‹‹ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠው የቦርዱን መከራከሪያ ሐሳብ ውድቅ በማድረግ ሆኖ ሳለ ፓርቲው ያቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው››
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ በሐረሪ ክልል ያቀረበው ዕጩ እንዲሰረዝና የክልሉ ተወላጅ የሆነን ዕጩ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት የመወሰኑ ምክንያት የምርጫ ቦርድ ደካማ ክርክር መሆኑን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ምላሽ፣ የሐረሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን እንደሌለው ጭምር መከራከሪያ ሐሳብ ቢያቀርብም፣ ፍርድ ቤቱ ባለመቀበል ውድቅ አድርጎ ውሳኔ ሰጥቶ እያለ ኢዜማ ቦርዱ እንዳልተከራከረ አድርጎ ያቀረበው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ‹‹ዴሞክራዊያዊ መብቶች በብሔር ማንነትና በመንግሥት አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ መውደቃቸው ምርጫውን ችግር ውስጥ ይከታል፤›› በሚል ሐሳብ በወቅታዊ የምርጫ ጉዳዮች ላይ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው ትኩረት ያደረገበት፣ በሐረሪ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ዕጩ ሰርዞ፣ የክልሉ ተወላጅ የሆነ ዕጩ እንዲያቀርብ በክልሉ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀልና ፍትሐ ብሔር ችሎት የተወሰነ ሲሆን፣ ፓርቲው በክርክሩ መብቱ የሚነካ ወገን ሆኖ እያለ፣ ነገር ግን ጥሪ እንዳልተደረገለት የፓርቲው መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ሕገ መንግሥት ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ተቃራኒ የሆነ ድንጋጌን ማካተቱንና በዚህም ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ የሚወዳደሩ ዕጩዎች የሐረሪ ብሔረሰብ አባልነትን መሥፈርት አድርጎ ማስቀመጡን፣ ነገር ግን በክልሉ ሕገ መንግሥት ባልተከለከለበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ዕጩ እንዲሰረዝ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው እንዲከራከር ጥሪ ካለመቅረቡ ባለፈ በጉዳዩ ተከራካሪ ሆኖ የቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደካማ ክርክር ለውሳኔው መነሻ ነው ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የመጀመርያ ዕግድ በፍርድ ቤቱ ሲሰጥ በክልሉ ሕገ መንግሥት እንኳን ያልተከለከለ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ተወዳዳሪን እየከለከሉ በመሆኑ፣ ከሕግ አኳያ አግባብ አለመሆኑንና በክርክሩ ተሳታፊ ሆነው ነገር ግን የፓርቲውን ክርክር እንዳላቀረቡ ለቦርዱ መግለጻቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ቦርዱ ክርክር ሳያደርግ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በፀጋ መቀበሉን አቶ ኢዮብ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ፓርቲው ተከራካሪ ወገን ስላልነበር ይግባኝ የማለት መብት ስለሌለው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት፣ ፓርቲው የሚያቀርበውን ክርክር በመስማት ውሳኔውን እንዲሽርላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበው የነበር ቢሆንም፣ መግለጫው በተሰጠ ዕለት ውድቅ እንዲሆንና ውሳኔው እንዲፀና መደረጉ ተመላክቷል፡፡
ጉዳዩን በምርጫ ወቅት ለማስጮህ እንዳልሆነ የገለጹት የፓርቲው መሪ፣ ከዚህ ቀደም በፓርቲው ሲወጡ በነበሩ መግለጫዎች ሲቃወሙ መቆየታቸውን፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን በሚመለከትም ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳነት ማስረከባቸውን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አሁን የተከለከሉት ዕጩ ለክልል ምክር ቤት ሳይሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ መሆኑንና ይህም በሐረሪ ሕገ መንግሥት ጭምር ያልተከለከለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የምርጫ ቦርድም የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለማስፈጸም ‹‹ደምና አጥንት አጣርታችሁ ሐረሪ የሆነ ሰው ለሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አቅርቡ ሲል የሰጠውን ውሳኔ ለመቃወም ነው የቀረብነው፤›› ብለዋል፡፡
በክልሉ ቋንቋ ብቻውን በቂ እንዳልሆነና ደምና አጥንት ጭምር እንደሚቆጠር የገለጹት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋየ፣ ይህ ሁኔታ የአንድ ዕጩ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመርህ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኢዜማ በተጨማሪ ነፃነትና እኩልነት፣ የወሎ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ (ኢሶዴፓ)፣ አዲስ ትውልድና ትብብር ለኢትዮጵያ ዕግዱ የተጣለባቸው ሌሎች ፓርቲዎች መሆናውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ተከትሎ በሕጉ መሠረት በሁሉም ምርጫ ክልሎች የዕጩዎችን ዝርዝር መለጠፉን፣ ይህን ተከትሎ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ጽሑፈት ቤት በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል የተለጠፈው የዕጩዎች ዝርዘርን በሚመለከት ያለውን ቅሬታ ለቦርዱ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ይሁንና የሐረሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1394/2017 እና ቦርዱ ባፀደቀው የዕጩዎች ምዝገባ መመርያ መሠረት፣ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መሰል ጉዳዮችን በራሳቸው ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ስለሌላቸው ለዋናው መሥሪያ ቤት ቀርቦ በመታየት ላይ እያለ፣ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ይግባኙን ለሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረቡን አስረድቷል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ያቀረበው ይግባኝ ላይ ቦርዱ ውሳኔ ለመስጠት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው፣ ፍርድ ቤቱም በሕግ ጉዳዩን ዓይቶ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን የሌለው መሆኑን በመግለጽ በጽሑፍ የተከራከረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ የቦርዱን ምላሽና ክርክር ሳይቀበል ውሳኔ ሰጥቷል ብሏል፡፡
ይህ ሁኔታ ባለበት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ፣ ቦርዱ ጉዳዩን በዚህ አግባብ ይዞ እየተከራከረ ባለበት ሁኔታ፣ እንዳልተከራከረ አድርጎ ያቀረበው መረጃ አግባብነት የሌለው መሆኑን አሳውቋል፡፡
በተጨማሪም የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የሐረሪ ተወላጅ ያልሆኑ ዕጩዎች ቀርበዋል ሲል ቅሬታ ያቀረበባቸው ዕጩዎችን ያቀረቡት ፓርቲዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው በመሆኑ፣ ክርክሩን እንዲያውቁና አስተያየት እንዲሰጡ ቦርዱ በደብዳቤ ቢያሳውቃቸውም፣ ኢዜማን ጨምሮ ቅሬታ የቀረበባቸው ሌሎች ፓርቲዎች መልስ አለመስጠታቸውን ቦርዱ ገልጿል፡፡
ፓርቲው በሰጠው መግለጫ የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዳልሆኑና ለገዥው ፓርቲ ‹‹ዓይን ያወጣ›› ወገንተኝነታቸውን በአደባባይ እያሳዩ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአፋር ክልል ለሁለት ሳምንት በእስር ላይ የነበረ ዕጩ ከቀናት በፊት መለቀቁንና አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አባላት መኖራቸውን አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም ፓርቲው ለሚያቀርባቸው አቤቱታዎች ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ መሆኑን፣ ነገር ግን ቆራጥ የሆነ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ላይ ችግሮች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
የፀጥታ ችግሮች ያሉባቸውን አካባዎች በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው መሪ አቶ ኢዮብ፣ ትጥቅ ባነሱና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት የሚደርስ ጫና መኖሩን ገልጸዋል፡፡
‹‹የመንግሥት መዋቅር ሥልጣኑን ላለመልቀቅ የሚያደርገው ግብግብ እንደተጠበቀ ሆኖ በየአካባቢው ትጥቅ ባነሱና ጠብመንጃ በሚወዘውዙ አካላት በተመሳሳይ፣ እዚህ ምርጫ ውስጥ መካፈል የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍል ውጤት እንደሚኖረው ለተወዳዳሪዎቻችን ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
በዋናነት በአማራ ክልል በጣም ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ ከታጣቂ ኃይሉም ከመንግሥት መዋቅርም በኩል በአባሎቻቸውና ዕጩዎቻቸው ላይ እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡
