የ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶአት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል የግዳጅ አፈሳ እየተካሄደ መሆኑንና ይኸም ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰና ሕገመንግስታዊ መሠረት የሌው ነው ሲል ድርጊቱን አወገዘ።
ኮሚሽኑ ከሚታፈሱት ሰዎች መካከልም አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን ማረጋገጥ ችያለሁነም ብሏል።
ኢሰመኮ ዛሬ ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በሚመለከት ባሰራጨው መግለጫው እንዳስታወቀው፣ በክልሉ እየተካሄደ ያለው ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራትና ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ ገደብና በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ግጭቶችንና ያስከተሏቸውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል።
በ2012 ዓ.ም ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ በክልሉ ተደርጎ በነበረው ምርጫ የተቋቋመውና በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የፈረሰው የምክር ቤት አባላት በድጋሚ በመሰብሰብ፣“የትግራይ ሕዝብን ሕልውና ለመጠበቅ” በሚል ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራት የውሳኔ ሰነድ አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋሉን እንዳረጋገጠ ኮሚሽን ገልዿል።
ሰነዱ ከሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ መደረግ ተጀምሯል ያለው የኮሚሽኑ፣ ይህም ማንኛውም ሰው ለግዳጅ ውትድርና የሚቀርብለትን ጥሪ የመቀበል ግዴታ እንዳለበት የሚደነግግ መሆኑን አስታውቋል።
የጸጥታ አካላት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ግለሰቦችን እንዲይዙና ፍተሻ እንዲያካሂዱ ሥልጣን የሚሰጥ ድንጋጌንም ያካተተ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ብሏል።
የግዳጅ ውትድርና ሰነዱንና ሌሎች ውሳኔዎችን በሰላማዊ መንገድ የሚተቹ ወይም የሚቃወሙ ግለሰቦች በከባድ እስራት እንደሚቀጡና ንብረታቸው እንደሚወረስ በሰነዱ መደንገጉን ገልዿል።
From The Reporter Magazine
ሰነዱ ከመውጣቱ በፊት በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን፣ በተለይም ሕጻናትን፣ ተፈናቃዮችን፣ የአእምሮ ጤና ሕሙማንን፣ እንዲሁም ከስደተኛ ካምፖችና ከጸበል ሥፍራዎች ጭምር በግዳጅ በማሰባሰብ ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ካምፖች የማስገባት ተግባር ሲፈጸም እንደነበር፣ የግዳጅ ውትድርና ሰነዱ ከወጣ በኋላም ይህ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ኢሰመኮ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ከአብነት ትምህርት ቦታዎች፣ ከገበያ ስፍራ፣ ከወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከላትና ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ በማፈስ ለወታደራዊ ተግባር እንዲሰማሩ ማድረግ መቀጠሉን ታፍሰው ከተመለሱ ወጣቶች፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከተለያዩ ሰነዶች ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።
በግዳጅ ከሚታፈሱ ሰዎች መካከልም በአብዛኛው እድሜያችዉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሕጻናት መሆናቸዉንም አስረድቷል።
From The Reporter Magazine
በተጨማሪም በክልሉና በአጎራባች ክልሎች በታጠቁ ኃይሎች መካከል የተከሰቱ ግጭቶችም በሲቪል ሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ እያስከተሉ ያሉት ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልዿል።
ለአብነትም ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሰሌንውሃ ቀበሌ በተከሰተ ግጭት አባትና ልጅ የሆኑ ሁለት ሲቪል ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና በአካባቢው በሚገኙ ከብቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በመግለጫው አመላክቷል።
በተጨማሪም በጥር ወር 2018 ዓ.ም በተከሰቱ ውጥረቶችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ከሰሜን ምዕራብ ዞን ፀለምቲና ላዕላይ ፀለምቲ ወረዳዎች፣ ማይ ፀብሪ ከተማ፣ ከደቡብ ምሥራቅ ዞን ዒስራ ዓዲ ወጀራት ወረዳ፣ እንዲሁም ከደቡባዊ ዞን ራያ ጨርጨርና ራያ አላማጣ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ያለ በቂ የምግብና የመጠለያ ድጋፍ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጨኣለሁ ብሏል።
በተመሳሳይ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአፋር ክልል አብዓላ ከተማ አስተዳደር ሙርጋ ቀበሌ ውስጥ ልዩ ስሙ አሳልጌ በተባለ ሥፍራ ጥቃት ተፈጽሞ በነዋሪዎችና በግመሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፣ እንዲሁም በርካታ የሙርጋ ቀበሌ ነዋሪዎች ከአካባቢው መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
በመሆኑም በትግራይ ክልል የሚስተዋለው የፖለቲካ ውጥረትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ የፕሪቶሪያን ስምምነት ተፈጻሚነት የሚጥስና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መንስኤ እንደሚሆን በማወቅ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ኃይል ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ውጥረትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አሳስበዋል።
በቅርቡ በክልሉ ወጣ የተባለው የግዳጅ ውትድርና ሰነድም ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ፣ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለውና ለተደራራቢና ከፍተኛ ለሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት በመሆኑ በአስቸኳይ ተፈጻሚነቱ እንዲቆም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።