- የዲጂታል የታክስ አስተዳደርንና ሌሎች ዕርምጃዎችን ማስፋፋትን እንደ መፍትሔ አስቀምጧል
የአፍሪካ ልማት ባንክ እ.ኤ.አ. የ2026 የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት ላይ እንደገለጸው የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የኡጋንዳና ሩዋንዳ የውጭ ዕዳ ከፍ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የውጭ ዕዳ ከጥቅል አገራዊ ምርት አንፃር እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ 33.9 በመቶ ከፍ ማለቱን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከቀናት በፊት ያወጣው እ.ኤ.አ የ2026 የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያንና የቀጣናውን አገሮች የዕዳ ጫና ከጥቅል አገራዊ ምርት አንፃር፣ የዕዳ አከፋፈል ሁኔታ፣ ለመዋቅራዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ስላላቸው የበጀት ክፍተቶች፣ በሕገወጥ የፋይናንስ ፍሰት ስላጋጠመ ኪሳራ፣ በጀትን በኃላፊነት ጥቅም ላይ የማዋልና ይህንንም ግልጽ ማድረግን ደረጃን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አመልካቾችን ይዟል።
ሰነዱ የምሥራቅ አፍሪካን የዕዳ እንቅስቃሴ ሁኔታና በልማት ፋይናንስ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ የተነተነበት ክፍል እንደሚገልጸው፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የውጭ ዕዳ ከጥቅል አገራዊ ምርት (GDP) አንፃር ሲታይ እ.ኤ.አ በ2024 ከነበረበት 23.8 በመቶ በተከታዩ 2025 ዓመት ወደ 33.8 በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክቷል።
በሪፖርቱ የቀረበው መረጃ የሚያሳየው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የውጭ ዕዳ ጫና በፍጥነት ከጨመረባቸው አገሮች መካከል መሆኗን ያሳያል።
የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጫና በቀጣናው ካሉ ሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር፣ በተመሳሳይ ዓመታት በኬንያ ከፍተኛ የዕዳ ጫና መቀጠሉ ቢገለጽም የውጭ ዕዳዋ ከ69.7 በመቶ ወደ 64.9 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተገልጿል። ጂቡቲ ከጥቅል አገራዊ ምርቷ አንፃር ያለባት የውጭ ዕዳ ጫና በ68.9 በመቶ ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ውስጥ እንደምትገኝም ሪፖርቱ ያብራራል።
በተቃራኒው ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳና ሶማሊያ ዝቅተኛና በመቀነስ ላይ ያሉ የውጭ ዕዳ መጠኖችን አስመዝግበዋል።
From The Reporter Magazine
የአፍሪካ ልማት ባንክ 2026 የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በቀጣናው አብዛኛዎቹ አገሮች የውጭ ዕዳ አገልግሎት ክፍያ ግዴታዎች (Debt Service Obligations) በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ብሏል።
ይህም ጭማሪ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ሁኔታዎች ጥብቅ እየሆኑ መምጣት፣ በብድር ወለድ መናርና አገሮቹ ከቀላል የብድር ምንጮች ይልቅ ወደ ገበያ ተኮር የውጭ ፋይናንስ ምንጮች በመሸጋገራቸው የተከሰተ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት በነበረው እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2019 ከነበረው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር፣ እ.ኤ.አ በ2020 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ውስጥ የቀጣናው መንግሥታት ከሚሰበስቡት ገቢ ውስጥ ለውጭ የመንግሥትና በመንግሥት ዋስትና ለተወሰዱ ብድሮች ክፍያ የሚውለው ድርሻ በአብዛኞቹ አገሮች ከፍ ማለቱንም ጠቁሟል። በተለይ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳና ሩዋንዳ ከፍተኛ ጭማሪ መመዝገቡንም የባንኩ ሰነድ ያሳያል።
From The Reporter Magazine
ሪፖርቱ እንደሚገልጸው፣ ኤርትራና ጂቡቲ በተመሳሳይ ወቅት ዝቅተኛ የዕዳ አገልግሎት ምጣኔ ቢያሳዩም፣ የዕዳ ክፍያ ጫና በአብዛኛው የክልሉ አገሮች ላይ አሁንም ከፍተኛ ሆኖ ቀጥሏል ተብሏል።
የዕዳ ክፍያ ግዴታዎች መጨመር መንግሥታት ለልማታዊ ፕሮጀክቶችና ለመሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሊመድቡት የሚችሉትን የፋይናንስ አቅም እያጠበበ መሆኑንም ሰነዱ ያስገነዝባል።
በመሆኑም የዕዳ አስተዳደርን ማጠናከር፣ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማስፋፋት፣ የካፒታል ገበያን ማጠናከር፣ የመንግሥት ኢንቨስትመንቶችን ቅልጥፍና ማሻሻልና ዝቅተኛ ወለድ ያላቸውንና የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ምንጮችን ቅድሚያ መስጠት የልማት ፋይናንስን በዘላቂነት የዕዳ ክፍያዎችን መፈጸም ጋር በማጣጣም ለመቀጠል ወሳኝ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ሪፖርቱ በተለይ የአገር ውስጥ ገቢ በብቃት ማሰባሰብ፣ የመንግሥት ኩባንያዎች አስተዳደርን ማጠናከርና ሕገወጥ የፋይናንስ ፍሰቶችን መቀነስን እንደ ቁልፍ ዕርምጃዎች ይጠቅሳል።
በሪፖርቱ የቀጣናው አገሮች ዓመታዊ የፋይናንስ ክፍተት ግምት ከጂዲፒ አንፃር በመቶኛ አሥልቶ ያቀረበ ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ ከጂዲፒዋ አንፃር በየዓመቱ 11 በመቶ እስከ 15 በመቶ የሚደርስ የፋይናንስ ክፍተት ሊያጋጥማት እንደሚችል ተተንብዩዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሰነድ ይህን የፋይናንስ ክፍተት ከቀጣናው የኢንቨስትመንት ፍላጎትና ከአገር ውስጥ የቁጠባ አቅም ጋር በማያያዝ ይተነትናል። አያይዞም የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ፣ የግል ካፒታል ተሳትፎን ማሳደግና የረዥም ጊዜ ፋይናንስ ምንጮችን ማስፋፋት ይህን ክፍተት ለመቀነስ ወሳኝ መሆናቸውን ይገልጻል።
ሪፖርቱ የልማት ፋይናንስን የሚያዳክሙ ሌሎች አስፈላጊ ክፍተቶችንም ይጠቅሳል። በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው መረጃ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት በንግድ ዋጋ ማዛባት (Trade Misinvoicing) ምክንያት በድምሩ 24 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት እንዳጣች ያሳያል። ባንኩ ይህንን ሁኔታ እንደ ሕገወጥ የፋይናንስ ፍሰት (Illicit Financial Flows) አካል በመግለጽ፣ እነዚህ ፍሰቶች የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብን እያዳከሙና የመንግሥትን የልማት ፋይናንስ አቅም እየቀነሱ መሆኑን አብራርቷል።
በሪፖርቱ መሠረት የንግድ ዋጋ ማዛባት የታክስ ገቢ ላይ ጫና ከመፍጠር ባሻገር፣ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትንና የመንግሥትን የኢንቨስትመንት አቅም እንደሚጎዳ ጠቅሶ፣ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የፊስካል አወቃቀርና የታክስ አስተዳደር አቅም ልዩነትን ታሳቢ ያደረገ የገቢ ማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ በእያንዳንዱ አገር ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በጥንቃቄ ቅደም ተከተል በመስጠት ሊተገበሩ እንደሚገባቸው ያትታል።
አያይዞም የታክስ ማሻሻያዎች የየአገሮቹን የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተቋማዊ ዝግጁነት፣ የአስተዳደር አቅምና አገራዊ ተግዳሮቶች በመገምገም መተግበር እንዳለባቸው ያመለክታል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛና ፈጣን የገቢ ጭማሪ ሊገኝ የሚችለው አዳዲስ ታክሶችን ከማስተዋወቅ ወይም የታክስ ምጣኔዎችን ከማሳደግ ይልቅ፣ በነባሩ የታክስ ሥርዓት ውስጥ የታክስ አስተዳደርንና የሕግ ተገዥነትን በማሻሻል መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል።
ሪፖርቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዕርምጃዎች ሲልም የዲጂታል የታክስ አስተዳደርን ማስፋፋት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) አሰባሰብንና የደረሰኝ ሥርዓትን ማጠናከር፣ የጉምሩክ የዋጋ ግምገማ ሥርዓቶችን ማሻሻል፣ የግብር እፎይታዎችን መቀነስና በጉምሩክ ባለሥልጣናትና በአገር ውስጥ የታክስ አስተዳደር ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከርን በዝርዝር አስቀምጧል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ 2026 የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት በሌላ በኩል በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር ጥራት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ውስን መሻሻል ብቻ አሳይቷል። ሪፖርቱ ይህ ሁኔታ በቀጣናው የሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር (Public Financial Management –PFM) ሥርዓቶች ውስጥ የሚታዩ መዋቅራዊ ድክመቶች አሁንም እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመላክቷል።
ሰነዱ እንደሚጠቁመው፣ የአገሮች የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር ጥራትን የሚለካው የ Country Policy and Institutional Assessment (CPIA) ውጤት በአገሮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ከዜሮ እስከ ስድስት በሚደርስ ምዘና አብዛኞቹ አገሮች በመካከለኛ ወይም በዝቅተኛ ደረጃ ይገኛሉ ተብሏል።
በውጤቱ መሠረት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ2015 እና በ2024 በሁለቱም የምዘና ጊዜዎች አራት ነጥብ አካባቢ የደረሰ ውጤት በማስመዝገብ በቀጣናው ውስጥ ከፍተኛ አፈጻጸም ካላቸው አገሮች መካከል እንደሚገኙ፣ ኬንያና ኡጋንዳ በ3.5 ነጥብ አካባቢ የተረጋጋ አፈጻጸም እንዳሳዩ በሪፖርቱ ተገልጿል።
በሌላ በኩል፣ ታንዛኒያና ጂቡቲ በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳዩም፣ በቡሩንዲ፣ ኮሞሮስና በተለይም በኤርትራ የታየው ዝቅተኛ አፈጻጸም የቀጣናውን አጠቃላይ ውጤት ደካማ እንዳደረገው ገልጾ፣ የኤርትራ ውጤት ከሁለት ነጥብ ወደ አንድ ነጥብ መውረዱ ጠቁሟል።
ሪፖርቱ አገሮች ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው በበጀት ዝግጅት፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ በሪፖርት አቀራረብና በአፈጻጸም ክትትል ላይ ከፍተኛ ተቋማዊ ድክመቶች መኖራቸውን አመላካች ነው ብሎ፣ በተወሰኑ አገሮች የታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ በቀጣና ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በዘርፉ ሰፊ የሆነ ዕድገት አለመኖሩ በበጀት ዝግጅት፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ በሪፖርት ሥርዓቶችና በተግባራዊ አፈጻጸም ላይ አሁንም ጉልህ ተቋማዊና የአተገባበር ገደቦች እንዳሉ አመላክቷል።