የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ የፌደራልና የክልል መንግስታዊ ተቋማት ዝግ ሆነው እንዲውሉ ጥያቄ አቅርቧል።
ቦርዱ ለአገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ በዕለቱ ድምፃቸውን ለመስጠት እንዲችሉና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/ 2011 አንቀጽ 161 መሠረት ለመንግሥታዊና ለማንኛውም መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ ማሳወቁን ገልጿል።
ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊ ተቋማት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ሥራ ዝግ እንዲያደርጉ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ ዝግ እንዲያደርጉ ዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2018ዓም አሳውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪዎች (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንዲዘጉ እንደማያስገድድ ገልጿል።
የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም፤ ዜጎች ድምፅ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችን፣ ዕቅዶችን እንዳይይዙና እንቅስቃሴያቸውን ድምፅ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ መክሯል።
