- የገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ተብሏል
በቴክኒክና ሙያ ማኅበራት ሥልጠና በሚወስዱ ሥራ ፈጣሪዎች የሚቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች)፣ የካፒታል እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥሪ ቀረበ፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከሰኔ 5 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ውድድር መክፈቻ፣ በቴክኒክና ሙያ ማኅበራት በሠለጠኑ የሥራ ፈጣሪዎች የሚመሠረቱ የንግድ ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ቁመናን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ምትኩ እሸቱ (ፕሮፌሰር)፣ የጥናቱ ውጤት ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እጥረት መኖሩን አሳይቷል ብለዋል።
በሐረር፣ በሃረማያና በድሬዳዋ ከተሞች 80 በሚደርሱ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ የክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ በተደረጉበት ጥናት እንደገለጹት፣ በአማካይ ከ79 በመቶ በላይ የኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ምንጭ ቤተሰብና ጓደኞቻቸው ናቸው።
ከፋይናንስ ተቋማት በተለይ ከባንኮች ብድር ማግኘት የሚያስችል መሥፈርቶችን አሟልቶ አለመምጣት ለዚህ አንዱ ችግር መሆኑን ጥናት አቅራቢው ገልጸዋል። የወሰዱትን ብድር በወቅቱ አለመመለስ የፋይናንስ አቅርቦት አናሳ እንዲሆን ያደረገ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ምትኩ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል። ከባንኮች ብድር ለማግኘት ባለው ውስብስብ ቢሮክራሲ ምክንያት ሐሳባቸውን ያጠፉ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለሥራ ፈጠራ የወሰዱትን ብድር ለሌላ አገልግሎት ማዋል፣ ብድርን ሳይከፍሉ ከአገር መውጣት ችግር እንደሚስተዋል፣ ለዚህ መንስዔው በመንግሥት አካላት በኩል ብድር የማስመለስ ቅንጅታዊ የክትትል ሥራ አለመኖሩን ገልጸዋል። ከባንኮች ጋር በተደረገ ንግግር የተወሰዱ ብድሮች ባለመመለሳቸው ምክንያት፣ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑም መናገራቸውን ጠቅሰዋል።
ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ አገሮች የመላክ አፈጻጸማቸው ደካማ ነው ብለዋል። ሥጋትና ውድቀትን የመቋቋም አቅማቸውም ዝቅተኛ መሆኑን አመላክተዋል። ለዚህም ችግር እንደ ምክንያት ያቀረቡት አንዱ ችግር የፋይናንስ አቅማቸው አናሳ መሆን ነው።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የብድር አማራጮች እንዲሰፉ የሚያደርጉ አማራጮች እየተፈጠሩ እንደሚገኝ፣ ሆኖም ተፈጻሚነት ላይ ግን ውስኝንቶች መኖራቸውን፣ ይህም እንዲቀረፍ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ከፋይናንስ በተጨማሪ የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ በሱስ ምክንያት ዝቅተኛ የጊዜ አጠቃቀም መኖርና ሌሎች ችግሮ ተብለው ተጠቃሽ ተደርገዋል።
From The Reporter Magazine
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ማኅበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ጥምረት እንዲፈጠር ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። ይህ ሥርዓት ከተፈጠረ ዘርፉ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት በጋራ የሚሠሩበት ዘላቂ ቅንጅትን እንደሚያመጣና ለችግሮች መፍትሔ ለማበጀት እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ሌላዋ የዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ግምገማ ባለሙያ ባንቻየሁ ግርማ (ዶ/ር) የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማኅበራት በተለይ የአምራች ዘርፉ ገበያን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፍላጎትን በተመለከተ ባደረጉት ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ዝቅተኛ የሥራ ማስኬጃ ካፒታልና የሥራ ቦታ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑን መስተዋሉን በተግዳሮትነት ገልጸዋል።
ለዚህም መንግሥት አማራጮችን ሊያመቻች እንደሚገባ፣ የዋጋ ንረት እንዲረጋጋ፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል። የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
From The Reporter Magazine
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ከባንኮች ጋር እየተሠራ መሆኑን፣ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሊሳካ እንደማይችል ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከጊዜው ጋር አብረው የሚሄዱ የገበያ ጥናትና የእሴት ሰንሰለት የተደረገባቸውን መደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም በ2018 ዓ.ም. 11 መደበኛና 36 አጫጭር ሥልጠናዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቲክስ፣ አዳዲስ የኃይል አማራጮች፣ የረቀቀ አምራች ዘርፍ (Intelligent Manufacturing)፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ፣ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ለአብነት ተጠቃሽ የሆኑ አዳዲስ የሥልጠና ዘርፎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ጉባዔው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሥራዎችን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ በተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አጋሮች መካከል ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በዲጂታል ሽግግርና በቴክኒክና ሙያ ማኅበራት ፈጠራ የኢንዱስትሪ ለውጥ፣ የፖሊሲ፣ አስተዳደር አካታችነትና ዓለም አቀፍ አጋርነት ላይ ማተኮሩም ተጠቁሟል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የክህሎት ልማትና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራን ያቀፈ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር›› በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው ጉባዔው፣ ከ16 በላይ የዓለም አገሮች የመጡ ተሳታፊዎች የተገኙበት፣ 30 የምርምር ጽሑፎች፣ 35 አዳዲስ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሥራዎች የቀረቡበት ስለመሆኑ ተናግረዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለዓለም ገበያ የሚሆኑ የሰው ኃይል ዝግጅት ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑንም አክለዋል።
ዓለም በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን አምስተኛውና ስድስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ተግባራዊነት ላይ በአገር ደረጃ መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል።
