በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የሚደረግለት በሚድል ኢስት ብሮድካስት ኔትወርክ (MBN) ሥር የሚተዳደረው አልሁራ (Alhurra) የዜና ምንጭ እንደዘገበው የግብፅ ጦር ከሰሞኑ ከደቡብ ሱዳን ነቅሎ ወጥቷል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የግብፅ ጦር ከግዛቷ ለቆ እንዲወጣ ጠይቃ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ግብፅ 260 ወታደሮቿ የሠፈሩበትንና የጦር ትጥቅ ያከማቸበትን በደቡብ ሱዳን ግዛት ከፍታው የነበረውን የጦር ሠፈር፣ ብዙም ኮሽታ ሳታሰማ ዘግታ መውጣቷ ነው የተዘገበው፡፡
የግብፅ ወታደራዊ ሠፈር፣ የተገነባው ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትጎራበት አፐር ናይል (Upper Nile) ግዛት ነው፡፡ ፓጀክ በተባለ አካባቢ ለኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር ቀርቦ የተሠራው የጦር ሠፈሩ፣ የግብፅ የጂኦ ፖለቲካ ተፅዕኖ ማሳረፊያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ለኢትዮጵያው ግዙፍ የውኃ ኃይል ማመንጫ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቀረበ አካባቢ የተሠራው የግብፅ የጦር ሠፈር፣ በዋናነት ኢትዮጵያን በተፅዕኖ ውስጥ የመክተት ግብ እንደነበረው ተዘግቧል፡፡ የህዳሴ ግድብ መገንባትን እስካሁንም እየተቃወመች ያለችውና በዓባይ ተፋሰስ ውኃ አጠቃቀም ጉዳይ የዘመናት የበላይነቷን ማስቀጠል የምታልመው ግብፅ፣ በኢትዮጵያ ዙሪያ ባሉ አገሮች ወታደራዊ መስፋፋት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከብዙዎቹ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጋር የጦር ትብብር ስምምነት ስትፈራረም የቆየችው ግብፅ፣ በአንዳንዶቹ የጦር ሠፈሮች ከመገንባት አልፋ ጦር እስከማስፈር መድረሷ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም ግብፅ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑም ብዙ የተባለበት ነው፡፡


የአልሁራ የዜና ምንጭ የውስጥ መረጃ ምንጮቼ አረጋግጠውልኛል ብሎ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ፣ ግብፅ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ጥያቄና ግፊት ነው የፓጀክ ወታደራዊ የጦር ሠፈሯን ዘግታ ለመውጣት የተገደደችው፡፡ ይህን ደግሞ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ ከተፈጠሩ የፖለቲካ ለውጦች ጋር ተንታኞች እንደሚያገኙት ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
ግብፅ የሦስቱ አገሮች መጋጠሚያ በሆነ ቀጣና ውስጥ ነው ይህንን የጦር ሠፈር የመሠረተችው የሚለው ዘገባው፣ እጅግ ቁልፍ የብሔራዊ ደኅንነቴ ጉዳይ ነው የምትለውን የዓባይ ተፋሰስ ጉዳይን በቅርበት ለመከታተል የጦር ሠፈሩ ሲያግዛት መቆየቱን ያትታል፡፡
ለዘገባው ሐሳብ በማጋራት የተጠቀሱት የቀድሞ የግብፅ ረዳት የውጭ ግንኙነት ሚኒስትር ፎውዚ አሸማዊ፣ የፓጀኩ የጦር ሠፈር መዘጋት ግብፅ በቀጣናው የነበራትን በቅርበት አካባቢውን የመቃኘት ዕድል እንደሚያሳጣት ጠቁመዋል፡፡
የጦር ሠፈሩ መዘጋት ለደቡብ ሱዳን ምን አንድምታ እንዳለው የሚያጠያይቀው ዘገባው፣ ውሳኔው የመጣው በአራት መሠረታዊ ጉዳዮች ለውጥ የተነሳ መሆኑን አመልክቷል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣን ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2024 ማብቂያ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperative Framework Agreement-ICFA) የሚባለውን ስምምነት መፈረሟ መሠረታዊ ለውጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን ይህን ስምምነት መቀላቀሏ ግብፅ ፀንቶ እንዲኖር የምትፈልገውን የቅኝ ግዛት የውኃ ክፍፍል ሁሉንም የተፋሰሱን አገሮች ባማከለ በአዲስ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ስምምነት እንዲተካ ወደ መፈለግ መሸጋገሯን ጉዳዩ እንደሚያመለክት ይጠቁሟል፡፡
በሁለተኝነት ደግሞ የደቡብ ሱዳን የግል ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ጭምር የጦር ሠፈሩ እንዲዘጋ ያስገደደ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ደቡብ ሱዳን በሰሜን ሱዳን ያለው ጦርነት መተንፈሻ አሳጥቷታል ይላል፡፡ መውጫ መግቢያ በር አዘግቶባታል ሲልም ያክላል የነዳጅ ዘይት ምርት ወደ ፖርት ሱዳን የምታደርስበት የነዳጅ ቧምቧ አደጋ ላይ ወድቋል፣ ወይም ተቋርጧል በማለት፣ ይህንን የመተካት ፍላጎት ያላት ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን አቋርጦ የሚያልፍ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ መስመር እንዲኖራት እንደምትፈልግ ነው ያመለከተው፡፡
From The Reporter Magazine
በሦስተኝነትም ዘገባው ባለሥልጣኑ አክለው ነገሩኝ ብሎ እንደከተበው፣ ደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ተጋግሎ የቀጠለው የሱዳን ጦርነት እሳቱ እንዲመጣባት አትፈልግም፡፡ ደቡብ ሱዳን በሱዳን ውስጥ የሚካሄደው የውጭ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት የበዛበት ጦርነትና ግጭት ድንበር ተሻግሮ እንዲመጣባት አትሻም ይላል፡፡ በሱዳን ጎራ ለይቶ የሚደረገው ጦርነት፣ የድሮን ጥቃትም ሆነ ሰብዓዊ ቀውስና የተፈጥሮ ሀብት ቅርምት ደቡብ ሱዳን እንዲመጣባት እንደማትፈልግ፣ በተለይ ሱዳን እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገሮች ጋር እየፈጠረች ያለችው አለመግባባትና ውጥረትም እንዲደርስባት እንደማትሻ፣ ደቡብ ሱዳን በውስጥ ያለባት የፖለቲካ ምስቅልቅል፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አለመረጋጋት ሳያንስ የቀጣናው አገሮችን ሽኩቻና ግጭት በግዛቷ ለማስተናገድ እንደማትፈልግ ባለሥልጣኑ መናገራቸውን ዘገባው ያትታል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የደቡብ ሱዳንን ውስጣዊ የፖለቲካ ምስቅልቅልን ያቀረበው ዘገባው፣ ደቡብ ሱዳን የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ እንደተሳናት ይጠቁማል፡፡ ምርጫ ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ከያዘች የቆየ ቢሆንም ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቷል ይላል፡፡ ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ዋነኛ ተቃዋሚዎቻቸው በሪክ ማቻር፣ እንዲሁም በታባንግ ዴንግ የሚመሩ ኃይሎችን በሰላምም ሆነ በኃይል አደብ ማስገዛት አቅቷቸዋል ብሏል፡፡
የቀድሞ ምክትላቸውን ሪክ ማቻርን በጁባ የቁም እስራት ውስጥ እያኖሩ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ካለፈው ወር ጀምሮ ግን መንግሥታቸው በጆንግሌ ግዛት ከሪክ ማቻር ሠራዊት ጋር ከባድ ውጊያ ውስጥ መግባቱ ይነገራል፡፡ የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፣ በጆንግሌ ግዛት ገና ያልበረደው ግጭት የአገሪቱን ሰብዓዊ ቀውስ አክፍቶታል፡፡ በትንሹ ስምንት ሚሊዮን ወይም 56 በመቶ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ለረሃብና ለአስከፊ የምግብ እጥረት ተጋልጧል፡፡ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) በአጭር ጊዜ ከ330 ሺሕ በላይ ሰዎች በጦርነት መዘዝ ተፈናቅለዋል፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ከ97 ሺሕ በላይ ሰዎች በጆንግሌ ግጭት መዘዝ ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ሲሆን፣ ዕርዳታ በፍጥነት መቅረብ ካልቻለና ግጭቱ ካልቆመ ደግሞ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ረሃብ አደጋ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡ አልጄዚራ የተመድ ሕፃናት አድን ድርጅትን (UNICEF) ጠቅሶ ሁለት ሚሊዮን ሕፃናት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የዘገበ ሲሆን፣ ዕርዳታ በፍጥነት ካልቀረበ 700 ሺሕ የሚሆኑት በአጭር ጊዜ በረሃብ አደጋ ሊሞቱ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡
From The Reporter Magazine
ደቡብ ሱዳን ይህ ሁሉ ሳያንስ በሱዳን ጦርነት መዘዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞችን ለመቀበል ተገዳለች፡፡ በሱዳን ጦርነት መዘዝ ዋና የገቢ ምንጯ የሆነውን ነዳጅ ዘይት ለዓለም ገበያ ማቅረብም አልቻለችም፡፡ ከፍተኛ የውጭ ብድር ናዳ ተቆልሎባታል የምትባለው ደቡብ ሱዳን ለኢኮኖሚ ቀውስም የተዳረገች አገር መሆኗን በርካቶች ዘግበውታል፡፡ ይህ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ቀውስ የተጫናት ደቡብ ሱዳን አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮችን ለማማተርና የአካሄድ ለውጦችን ለማድረግ መገደዷ ይነገራል፡፡
ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ የሚያነሳው የአልሁራ ዘገባም ቢሆን፣ ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፍና ከባህር በር ጋር የምትገናኝበት አዲስ የንግድ ኮሪደር መፍጠር የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነባት ነው የሚጠቅሰው፡፡ በተለይ የጋምቤላ-ፓጆክ-ፍሎጅ የንግድ ኮሪደር በደቡብ ሱዳን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል ይላል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ነዳጅ ማውጫ ቦታዎች ተነስቶ በኢትዮጵያ ድንበር የሚያልፍ የንግድ ኮሪደር ነው ለመፍጠር ጥረት ላይ ነች፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ፖሊሲና ግንኙነት መቀየር የሚያስገድድ በመሆኑ ነው የግብፅ ጦርን ከአገሯ ያባረረችው ተብሏል፡፡
ለአልሁራ ሐሳባቸውን ያጋሩት የግብፅ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ፋውዚ አሽማዊ እንደተናገሩት ከሆነ ግን፣ ግብፅ ከደቡብ ሱዳን መባረሯ ብቻውን አገሪቱን አደብ አያስገዛትም፡፡ ካይሮ የዓባይ ውኃ ፍሰትን ለመለካት ከምትችልበት ለህዳሴ ግድብ ቅርብ ከሆነው ከፓጆክ የጦር ሠፈሯን ዘግታ እንድትወጣ መደረጉ ኪሳራ ቢሆንም፣ ነገር ግን ደግሞ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን ፖሊሲዋን ሙሉ ለሙሉ አያሰናክለውም ብለዋል፡፡
‹‹የካይሮ ኢትዮጵያን በመክበብና በመነጠል ላይ ያተኮረው መሠረታዊ ፖሊሲ ሰፊ አድማስ ያለው እንጂ፣ ደቡብ ሱዳንን ብቻ መረማመጃ ያደረገ አይደለም፡፡ የግብፅ ኢትዮጵያን ዒላማ ያደረገው ፖሊሲ ሱዳንንም ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን በሙሉ መገልገያ ያደረገ ጭምር ነው፤›› በማለት የቀድሞው ባለሥልጣን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ግብፅ የዓባይ ውኃ እንዳይነካ ለማድረግ በደቡብ ሱዳንና ሱዳንን በመሳሰሉ አገሮች ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በማካሄድ የላይኞቹን የተፋሰስ አገሮች ስትጫን ኖራለች፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ከባህር ጋር እንዳትገናኝና የባህር በር ጥያቄዋ መልስ እንዳያገኝ ለማድረግ የቀጣናው አገሮችን ከመገልገል ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች ጭምር የማከላከል ሥራ እንደምታከናውን ባለሥልጣኑ አስረድተዋል፡፡
የሶማሊያ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሰላም ለማስከበር በሚል ጣልቃ የምትገባው፣ ከኤርትራ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመፍጠር የምትሠራው፣ እንዲሁም የሱዳን ሠራዊትን ደግፋ በሱዳን ጦርነት የምትሳተፈው የዓባይ ተፋሰስ ዋና ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት እንደሆነ የቀድሞው ምክትል ሚኒስትር አጋልጠዋል፡፡ ግብፅ በደቡብ ሱዳን ፓጆክ የነበራት ወታደራዊ ሠፈር መዘጋቱና ጦር ማስወጣቷ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው አጋጣሚ ቢሆንም እንኳን፣ በቀድሞው የግብፅ ባለሥልጣን እምነት ካይሮ በሌሎች ግንባሮች ኢትዮጵያን ለመጉዳት መንቀሳቀሷ ግን አይቆምም፡፡ ግብፅ በዚህ ቢዘጋባት በሶማሊያ፣ በጂቡቲ፣ በኤርትራ፣ በሱዳን ወይም በኡጋንዳ በኩል የተለያዩ አጋርነቶችን በመፍጠር ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴዋን እንደማታቆም ነው አልሁራ የዜና ምንጭ የዘረዘረው፡፡
ባለፈው ሳምንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው (አምባሳደር)፣ ስለግብፅ እንቅስቃሴና ስለቀጣናዊ የጂኦ ፖለቲካ ውጥረቶች ተጠይቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ግብፅ በቀጣናው የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ኢትዮጵያን የመክበብ ዓላማ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሰከነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው የምትመራው፡፡ የባህር በር ጉዳይ ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስማማበት ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ መፃዒ የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ጋር የተሳሰረ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በሌሎችም አገሮች ዘንድ ጭምር የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሕጋዊና አግባብነት ያለው መሆኑ ጭምር በጎ ምላሽ እየተሰጠው ያለ ጉዳይ ነው፤›› በማለት የተናገሩት ነቢያት (አምባሳደር)፣ የግብፅ መንግሥት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ የኤርትራ መንግሥትም ሆነ የሱዳን ጦር ለሚያሰሙት ክሶች የኢትዮጵያ ምላሽ የሰከነ ዲፕሎማሲን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ድረ ገጽ ላይ፣ ‹‹Egypt’s Encirclement Arc: Ethiopia’s Strategic Posture in the Nile-to-Red-Sea Theatre›› በሚል ርዕስ የተነበበው የምሕረት ዘለቀ ሰፊ ሀተታም ቢሆን፣ ግብፅ በኢትዮጵያ ዙሪያ በምን መንገድ ስታንጃብብ እንደኖረች ያብራራል፡፡ የሱዳን ጦርነት፣ የደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት፣ የኤርትራ ግብዣም ሆነ የሶማሊያ ቅሬታ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዙሪያ ባሉ አገሮች ምንም ዓይነት አጋጣሚ ቢከሰት፣ ካይሮ ለፀረ ኢትዮጵያ ፖሊሲዋ ማስፈጸሚያ ልታደርገው የማትፈልገው ዓይነት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ ለውጥ አለመኖሩን ይኸው ትንተና በሰፊው ይጠቁማል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 ነሐሴ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር የተፈራረመችው ግብፅ በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት በማዋጣት እንድትሳተፍ በር ተከፈተላት ይላል፡፡ በዚያው ዓመትና በ2025 ደግሞ ከኤርትራ ጋር በመሪዎችና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር የኢትዮጵያን የባህር በር ማግኘት ፍላጎት የሚያደናቅፍ አጋርነት ስትፈጥርም ታይታለች በማለት ያስታውሳል፡፡ በሌላ በኩል የሱዳን ጦርን በቀጥታ በመደገፍ በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፈች መሆኗን፣ ይህ ጦርነትም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በቀረበ አካባቢ ጦር ለማስጠጋት እንደሚጠቅማት በማሰብ ነው የምትንቀሳቀሰው ሲል ያክላል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎቿ በተጨማሪ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በመሆን የምታንቀሳቅሰውን የቀይ ባህር ተጋሪ አገሮች ማኅበር በመጠቀም፣ ኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባህር እንዳትቀርብ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየሠራች ነው በማለት ያስረዳል፡፡
ይህን ሁሉ በመዘርዘር የግብፅ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ በኩል በምን መንገድ መታየት እንዳለበት ለማስቀመጥ የሞከረው ሀተታው፣ ጉዳዩን ‹‹የግብፅ ኢትዮጵያን የመክበብ ፖሊሲ ሊባል ይችላል፤›› ሲል ነው የሚገልጸው፡፡ ግብፅ ‹‹ከዓባይ እስከ ቀይ ባህር ባለው ቀጣና ኢትዮጵያን ከቦ የማስቀረት›› ፖሊሲ አላት የሚለው ይህ ትንተና፣ ሁለቱንም እንዳትጠቀም ለማድረግ ስትል በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገሮችን በሙሉ ለመጠቀም እንደምትሞክር ነው ያብራራው፡፡
