ለሙስና ጠቋሚዎች (Whistleblowers) ደኅንነት ዋስትና የሚሰጥ የተጠናከረና አፋጣኝ የጥበቃ ሥርዓት እንዲኖር፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባወጣው ጥናት ጠየቀ፡፡
በመንግሥትና በሌሎች አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሙስና አዝማሚያ ወይም ድርጊት መኖሩን የሚጠቁሙ አካላትን የደኅንነት ጥበቃ በሚመለከት፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሟቋሚያ አዋጁ 1236/2021 በግልጽ ተደንግጓል፡፡
በአዋጁ ሙስናን ለመከላከል ለኮሚሽኑ ጥቆማ በመስጠታቸው ምክንያት በተጠቆበት ወገን የቂም በቀል ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ጠቋሚዎች ሲኖሩ፣ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ጥበቃ እንደሚደርግላቸው ተደንግጓል፡፡ አዋጁ ይህን ቢልም በተደነገገው ልክ ለጠቋሚዎች የሚሰጠው ከለላ እምብዛም መሆኑን፣ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ለኮሚሽኑ አራተኛ የሆነው ብሔራዊ የሙስና ዳሰሳ ጥናት ሰነድ እንደሚያሳየው፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች ሙስና አሳሳቢ ችግር መሆኑንና አሁን ያለው የሙስና ደረጃ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ምጣኔ የበለጠ ስለመሆኑ በመረጃ ሰጪዎች በብዛት የተነገረ መሆኑን ያብራራል፡፡ ጥናቱ ተቋማዊ ሪፎርምና ከፍተኛ ተጠያቂነትን ሊያመጡ የሚችሉ ዕርምጃዎችን በመተግበር የሕዝቡን እምነት መመለስ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው የኮሚሽኑ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የጥቆማ ሒደቱ የተንዛዛ መሆን፣ ዜጎች እንዴት መጠቆም እንዳለባቸው መረጃ አለመኖር፣ ጥቆማ አቅራቢዎች ሊደርስባቸው የሚችል የአፀፋና የበቀል ዕርምጃ ሊታደግ የሚችል ጠንካራ ከለላና የሕግ ጥበቃ አለመኖሩ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም ጥናቱ ጠንካራ የጥበቃ ሥርዓትን በመገንባት አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና ተጨባጭ፣ የሚታመንና ተፈጻሚ የሚደረግ ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡ አክሎም ቀላልና ማንነትን የማያጋልጥ የጥቆማ መንገድ እንዲተገበር ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱና የአገር ሀብት በሚመዘብሩ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ መውሰዱን አሳውቆ ነበር፡፡
From The Reporter Magazine
በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በልማት ድርጅቶች፣ በመንግሥት መዋቅር፣ በግለሰቦችና በተገልጋዮች ጭምር በተደራጀ መንገድ በስፋት እንደሚታይ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሯ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔን ጨምሮ ከአንደ መቶ በላይ ተጠርጣሪዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
ሚኒስትሯ ወ/ሮ እናትዓለም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፈጣን ልማትና ዕድገት እንድታረጋግጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ሰፋፊና አስደናቂ አገራዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት ‹‹መንግሥታዊ ሌብነት የለም›› በሚል በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም፣ በሥርቆት እየተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ የሚባሉ የመንግሥት ተሿሚዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
From The Reporter Magazine
የኮሚሽኑ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያስረዳው በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞች ከሰጡት ምላሽ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የጨረታ ሰነዶች የሚያሸንፉት በእጅ መንሻ መሆኑን ሲገልጹ፣ ከተሳታፊዎች 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳዩ ላይ ሐሳብ ለመስጠት አንፈልግም ማለታቸውን ያስረዳል፡፡ አክሎም በአጠቃላይ የመንግሥት ተቋማት የግዥ ሥርዓት ሪፎርም እንደሚያስፈልግው አሳብቧል፡፡
በሁሉም ክልሎች በተደረገው ጥናት ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ገለልተኛ ናቸው ብለው እንደማያስቡ፣ ይህም ምክንያቱ ሚድያዎች ከመንግሥት ጋር በፋይናንስ የተሳሰሩ በመሆናቸው ጋዜጠኞች ገለልተኛ ቢሆኑም እንኳ ተቋማቱ ከሙስና የፀዱ ናቸው ብለው አያስቡም ይላል፡፡
ሚዲያ ኤዲቶሪያል ነፃነቱን ጠብቆ እንዲሠራ ሕጋዊ ዋስትና እንዲኖረው፣ ከመንግሥት ባልሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ነፃ መደረግ እንዳለበት አስረድቷል፡፡
የሚዲያ ተቋማት ለኮሚሽኑ ጥናት በሰጡት ምላሽ ማስፈራሪያ፣ ዛቻ፣ የመረጃ መከልከል፣ የፖለቲካ ጫና ዋነኛው የሥራቸው መሰናክል ናቸው ያለው ጥናቱ፣ የሙስና ጉዳዮችን በተመለከተ የምርመራ ዘገባ የሚሠሩ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ከውጫዊ ጫና ነፃ በመሆን መሥራት አለባቸው ብሏል፡፡
ሙስና በኢትዮጵያ በስፋት የተንሰራፋና ሥር የሰደደ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን የገለጸው ጥናቱ፣ ይህ ገጽታ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ተቋማትና አሠራሮች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አብራርቷል፡፡ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በተካሄደው ዳሰሳ መሬትን የተመለከቱ ጉዳዮች በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስና የተጋለጡ መሆናቸውን የጥናቱ ተሳታፊዎች ምላሽ መስጠታቸውን ያመላክታል፡፡ በአብዛኞቹ ክልሎች ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው በሚል የተለዩት የመሬት ምዝገባና የመሬት አስተዳደር ቢሮዎች፣ የገቢዎች፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ ቢሮዎች፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኮንስትራክሽን ፈቃድና ቁጥጥር፣ የቀበሌና የወረዳ ቢሮዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ይገኙበታል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ ምላሽ የሰጡት ተሳታፊዎች ባለፉት ዓመታት ለሙስና ድርጊት የተጋለጡ ሰዎች ምክንያታቸው፣ አገልግሎት ለማግኘት ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ እንደሆነና እነዚህ ድርጊቶችም በዕለት ተዕለት ሕይወት የተለመዱ እየሆኑ መጥተዋል ይላል፡፡
ለዳሰሳ ጥናቱ አስተያየት ከሰጡት የመንግሥት ሠራተኞች መካካል 62 በመቶ የሚሆኑት የበላይ አለቃን ማስደሰትና የሚፈልጉትን መፈጸም ለቀጣይ የሥራ ደረጃ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መናገራቸውን፣ የማንነትና የክልል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ወገንተኝነት በሥራ ውስጥ ሌላው የደረጃ ዕድገት መወሰኛ መሠረት መሆኑ መገለጹን ያብራራል፡፡