በቀዶ ሕክምና በስፔሻሊቲ ደረጃ የሚሰጥ ትምህርት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የታገዘ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን፣ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ሕክምና ማኅበር 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዓርብ ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ሲያካሂድ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብደላ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ የሚሰጡ የጤና ትምህርት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ወይም ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተደራሽ ያደረገ አይደለም፡፡ የጤና ትምህርት አሰጣጡ ኢትዮጵያ ከደረሰችበት ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጣም በሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ ሊካተት ይገባል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለስፔሻሊስት ሐኪሞች በሚሰጠው የቀዶ ሕክምና ትምህርት በኤአይ የታገዙ ኮርሶችን አካቶ ለመተግበር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ደኤታዋ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) መሠረት ያላቸው ቴክኖሎጂዎች በመጨመር ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም በስፔሻሊቲ ደረጃ የሚሰጡ የጤና ትምህርቶች በኤአይ እንዲታገዙ ማድረግ ቴክኖሎጂውን በቀላሉ ለመጠቀምና ሕሙማኑንም በተገቢው ሁኔታ ለማከም እንደሚረዳ፣ በስፔሻሊቲ ደረጃ የሚሰጡ ኮርሶችን በቀጣይ በሌሎችም የጤና ትምህርቶች ለማስፋትና የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጤና ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ የተቃኘ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ ለመሥራት ከስምምነት መድረሱን ያስታወቁት ወ/ሮ ሳህረላ፣ ስምምነቱም ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠትና የሕክምና ባለሙያዎችን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ለሕመምተኞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የታገዙ የጤና አገልግሎቶችን መተግበር እንደጀመረና በዚህም ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበ የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሽታ ይበዛባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች በኤአይ የታገዙ የኤክስሬይ ማሽኖችን በመጠቀም የተከናወነው ሥራና የተገኘው ውጤት ለአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
From The Reporter Magazine
የስኳርና የሆርሞን ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስትና የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ብሩክ ዓለማየሁ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ አሁን ባለው የሕክምና አሰጣጥ አገልግሎት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዘርፈ ብዙ ሚና በመጫወት ላይ ሲገኝ ሐኪሞችም በስፋት ይጠቀሙበታል፡፡
ይህ መሆኑም የሕክምና አሰጣጡን ከማሳለጥ፣ ሐኪሞች ትኩረት ባልሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ከማድረግ፣ አንዳንድ የዲያግኖስቲክ ችግሮችን ለማወቅ የሚፈጀውን ጊዜ ከማሳጠር፣ የላቦራቶሪ ውጤት ትክክለኛነትን ከማሻሻል፣ በሰው ዓይን ሊታዩ የማይችሉ ነገሮች ጎልተው እንዲታዩ ከማድረግና በሌሎችም ሕክምናዎች ከፍተኛ ዕገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሆኖም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ገና በማደግ ላይ የሚገኝ ቴክኖሎጂ በመሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖም አለው ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ቴክኖሎጂው የሚሰጠው መረጃ ባለው ዳታ ላይ የተመሠረተና ኦንላይን ላይ ያሉ አንዳንድ መረጃዎች የተዛቡ ከመሆናቸው አንፃር ጉዳቱ ያመዘነ እንዳይሆን፣ መረጃዎችን የማጥራትና በዚያው ልክም የቁጥጥር ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡