- በአፍሪካ 565 ሚሊዮን ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም ተብሏል
ኬንያ ከምትጠቀመው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 13.4 በመቶ የሚሆነውን ያገኘችው ከኢትዮጵያ መሆኑ በሪፖርት ተመላከተ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው እ.ኤ.አ. የ2026 ዓመታዊ የልማት ውጤታማነት ግምገማ ሪፖርት (Annual Development Effectiveness Review)፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ቀጣናዊ የኃይል አቅራቢ አገሮች መካከል አንዷ እየሆነች መምጣቷን በመግለጽ፣ በሌላ በኩል አኅጉሪቱ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ጠቁሟል።
እንደ ሪፖርቱ ማብራሪያ፣ ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2024 ከተጠቀመችው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 13.4 በመቶ የሚሆነውን ከኢትዮጵያ የተላለፈ መሆኑ ታውቋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት አገሮች የኃይል ወጪን ለመቀነስ፣ አስተማማኝነቱን ለማሻሻልና ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋቶቻቸውን ለማረጋጋት (Stabilize National Grids) ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት በስፋት መጠቀም በመጀመራቸው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር እየተፋጠነ መሆኑን ያሳያል።
በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ የኃይል ትስስር ፕሮጀክቶች በአኅጉሪቱ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ኢኒሼቲቮች (Initiatives) መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሲሆን፣ በተለይም ለኬንያና ለጂቡቲ የሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል በምሳሌነት ተቀምጧል።
እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፣ የኢትዮ-ጂቡቲ የኃይል ትስስር የጂቡቲን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ወጪ በ60 በመቶ፣ ታሪፍን ደግሞ በ24 በመቶ ዝቅ አድርጓል። በተጨማሪም የጂቡቲን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀምን በ170 በመቶ ያሳደገ መሆኑን፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነትን ደግሞ በ65 በመቶ ማስፋቱ በሪፖርቱ ተገልጿል። ይህ በአገሮቹ መካከል ያለ የኃይል ትስስር በየዓመቱ ከ143 እስከ 274 ኪሎ ቶን የሚመዝን የካርቦን ዳይኦክሳይድ አቻ የሚሆን መጠን ያለው (Carbon Dioxide Equivalent) የበካይ ጋዝ ልቀትን ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአኅጉሪቱን እየሰፋ የመጣ የኃይል እጥረት ለመቅረፍና የኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል የአኅጉራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን እንደ ዋና ስትራቴጂ አድርጎ እየተንቀሳቀስ መሆኑን የሚጠቁመው ሪፖርት፣ ምንም እንኳን የኃይል ፍላጎትና ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት እየታየ ቢሆንም የተበታተኑ የብሔራዊ ኃይል አቅርቦት ሥርዓቶች (Systems) እና ደካማ የድንበር ተሻጋሪ የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች፣ የአፍሪካን የኢነርጂ ሀብቶች በአግባቡና በበቂ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አሁንም እያደናቀፉ ይገኛሉ ብሏል።
From The Reporter Magazine
ቀጣናዊ የኃይል ትስስር አገሮቹ ያላቸውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ፣ ወጪን እንዲቀንሱ፣ የኃይል አቅርቦት ሥርዓታቸውን ጥንካሬ እንዲያሻሽሉና ውድ በሆነ የአስቸኳይ ጊዜ የኃይል ማመንጫ (Expensive Emergency Power Generation) ዘዴዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲቀንሱ እንደሚያስችላቸው የባንኩ ሪፖርት ገልጿል።
ሪፖርቱ እንደሚጠቁመው፣ በምሥራቅ አፍሪካ የድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ንግድ እ.ኤ.አ. በ2010 ከነበረበት በሰዓት 280 ጊጋ ዋት (Gigawatt Hours) እ.ኤ.አ. በ2023 ወደ በሰዓት 3,217 ጊጋ ዋት አድርጓል። በተመሳሳይ የቀጣናው የኃይል ማስተላለፊያ መረብ (Transmission Network) እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ303 ኪሎ ሜትር ወደ 2,753 ኪሎ ሜትር ስፋት ወደ መሸፈን መሸጋገሩም ተብራርቷል።
ለአኅጉሪቱ የወደፊት የጋራ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ መሠረት የሚሆኑ አምስት ቀጣናዊ የኃይል ጥምረቶችን (Regional Power Pools) ሪፖርቱ ለይቶ አስቀምጧል።
From The Reporter Magazine
በዚህም አገሮች የታዳሽ ኃይል ሲስተሞቻቸውን ሚዛን ለማስጠበቅ፣ ድንገተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቶችን ለመቋቋምና የአቅርቦት አለመረጋጋትን ለመቅረፍ በሚጥሩበት በዚህ ወቅት፣ ቀጣናዊ ትስስር ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ እየሆነ መምጣቱንም ገልጿል። ይሁንና እነዚህ መሻሻሎች ቢመዘገቡም፣ የአፍሪካ አጠቃላይ የኃይል አቅርቦት ቀውስ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ሪፖርቱ በጥብቅ አሳስቧል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በዓለም ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከሌላቸው አጠቃላይ ሕዝቦች ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ2010 ከነበረበት 50 በመቶ አሁን ላይ ወደ 85 በመቶ ከፍ ብሏል። እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ ወደ 565 ሚሊዮን የሚጠጋ የአኅጉሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዳላገኘ መመዝገቡም ተጠቁሟል። በአኅጉር ደረጃ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በ2020 ከነበረበት 56 በመቶ በ2023 ወደ 60 በመቶ ቢያድግም፣ የባንኩ ሪፖርት ግን ይህ የታየው መሻሻል ከዕለት ወደ ዕለት ከሚጨምረው የኃይል ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን የቻለ አይደለም ብሏል።
ሪፖርቱ ለዚህ አዝጋሚ መሻሻል እንደ ዋና ምክንያት የጠቀሳቸው የተበታተኑ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ መረቦችን፣ ውስን ቀጣናዊ ትስስርንና ደካማ የኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓቶችን ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ አፍሪካ በዓለም ላይ ገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ እጅግ ግዙፍ የኃይል ክምችቶች ካሏቸው አኅጉራት አንዷ መሆኗን ሪፖርቱ ያሳያል። የአፍሪካን የፀሐይ ኃይል እምቅ አቅም 10,000 ጊጋ ዋት እንደሆነ የሚገምት ሲሆን፣ ይህም ቻይናና አሜሪካ በጥምረት በአሁን ወቅት ካላቸው በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም በላይ መሆኑን አመላክቷል። ሆኖም ከዚህ ዕምቅ አቅም ውስጥ እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ ነው ብሏል።
በተጨማሪም አኅጉሪቱ በግምት 350 ጊጋ ዋት የውኃ ኃይል (Hydropower)፣ 110 ጊጋ ዋት የንፋስ ኃይል እና 15 ጊጋዋት የጂኦተርማል (የእንፋሎት) ኃይል ዕምቅ አቅም እንዳላት የተጠቆመ ሲሆን፣ ከዚህም በላይ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተረጋገጠው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ውስጥ ከሰባት በመቶ በላይ ድርሻ ያላት እንደሆነ፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2018 ባለ ጊዜ ውስጥ ከተመዘገቡ ዋና ዋና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መገኛ ቦታዎች መካከል ሞዛምቢክ፣ ግብፅ፣ ታንዛኒያ፣ ናሚቢያና ኮትዲቯር እንደሚገኙበት ተብራርቷል።
ይሁንና በደካማ ቀጣናዊ መሠረተ ልማትና ውስን የኤሌክትሪክ ግብይት ሥርዓቶች ምክንያት እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በእኩልነት ያልተከፋፈሉ፣ የኃይል ምንጮቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች በበቂ ሁኔታ ለምተው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ካላቸው ማዕከላት ጋር በአግባቡ ያልተገናኙ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያሳያል።
እ.ኤ.አ. በ2024 በአፍሪካ አኅጉር የተመዘገበው የማስተላለፊያና የኃይል ሥርጭት ኪሳራ (Transmission and Distribution Losses) አጠቃላይ ከተመረተው ኃይል ውስጥ 15 በመቶ መድረሱን፣ ይህም በተበታተኑ ብሔራዊ የኃይል ሥርዓቶች ውስጥ ያለውን የአሠራር ብቃት ማነስ ያንፀባርቃል ተብሏል።
ይሁን እንጂ የአፍሪካ ልማት ባንክ እርስ በርስ የተሳሰሩ ቀጣናዊ የኃይል ሥርዓቶችን ማስፋፋት ከመሠረተ ልማት ወጪ መቀነስ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ የኃይል ማመንጫ ወጪዎች መቆጠብና እያደገ ከሚመጣ ቀልጣፋ ከሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ንግድ ጋር ተዳምሮ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2030 ባሉት ዓመታት ውስጥ በምዕራብ አፍሪካ እስከ 32 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ እስከ 18.6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል በሪፖርቱ ጠቁሟል።
