የሥርዓት ለውጥ ከተደረገበት 2010 እስከ 2018 ዓ.ም. የወጡ አብዛኛዎቹ አዋጆች በችኮላና በይድረስ ይድረስ የተዘጋጁ በመሆናቸው፣ ለተደጋጋሚ ማሻሻያዎች መጋለጣቸውንና የአዋጁን ድንጋጌ የጣሱ ደንብና መመርያ እንዲወጡ ምክንያት መሆናቸውን የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ባጠናው ጥናት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ስለተደረገው ጥናት ያስታወቀው፣ የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በ2018 ዓ.ም. ያከናወናቸውን አምስት ጥናቶች ማፀደቂያ ዓውደ ጥናት ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲካሄድ ነው፡፡
የሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋት በኢትዮጵያ በሚል ኢንስቲትዩቱ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ያደረገው ጥናት ግኝት፣ በ2010 ዓ.ም. የተደረገውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የወጡ አብዛኞቹ አዋጆች በችኮላና በይድረስ ይድረስ የተዘጋጁ ስለነበሩ ለተደጋጋሚ ማሻሻያዎች የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቱን ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሙሐመድ ዳውድ (ረዳት ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡
ከ2010 እስከ 2018 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡ ሁሉም አዋጆች በጥናቱ መሸፈናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋትን በተመለከተ አገሪቱ ምንም ዓይነት ፖሊሲ የላትም ተብሏል፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1115/2011 በዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 1173/2012 ተሻሽሎ እንደነበር፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በ2015 ዓ.ም. እንደገና በአዋጅ ቁጥር 1279/2015 መሻሻሉ በጥናት ግኝቱ ተካቷል፡፡ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 በዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 1229/2013 መሻሻሉን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 1287/2015 እንደገና ሌላ ማሻሻያ እንዳረገበት ተገልጿል፡፡
አዋጆች ከበላይ ሕጉ ወይም ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨታቸው መታየቱን የሚያስረዳው የጥናት ግኝት፣ በዚህም ምክንያት አንዲሻሻሉ መደረጉን የሚገልጹት ሙሐመድ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ለምሳሌነት በወንጀል የተገኘ ሀብትን ሕጋዊ ማስመሰልን በተመለከተ፣ የሰብዓዊ መበት ጥሰትን የያዘ ድንጋጌ በመሆኑ ማክሰኞ ወጥቶ በሳምንቱ ማክሰኞ ማሻሻያ የተደረገበት ሒደት አለ፤›› ብለዋል፡፡
በበታች ሕጎች መሻር፣ መሻሻልና ተቃራኒ የበታች ሕጎች መውጣት እንደሚታይ፣ በተለይም የታክስ ሕጎች ላይ ችግሩ በአደገኛ ሁኔታ መስተዋሉን ገልጸዋል፡፡
From The Reporter Magazine
አንድ መመርያና ደንብ ከመውጣቱ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የማይገመገም መሆኑ ችግሩን ማባባሱን፣ የአዋጆች አፈጻጸም ሌላኛው የሕግ አወጣጥ ሥርዓት አለመረጋጋት ዓይነት ሆኖ በጥናት መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋት ጋር በተያያዘ የታዩ ጥንካሬዎች በጥናቱ የተካተቱ ሲሆን፣ አፋኝና አምባገነን ሕጎችን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች፣ ግጭቶችን ለመቀነስና ተቋማትን ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸው፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ የሕጎች ተፈጻሚነትና ክትትል ዳይሬክቶሬት መኖር ይገኙበታል፡፡
በበጀት ዓመቱ 78 ጥናት ይደረግባቸው የተባሉ ርዕሶች ቀርበው እንደነበር፣ ነገር ግን አስፈላጊና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ አምስት ርዕሰ ጉዳዮች ተመርጠው ጥናት እንደተደረገባቸውና ሦስቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ሁለቱ ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
From The Reporter Magazine
ጥናቶቹ የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሒደት በኢትዮጵያ ሕጋዊ መሠረትና የአተገባበር ማዕቀፍ፣ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋት በኢትዮጵያ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም መርሆዎች በኢትዮጵያ፣ የወንጀል ደጋጋሚነትና የማረሚያ ቤት ሚና በኢትዮጰያ የሕግ ማዕቀፍና አተገባበር፣ እንዲሁም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችል የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የሕግ አወጣጥ በኢትዮጵያ የሚሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የሕገ መንግሥት አርቃቂዎች ሕገ መንግሥቱን ሲያዘጋጁ ጠቅለል ያሉ ሐሳቦችን ስለተጠቀሙ አሻሚ ቃላት ስለሚስተዋሉ፣ አልፎ አልፎም የሚጋጩ መርሆዎች ስለሚኖሩ፣ ግልጽነት የጎደላቸው አንቀጾችም ስለሚታዩ፣ ሕገ መንግሥት መተርጎም አለበት በማለት ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም መርሆዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የተካሄደውን ጥናት ያቀረቡት፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ንጉሤ አፈሻ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲተረጉም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ለማድረግና አንቀጾችን ሥራ ላይ ለማዋል በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የማቅረብ መብት ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማት ሲያስረዱ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ባለመብት ወገኖች፣ በአንድ ሦስተኛ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የፌዴራል ወይም የክልል ምክር ቤት አባላትና በፌዴራል ወይም በክልል አስፈጻሚ አካላት ሊቀርቡ እንደሚችል ንጉሤ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከ1991 እስከ 2017 ዓ.ም. ከተቀበላቸው 10‚091 አቤቱታዎች መካከል 7‚377 መዛግብት ዕልባት ማግኘታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 98.64 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም አያስፈልጋቸውም ተብለው ውድቅ ያደረጋቸው መሆኑን የጥናቱ ግኝት ያስረዳል፡፡ ይህም የአጣሪ ጉባዔው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሄዱ የክስ ዓይነቶችን በመግታት በውጤታማነት እያገለገለ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም. የተመዘገቡ 622 የይግባኝ መዛግብት ውስጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ99 በመቶዎች ላይ የአጣሪ ጉባዔውን የሚያፀድቅ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ትርጉም ፍልስፍና የሚቀረፀውና የሚመራው በአጣሪ ጉባዔው የባለሙያ ምርምር ደረጃ ላይ መሆኑ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሆኖም ከመመርያ ክፍተትና ከተገማችነት ማጣት አኳያ ሥርዓቱ የሚመራበት ይፋዊና ወጥ የሆነ የትርጓሜ መርህ አለመኖሩ፣ በሕግ ሥርዓቱ ላይ የተገማችነት ማጣትንና የወጥ አገራዊ የሕግ ፍልስፍና አለማደግ መዋቅራዊ ማነቆ መፍጠሩ በጥናት ግኝቱ ተካቷል፡፡
የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሒደት በኢትዮጵያ ሕጋዊ መደረግና የአተገባበር ማዕቀፍን በሚመለከት በኢንስቲትዩቱ የተደረገውን ጥናት ያቀረቡት በኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ አቶ ኖህ ግርማ፣ ጥናቱ ሒደቱ ቀድሞ በተጀመረባቸው በአዲስ አበባ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ብቻ መደረጉንና በትግራይ ክልል ሒደቱ ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም መረጃ ለመሰብሰብ አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ በጥናቱ ማካተት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡
የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሒደት በአጭር ጊዜ ውስጥ የመዳኘት መብት ጋር በተያያዘ ጥሩ ተሞክሮ ያለው መሆኑን፣ በዚህም በጥናት ከተገመገሙ 712 መዛግብት ውስጥ 378 ጉዳዮች ተከሳሽ ከቀረበ በ30 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘታቸውን፣ 476 ጉዳዮች ደግሞ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡
ሆኖም ከ712 መዛግብት ውስጥ 75.6 በመቶ የሚሆኑት ተከሳሾች ያለ ጠበቃ በሒደቱ ያለፉ መሆናውን፣ የራሳቸውን መከላከያ ማስረጃ ያቀረቡት ደግሞ 31.2 በመቶ ብቻ መሆናቸው በግኝቱ ተመላክቷል፡፡
የወንጀል ተደጋጋሚነትና የማረሚያ ቤት ሚና በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍና አተገባበር ሥርዓት በኢንስቲትዩቱ የተከናወነው ሌላኛው ጥናት ሲሆን፣ ጥናቱ ያስፈለገው የወንጀል ደጋጋሚነትን ለመከላከል የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ መሆኑን ጥናቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ወ/ሪት ቤተልሔም ግዛቸው ገልጸዋል፡፡
በጥናቱ በተሳተፉ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከተደጋጋሚ ታራሚዎች በጽሑፍ መጠይቅ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት 57.9 በመቶ ታራሚዎች አንድ ጊዜ፣ 31 በመቶ ሁለት ጊዜ፣ 8.7 በመቶ ሦስት ጊዜ፣ እንዲሁም 2.4 በመቶ አራት ጊዜ ከዚህ ቀደም በወንጀል ተከሰው የተቀጡ መሆናቸው በጥናት ግኝቱ መካተቱን አብራርተዋል፡፡
ወደ ወንጀል ድርጊት ተመልሰው የገቡበትን ጊዜ በተመለከተ ሲያስረዱ 36.5 በመቶ የሚሆኑት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት፣ 17.5 በመቶ ከስድስት ወራት በታች፣ 23 በመቶ ከስድስት እስከ አንድ ዓመት፣ 17.5 በመቶ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ፣ እንዲሁም 5.6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ነው ብለዋል፡፡
ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ሥራ ለማግኘት መቸገር፣ የገንዘብ ችግርና ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ክትትልና ድጋፍ አለመኖር ታራሚዎች ተመልሰው ወደ ወንጀል ድርጊት እንዲገቡ የሚያደረጋቸው ምክንያት መሆኑ በጥናቱ ተካቷል፡፡
በተጨማሪም ከእስር የመፈቻ ጊዜያቸው የደረሰ ታራሚዎችን ለማዘጋጀት የሚከናወን የቅድመ ዝግጅት ድጋፍ አለመኖርና ከወጡ በኋላ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘት ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
የወንጀል ተደጋጋሚነት ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱና በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው፣ እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪና የሥራ ጫና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል፡፡