ሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመዘገብ ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ወደ ጎንደር ጉዞ የጀመረችው የሪፖርተር ሚዲያ ዘጋቢ፣ በአዲስ አበባ ይታይ የነበረው የመቀዛቀዝ ስሜት በጎንደር ከተማም ተቀብሏታል።
ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ባሉት መንገዶችና አደባባዮች ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት ያቀረባቸው ዕጩዎችና የፓርቲውን የመወዳደሪያ ምልክቶች ከያዙ ባነሮች ውጪ፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን የሚያሳዩ አንድም ባነር አልነበረም።
የፀጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ቁጥር ይታዩ የነበረ ሲሆን፣ በተለይም በዋና ዋና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የምርጫ ጣቢያዎች አቅራቢያ በብዛት ነበሩ።
ሁለት የምርጫ ክልልና 240 የምርጫ ጣቢያዎች ያሏት የጎንደር ከተማ፣ በምርጫው ዋዜማ ዕለት የምርጫ ቁሳቁስ ከዋናው የማከማቻ ቦታ ወደ ሁለቱም የምርጫ ክልሎችና በኋላም ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ እስከ ምሽቱ 11 ሰዓት ተሠራጭቶ መጠናቀቁ ተገልጿል።


የወትሮው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እስከ 10 ሰዓት ድረስ የተለመደ ዓይነት የነበረ ቢሆንም፣ ከ10፡00 ሰዓት ጀምሮ ግን የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ማቆማቸውንና የንግድ ሱቆችም በአብዛኛው ዝግ እንደነበሩ ተመልክተናል።
በዋዜማው ከምሽት ጀምሮ የፀጥታ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንደነበር ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች የተረዳ ሲሆን፣ ምንም እንኳን የምርጫ ሒደቱን የሚያደናቅፍ የፀጥታ ችግር ባይከሰትም በከተማዋ ዙሪያ ግን የተኩስ ድምፅ በዋዜማው ምሽት መሰማቱን ከነዋሪዎች ማረጋገጥ ተችሏል።
በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለድምፅ መስጫ ቀን በተያዘው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎችን የሪፖርተር ዘጋቢ ተዘዋውራ እንደተመለከተችው፣ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አስፈጻሚዎች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም፣ በከተማዋ ምንም ዓይነት የሰዎች እንቅስቃሴ አልነበረም።
From The Reporter Magazine
ከ12 ሰዓት ጀምሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች በምርጫ ጣቢያዎች የተገኙ ሲሆን፣ እስከ ረፋዱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ቁጥራቸው እየጨመረና ሠልፎች መታየት መጀመራቸውን ተመልክተናል።


ተዘዋውረን በተመለከትናቸው የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሒደቱ 12፡00 ሰዓት መጀመሩን የተመለከትን ሲሆን፣ በአብዛኛዎቹ ምርጫ ጣቢያዎች ይታዩ የነበሩት መራጮች አብዛኞቹ ሴቶች እንደነበሩ ተመልክተናል። ከምርጫ ቦርድ ባጅ ከተሰጣቸው የውጭ ታዛቢዎች ውጪ የአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ ታዛቢዎችም ፈቃድ መውሰዳቸው ቢታወቅም፣ በተመለከትናቸው የምርጫ ጣቢያዎች ግን ከሁለቱ ተቋማት የተወከለ ታዛቢ ማግኘት አልቻልንም።
ሆኖም ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን አረጋግጠናል።
From The Reporter Magazine
በግራር ሠፈር ምርጫ ጣቢያ የብልፅግናና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲን በመወከል የምርጫ ሒደቱን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ታዛቢዎች፣ ምርጫው ሰላማዊና የዜጎችን መብት ባከበረ መንገድ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። ድምፅ የመስጠት ሒደቱ ከመጀመሩ በፊት የድምፅ መስጫ ሳጥኑን ጨምሮ ሁሉንም የምርጫ ቁሳቁሶች መራጮች ጭምር እንዲመለከቱት መደረጉን ተናግረዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን፣ መራጮችም ከ12፡00 ሰዓት ጀምረው መምጣታቸውን ገልጸው፣ የገጠማቸው ችግር እንደሌለ አስረድተዋል።
ሆኖም ሪፖርተር በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ለረዥም ሰዓታት በመጠበቃቸው ቅሬታቸውን በግልጽ ሲያሰሙ ተመልክቷል። ለአብነትም በምርጫ ክልል ሁለት የሸዋበር ቀበሌ የሴቶች ወፍጮ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ የመስጠት ሒደቱ ለ30 ደቂቃ ዘግይቶ መጀመሩን በቦታው የተገኙ መራጮችም ሲጠይቁ ነበር።
1,501 መራጮች በተመዘገቡበት 16 ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ብልፅግናን ጨምሮ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም ለኢትዮጵያና ኢዜማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ዕጩዎቻቸውን ማቅረባቸውን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ አቶ አብርሃም ተስፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ሕጋዊ ያልሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢ ባጅ በመያዝ ወደ ምርጫ ጣቢያው ለመግባት ሞክሮ እንደነበርና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ኃላፊው አስረድተዋል።
ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወክለው በታዛቢነት የተገኙ ሰዎች እስከ እኩለ ቀን 8፡00 ሰዓት ድረስ ብቻ እንደቆዩና ከዚያ በኋላ በነበሩ ሰዓታት ግን ድምፅ የሚሰጥ መራጭ ቢኖርም፣ ታዛቢዎች ትተው በመውጣት የድምፅ መስጠት ሒደቱ ሲጠናቀቅ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የታጠቀ የፀጥታ ኃይል ባንመለከትም፣ በምርጫ ጣቢያዎቹ ቅርብ ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች በርከት ያሉ የፀጥታ ኃይሎች የሰዎችን እንቅስቃሴ በተጠንቀቅ ሲከታተሉ ነበር። በተመለከትናቸው የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ድምፃቸውን ሲሰጡ በምን መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ከሚያሳዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ባነሮች ውጪ የዕጩዎች ዝርዝር አልተለጠፈም።
ሪፖርተር በመስተንግዶ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ ሔለን ታደሰና ኤደን ነበር የተባሉ ሁለት ሴቶችን ስለምርጫው ሒደት ያነጋገራቸው ሲሆን፣ ሁለቱም ምርጫ ካርድ አውጡ ሲባል ስለሰሙ ብቻ ማውጣታቸውን፣ ነገር ግን ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ ስለሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲ ዕጩዎች ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ከተማችን ሰላም እንድትሆን ነው ፍላጎታችን የሚሉት ሁለቱ ሴቶች፣ ምርጫውን ተከትሎ የፀጥታ ችግር ይፈጠራል የሚል ከፍተኛ ሥጋት እንደነበረባቸው ተናግረዋል።
በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ የቆዩና በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት የ65 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው አቶ ያሬድ እጅጉ፣ በተመሳሳይ እንደተፈራው አይደለም በማለት የነበረባቸውን የፀጥታ ሥጋት ይገልጻሉ።
በምርጫ ዋዜማ በከተማው ውስጥ የሚያስጨንቅ ድባብ እንደነበር፣ ይህም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖር ከነዋሪው ሥጋት ጋር ተጨምሮ የፈጠረባቸው ስሜት እንደነበር አስረድተዋል።
ብልፅግና ፓርቲን በመወከል በጎንደር ከተማ በምርጫ ክልል አንድ ፒያሳ ቀበሌ መድን ድርጅት ምርጫ ጣቢያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በምርጫ ጣቢያው ድምፃቸውን ለመስጠት ሲገኙ፣ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ይታይ ነበር።
አቶ አገኘሁ ድምፅ ሰጥተው እንደወጡ የምርጫ ጣቢያው አቅራቢያ ሆነው ለሚዲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹የዚህ ምርጫ ስኬት ወደፊት ለምናቋቁመው መንግሥት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፤›› ብለዋል።
ከተማውን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የገለጹት አፈ ጉባዔው፣ ፍፁም የተረጋጋና ምርጫውን ለማካሄድ ከየትኛውም አካባቢ የተሻለ ፍፁም ሰላማዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ሕጋዊ መንግሥት ሲቋቋም መንግሥት ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ሥራዎች ይበልጥ አሻሽሎና አደራጅቶ፣ በተለይም በአገራችን በአሁኑ ሰዓት አሉ የሚባሉ የሰላም ችግሮችንና የኑሮ ውድነትን አቅዶ ይፈታል፤›› በማለት አስረድተዋል።
ድምፅ የመስጠት ሒደቱን በሚመለከት ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች 12 ሰዓት ላይ ማጠናቀቃቸውን፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድምፅ የመስጠት ሒደቱ እስከ 12፡00 ሰዓት ሠልፍ ላይ የነበረው ድምፅ ሰጪ ድምፁን ሰጥቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሒደቱ እንደሚቀጥል አሳውቆ ነበር።
ቦርዱ በድጋሚ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 49 ንዕስ አንቀጽ 4 መሠረት ቦርዱ የምርጫው ነፃና ፍትሐዊነት ይበልጥ ያሰፍናል ብሎ ካመነ የድምፅ መስጫ ሰዓቱን ሊያራዝም እንደሚችል የተደነገገውን በማስታወስ፣ የድምፅ መስጫ ሒደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ለሊት 6፡00 ሰዓት ድረስ የተራዘመ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሒደት ሲከናወን እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የሪፖርተር ባልደረባ ከድምፅ መስጫው ቀን ማግሥት ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 1:30 ጀምሮ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች መለጠፋቸው ተዘዋውራ የተመለከተች ሲሆን፣ በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መለጠፍ የጀመረው ከማለዳው 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው።
በሰባት ምርጫ ጣቢያዎች የተለጠፋትን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶች የተመለከትን ሲሆን፣ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ብልፅግና ፓርቲን ወክለው ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎች በከፍተኛ ልዩነት በአንደኛነት ተቀምጠዋል።
ለአብነትም 1,501 መራጮች በተመዘገቡበት በምርጫ ክልል ሁለት 16 ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ብልፅግና ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ 1,208 ድምፅ በማግኘት የአንደኛነቱን ቦታ ይዘዋል።
የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያቀረባቸው ዕጩ አቶ ግዛቱ አወቀ 62፣ የኢዜማው አሰፋው ደገፋ 42፣ የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አቶ መኮንን ብርሃን 22፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ዕጩ ሙሉጌታ ተፈራ 23፣ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሰይድ ዓሊ 17፣ የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ዕጩ ብርቱካን አዲስ አሥር፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት አቶ ሻምበል ተረፈ አሥርና የአርጎባ አንድነት ጀበርቲ ያቀረባቸው ዕጩ ሃያት ሙሉ አምስት ድምፅ ማግኘታቸው በምርጫ ጣቢያው የተለጠፈው ጊዜያዊ ውጤት ያሳያል።
