የዓለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ የሆነ ጫና ያሳተፉ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ክስተቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የብዙ አገሮችን ኢኮኖሚ ተገዳድሯል፡፡ ዛሬ ላይ ወረርሽኙ እንደ ሥጋት መታየቱ ቢቀንስም ቁስሉ አልሻረም፡፡ ወረርሽኙ የዓለምን ኢኮኖሚ አካሄድና አሠራር ቀይሯል፡፡ ለመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት ሆኖ የአገሮች የዋጋ ንረት ምጣኔያቸውን ሰቅሏል፡፡ ብዙ አገሮች በዚህን ወቅት የገጠማቸውን የዋጋ ንረት ለማውረድ አሁንም ድረስ እየተፈተኑ ነው፡፡ ከዚህ ወረርሽኝ እንደምንም ተወጣ ሲባል የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ የኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ዕድሜ አራዝሞታል፡፡
እነዚህ ለተከታታይ ዓመታት ዓለምን የተጫኑት ክስተቶች ረገብ ሊሉ ይችላሉ ተብሎ በተገመተበት ወቅት ግን ሌላ የዓለምን ኢኮኖሚው ሥጋት ውስጥ የከተተ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ሥጋት የመነጨውም የዓለምን ኢኮኖሚ የሚዘውሩ ተቀናቃኝ አገሮች የሸቀጦች ታሪፍ ጦርነት ውስጥ መግባት በመጀመራቸው ነው፡፡
የፋይናንስ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረ መድኅን እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ኮቪድን ጨምሮ ትላልቅ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ታይተዋል፡፡ እንደ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የጋዛ ጦርነትም የዋጋ ንረትና ተያያዥ ችግሮች የዓለም ኢኮኖሚን በእጅጉ ጎድቷል፡፡
ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ኢኮኖሚን የሚያረጋጋ የዕፎይታ ጊዜ አልነበረም ያሉት አቶ አሰግድ፣ በዓለም ላይ የዋጋ ንረት ብዙም የማያውቃቸው አገሮች ሳይቀሩ በእነዚህ ዓመታት መፈተናቸውን ጠቁመዋል። ሌሎች ተገማች ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መታየታቸውንም የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ይተነትናሉ፡፡ ዓለም ከዚህ አዙሪት ሳትወጣና ሰሳታገግም ከፊት ለፊት ሌላ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይፈጥራል የተባለ ሥጋት እንደተደቀነባትም ይናገራሉ፡፡ ይህም አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አሜሪካ ገበያ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ የወሰኑት የታሪፍ ጭማሪ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከተለያዩ አገሮች ወደ አሜሪካ ገበያ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከዚህ ቀደም ተጥሎ የቆየውን ዝቅተኛ ታሪፍ በመከለስ፣ አሜሪካ ሸቀጦቹ ከሚመረቱባቸው አገሮች ጋር ያላትን የንግድና ዲግሎማሲዊ ግንኙነቶች መሠረት ያደረገ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ እንዲጣል ወስነዋል። ምንም እንኳ የወሰኑት የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊነት ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ቢደረግም፣ ከፍተኛ ታሪፍ የተጣለባቸው እንደ ቻይና ያሉ ተቀናቃኝ አገሮች ተመሳሳይ ውሳኔ ከወዲሁ ማሳለፍ ጀምረዋል። ይህም በተቀናቃኝ አገሮቹ መካከል ከፈትኛ የኢኮኖሚ ጦርነትን መቀስቀሱ እንደማይቀር አቶ አሰግድ ይገልጻሉ፡፡
አሜሪካ የጣለችው ታሪፍ በ90 ቀናት ውስጥ እንዳይተገበር የሚል የዕፎይታ ጊዜ የተሰጠው ቢሆንም የተወሰኑ ማሻሻያ ሊደረግ ይችል ይሆናል እንጂ የታሪፍ ጦርነቱ በይፋ ተጀምሯል ሊባል እንደሚችልም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ በበኩላቸው፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ አገሮች ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ እንዲጣል የወሰኑት ታሪፍ በተባለው ልክ የሚተገበር ከሆነ የዓለም አገሮችን ወደ ንግድ ጦርነት ውስጥ እንደሚያስገባ ገልጸዋል። አቶ አሰግድ እንደሚሉት፣ አሜሪካ ራሷ በጀመረችው የታሪፍ ጦርነት መጎዳቷ የማይቀር ቢሆንም፣ የንግድ ጦርነቱ ጦስ ለተቀሩት የዓለም አገሮችም እንደሚተርፍ ጠቁመዋል።
በዚህ የንግድ ጦርነት ቻይና በተለየ መልኩ ተጎጂ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ ቢሆንም ሌሎች የዓለም አገሮችም መጠኑ ከፍና ዝቅ ቢልም መጎዳታቸው እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ላይ ከተጣለው ታሪፍ አንፃር ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሚባለው ታሪፍ የተጣለባት በመሆኑ የዚህ የንግድ ጦርነቱ ብዙም ላይጫናት እንደሚችል ያላቸውን ግምት አክለዋል፡፡
እንደውም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ከፍ ብሎ እንደሚታያቸው የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ይህ ታሪፍ ጦርነት በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ ላኪዎች የተሻለ ዕድል ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚጣ የሚችለውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ግን እንደ አገር ብዙ መሠራት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሲባል ግን ጨርሶ ጉዳት አይኖረም ማለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
‹‹እስካሁን ባለው ሁኔታ ብቻ የተፈጠረው ቀውስ ቀላይ አይደለም የሚሉት አቶ አበባየሁ፣ የታሪፍ ጦርነቱ ጅማሬ አሜሪካንን ጨምሮ የበርካታ አገሮችን የካፒታል ገበያ (ስቶክ ማርኬት) ቁልቁል እንዳወረደው፣ እጠቀምበታለሁ ብላ የታሪፍ ጦርነቱን የጀመረችው አሜሪካን ሳትቀር ኢኮኖሚዋ መጉዳት መጀመሩ በግልጽ እየታየ እንደሆነ አስረድተዋል። ምናልባትም ከዚህ የከፋና ያልተጠበቁ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል።
‹‹አሜሪካ ትቅደም›› ብለው የተነሱት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የገጠማቸውን የንግድ ጉድለት ለማመጣጠን ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ በሚልኩ አገሮች ላይ እንዲጣል የወሰኑት ከፍተኛ ታሪፍ ከአወንታዊ ውጤቱ ይልቅ ለራሷ ለአሜሪካ ኢኮኖሚዊ ቀውስ ይዞባት እንደሚመጣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ዘግየት ብለውም ቢሆንም እየተረዱት መምጣታቸውን አቶ አሰግድ ገልጸዋል። በተለይም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨማሪ የዋጋ ንረትን ያስከትላል የሚለው ሥጋትም ጎልቶ እየወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አበባየሁ፣ ይህ የትራምፕ የታሪፍ ውሳኔ የአሜሪካን ኢኮኖሚ መልሶ የሚጎዳ ስለመሆኑ በሰጡት ማብራሪያ በተለይ ታሪፍ የተጣለባቸው ትልልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች በቴክኖሎጂ የዳበሩ በመሆናቸው አዲስ ገበያ ወደሚያገኙበት እንደሚሄዱ፣ ይህም ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ጉዳት እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።
አንድ አገር ከፖለቲካዊ ግብ ጋር የተቆራኘ ታሪፍ በምትጥልበት ጊዜ፣ ታሪፍ የተጣለበት አገርም አጠፋዊ ምላሽ መስጠቱ የማይቀር በመሆኑ ነገሩ ተካሮ በአገሮች መካከል የንግድ ጦርነት እንደሚወልድ፣ ይህም ዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚ ጉዳትን እንደሚያስከትል ገልጸዋል።
‹‹የመንግሥት ገቢ ታክስ ነውና በታሪፍ ምክንያት ገቢው ሲቀንስ ያንን ለመሙላት ፊትህን ወደ አገር ውስጥ ታዞራለህ ማለት ነው፤›› ይህ ማለት ዋጋ ይጨምራል ሸማቾችንም ይጎዳል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ንቅናቄና አለመረጋጋትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀውሱ ከንግድ ጦርነት ባሻገር ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውሶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ችግሩ በኢኮኖሚ ጦርነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይሆንም፡፡ ይህ አካሄድ ጦርነትን ወደ መፍጠር የሚሄድበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሁሉ ጥንቃቄን የሚፈልጉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
ሰሞኑን ከአሜሪካ መንግሥት የተሰማውን ከፍተኛ የታሪፍ ማሻሻያ ውሳኔ ተከትሎም በርካታ አገሮች የአሜሪካ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ታሪፍ በመጣል አጠፋዊ ዕርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አቶ አሰግድ ጠቁመዋል። ለዓብነትም ቻይናና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ከሰሞኑ የአጠፋ ዕርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ አገሮች ቀደም ብሎም ሜክሲኮ፣ ካዳናና ሌሎች አገሮች በአሜሪካ ላይ አጠፋዊ ዕርምጃ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ አኅጉር የሚገኙ 17 የአፍሪካ አገሮችም ተመሳሳይ ዕርምጃ እንደወሰዱ የገለጹት አቶ አሰግድ፣ ለዓብነትም አልጀሪያ፣ ናይጀሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞርሺየስ፣ ዝምባብዌ፣ ሞዛምቢክና ደቡብ አፍሪካ በአሜሪካ መንግሥት ለተጣለባቸው ከፍተኛ ታሪፍ ፈጣን የሚባል ዕርምጃ በመውሰድ አጠፋዊ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ አገሮች በሜሪካ ላይ እስከ ሦስት እጥፍ የሚደርስ ታሪፍ መጣላቸውን፣ ይህንን ሲያርጉም ከአሜሪካ ገበያ ውጪ ምርቶቻቸውን የሚፈልጉ ሌሎች ገበያዎች መኖራቸውን የሚገልጽ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጠቁመዋል።
ለተወሰኑ አገሮች ሊፈጥር የሚችለው መልካም ዕድል
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ በብዙኃኑ አገሮች ላይ ተገማች ያልሆኑ ቀውሶችን ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም፣ በአንፃሩ ደግሞ አሜሪካ በተለያዩ አገሮች ላይ የጣለቸው ከፍተኛ ታሪፍ ዕድል የሚፈጠርላቸው የተወሰኑ አገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በታሪፍ ምክንያት ገበያቸው የተነካ አገሮች ከጥገኛነት ለመውጣት የተጣለባቸውን ታሪፍ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወስዱት ይችላሉ ያሉት አቶ አበባየሁ፣ ይህም ሊፈጠሩ ከሚችሉት ዕድሎች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ ሥርዓት ቀርፀው በመተግበር ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ሲተኩ ተጠቃሚው በተሻለ ዋጋ ምርቱን እንዲያገኝ ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ የታሪፍ ወሳኔ የሚጉዱ አገሮች አዳዲስ ገበያዎችን እንዲያማትሩ ወይም እንዲፈጥሩ በማድረግ የገበያ ዕድሎችን ሊያሰፉ እንደሚችሉ፣ ይህ ከሆነ ደግሞ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።
አዲሱን ክስተት ከአፍሪካ አንፃር ከታየ ደግሞ የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጣቸውን በማሳደግ ትልቅ ገበያ የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ሊመጣ እንደሚችል ገልጸዋል። ይህም ከአራት በመቶ ለማይበልጠው የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ ግብይትን ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ሌላው መልካም ዕድል ቻይና ከምትወስደው ምላሽ ሊመነጭ የሚችል ነው። አቶ አበባየሁ እንደሚሉት ቻይና ከአሜሪካ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣል ብቻ አትመልስም። ቻይና አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ ወደ ዕድል ልትቀይረው እንደምትችል የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ትልቋ የአሜሪካ ተገዳዳሪ ከጣለችው በላይ ታሪፍ በመጣል ብቻ አትመለስም፡፡ አገሮች ዓለም ላይ የመጣውን ትሬት ቻይና ወደ ኦፖርቺኒቲ ትቀይረዋለች፡፡ ይህም የሚሆንበት ታሪፍ በተጣለችባቸው ቻይና ከሌሎች የአሜሪካ ታሪፍ ሰለባ ከሆኑ አገሮች ጋር ዲፕሎማሲ ግንኙነቷን በማጠናከር ሌላ የኢኮኖሚ አቅም የመፍጠር ስትራቴጂን ልትከተል እንደምትችል፣ ወደ አሜሪካ ገበያ ይልኩ የነበሩና አሁን ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የተጣለባቸው አገሮችን በማግባባት ምርቶቻቸውን ወደ ቻይና እንዲልኩ እንዲሁም በአሜሪካን አገር ተመርተው ወደተቀረው የዓለም ገበያ የሚላኩ ምርቶችን ራሷ ማምረት ልትጀምር እንደምትችል ጠቁመዋል።
በዚህም ወደ አሜሪካ ይላኩ የነበሩ ምርቶች ወደ ቻይና ገበያ የሚላኩበትና ከአሜሪካ የሚወጡ ምርቶች ደግሞ በቻይና ተመርተው ወደ ዓለም ገበያ የሚሠራጩበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል የሚል ዕምነታቸውን አጋርተዋል።
ቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶቿ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ መጣሉ ከፍተኛ ጥቅም የሚያሳጣት መሆኑን የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ይህንን ጥቅሟን በተዘዋዋሪ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን እንደምትጠቀም ጠቁመዋል።
ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ ኩባንያዎቿን አሜሪካ ዝቅተኛ ታሪፍ ወደጣለችባቸው አገሮች በማሰማራትና በእነዚህ አገሮች ውስጥ በማምረት ወደ አሜሪካ ገበያ የምትልክበትን መንገድ በድብቅ ልትቀይስ እንደምትችል ገልጸዋል።
ቻይና ከዚህ ቀደምም እንዲህ ያለ አማራጭ ስትከተል እንደነበር የጠቀሱት አቶ አበባየሁ፣ ለምሳሌ ወደ አፍሪካ አገሮች ዘልቃ በመግባትና ምርቶቿን በእነዚህ አገሮች በማምረት ወደ ትልቁ የአሜሪካ ገበያ ልትልክ የምትችልበት ዕድል መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን የምታደርግ ከሆነ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ሌላ ተጨማሪ ዕድል ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው በተጨማሪ ሊፈጠሩ በሚችሉ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች አማካይነት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዕድል ይፈጠራል ወደሚል ግምት ይወስዳል፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ባላት የንግድ ልውውጥ የንግድ ሚዛኑ ወደ አሜሪካ ያደላ ቢሆንም፣ ይህንን ጉድለት መለወጥ ይቻላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። እሳቸው ኤስፖርት የሚያደርጓቸው ምግብ ነክ ምርቶችም የተሻለ ገበያ ሊያገኙ እንደሚችሉም ያምናሉ።
ኢትዮጵያ ከታሪፍ ውሳኔው ትጠቀማለች?
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው የአሥር በመቶ ታሪፍ በኢትዮጵያ ወሳኝ የቡና የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በቡና ኤክስፖርት ፋይናንስ ጋር በተያያዘ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱት የባንክ ባለሙያ አቶ ደመቀ ፀጋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ ቡናን በመግዛት በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከቡና ከምታገኘው ገቢ ውስጥ ትልቁን ድርሻን የሚይዘው የአሜሪካ ገበያ ነው።
‹‹አሜሪካ የጣለችው ታሪፍ ከቡና ዋጋ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋል፣ የዋጋ ጭማሪን ያመጣል፤›› የሚሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹የሚጣለው ታሪፍ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ወጪ ተጨምሮበት የኢትዮጵያን የቡና ምርት የመሸጫ ዋጋን ስለሚንረው፣ በአሜሪካ የሚገኙ ደንበኞች እንደ ብራዚል፣ ፔሩና ኮሎምቢያ ባሉ ደቡብ አሜሪካውያን አምራቾች በጅምላ የሚቀርበውን የሮቦስታ ቡናና ሌሎችንም እንዲመርጡ በማድረግ ለኢትዮጵያ ቡና ያላቸው ፍላጎት ሊቀንስ ይችላል፤›› ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ በሌሎች ቡና አምራች አገሮች ላይም ከፍተኛ ታሪፍ የጣለች መሆኑ የኢትዮጵያ ቡና በአሜሪካ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል ዝግ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያ የቡና አቅርቦት ሰንሰለት፣ የማምረት ወጪ፣ ሎጂስቲክስና አጠቃላይ ውጤታማነትን ጨምሮ ሌሎች ወጪን የሚያሳድጉ ምክንያቶች ለመቅረፍ የተቻለ እንደሆነ ነው ብለዋል።
የላቲን አሜሪካ አገሮች ቡናን በብዛት ከማምረት በተጨማሪ ለአሜሪካ ገበያ ቅርብ በመሆናቸው የተሻለ የውድድር ጥቅም እንዳላቸው የገለጹት አቶ ደመቀ፣ ኢትዮጵያ በቡና ምርት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ረዥምና አላስፈላጊ ሒደቶች በመቀነስ ምርትነቷን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻልና አቅርቦትን ማቅረብ እንደሚኖርባት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያና የአሜሪካ የንግድ ልውውጥ የሚያመለክቱ መረጃዎች እ.ኤ.አ. በ2021 ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከተላከ የወጪ ንግድ ምርት 601.0 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ በአንፃሩ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከላከቻቸው ምርቶች 575.5 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ በ2021 በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ያጋደለ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ልካ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ በ25.5 ሚሊዮን ብልጫ ያለው ነው፡፡ በ2022 ግን አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ልካ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡ በዓመቱ ውስጥ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከላቻቸው ምርቶች ያገኘችው ገቢ 1.08 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ 718 ሚሊዮን ዶላር ስለማግኘቷ ያመለክታል፡፡ ይህም 366.2 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው የንግድ ልውውጥ መደረጉን ያመለክታል፡፡ በቀጣዩ በ2023ም አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ልካ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ዕድገት በማሳያነት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ ኢትዮጵያ ደግሞ 490 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷ ተመልክቷል፡፡ ይህ የ2023 የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ 730.2 ሚሊዮን ዶላር ልዩነት ያሳየ ሆኗል፡፡
በተጠናቀቀው 2024 ዓመት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው ምርቶች 1.01 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የላከችው ምርት ግን ከቀዳሚዎቹ ዓመታት አሽቆልቁሎ 465.8 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በአዲሱ 2025 የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወሮች ኢትዮጵያ 102.7 ሚሊዮን ዶላር ስትልክ አሜሪካ 449.6 ሚሊዮን ዶላር ወደ አሜሪካ ልካለች፡፡ ከምትልከው ምርት ታገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ የቀነሰበት ዋነኛ ምክንያት ከቀረጥ ነፃ ታስገባቸው የነበሩ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ምርቶች በመቀነሱ ነው፡፡
የአገዋ ዕድል ይከልከል እንጂ እስካሁንም በቀረጥም ወደ አሜሪካ እየገቡ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበባየሁ አሁን ያለው ታሪፍ የተሻለ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው ምርቶቻቸውን መላክ የመሚችሉበት ዕድል መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የንግድ ጉድለት ማጥበብ እንደምትችል ለዚህም አዳዲስ ምርቶችን በማስገባት ገበያውን የማስፋት ስትራቴጂ መከተል እንደሚኖርባት አመልክተዋል።
በተደጋጋሚ የአሜሪካን ገበያ በቃኙበት ወቅት መደብሮች በቻይና ምርቶች ተሞልተው መመልከታቸውን፣ እዚያው ገበያው ላይ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችም መኖራቸውን እንደታዘቡ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አሁን የመጣው ዕድል እነዚህን ምርቶች በጥራትና በብዛት ማምረት ገበያውን ማስፋት ውጤት እንደሚኖረው አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህ እንደ ምሳሌ ያነሱት አንድ የቻይና ጅንስ ሱሪ እስካሁን በነበረው ዋጋ ሃያ ዶላር ይሸጥ ከነበረ እዚህ ጅንስ ላይ መቶ በመቶ ታሪፍ ከጣለ ዋጋ ወደ 40 ዶላር ይጠጋል፡፡ ስለዚህ የቻይና ምርት እንደ ቀድሞ የአሜሪካንን መደብሮች የሚያጣብበት ሁኔታ አይኖርም፣ ይህ ደግሞ ለአሜሪካ ገዥዎችም ሆነ ለቻይና ትልቅ ጉዳት እንደሚሆን ይግለጻሉ፡፡ በአንፃሩ ዝቅተኛ ታሪፍ ከተጣለባቸው አገሮች ሊገባ የሚችለው ጂንስ ሱሪ በቅናሽ ስለሚሸጥ ለአዳዲስ አገሮች ገበያ የሚከፍትበት ዕድል እንደሚር ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት ምርቶቿን ወደ አሜሪካ ለመላክ የምትችልበት ጊዜው አሁን መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ አበባየሁም ሆነ አቶ አሰግድ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ በተለያየ ሁኔታ ይቀይራል ተብሎ የተሠጋው የንግድ ጦርነት አካሄድ ከግምት በማስገባት ተጠቃሚ የሚኮንበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ እንዴት መጠቀም እንችላለን? የሚለውንና ተፅዕኖም ካለ ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ በመንግሥት ደረጃ መቀረፅ እንዳለበትም ያምናሉ፡፡
የዓለም ተለዋዋጭ ባህሪ በተለመደው መንገድ መጓዝ የሚያስችል መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሰግድ ፖሊሲዎች ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እየተናበቡ መሻሻል እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል፡፡
በዚህ ረገድ ሁሉም የሮድ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያሉት አቶ አበባየሁ በበኩላቸው፣ እንደ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ላይ እንዲመከርበት የሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተፅዕኖውና መልካም ዕድሎቹ የትኞቹ ናቸው? የሚለው ላይም ጥናት እንዲደረግና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሠሩ እየተዘጋጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡