ አደሮች በሚያዝያ ወር የተለያዩ ሰብሎችን ዘርተው እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ ባለመጣሉ 9,088 ሔክታር መሬት ሰብል ማብቀል ሳይችል በመቅረቱ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ወረዳው ዜጎችን ከድርቁ ለመታደግ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ነገር ግን ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ አዳነ ጥሪ አቅርበዋል።