ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ በሙሉ እንደምን ከረማችሁ? እንዲያው ለመሆኑ በአገራችንም ሆነ በዓለም የምንሰማቸው ደስ የማይሉ ነገሮች እንዴት እያደረጓችሁ ነው? በዚህ መሀልስ የሰው ልጅ ተለዋዋጭ ባህሪ ሲታከልበትስ ምን ይሰማችሁ ይሆን? ‹‹እንደ እንስሳ ሆዱን መቼ ይመለከታል፣ ሰው ፍቅር ካገኘ ምግብማ ሞልቷል…›› ያለው ነፍሱን ይማረውና የአገራችን ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ትዝ እያለኝ እኔ እንዳለሁ አለሁ። ደብዳቤ አስመሰልኩት እንዴ? ምን ይደረግ ሰው በነገር ሆዱን ሲታመም ንግግሩ ሁሉ ብሶት፣ ብሶቱ ደግሞ ደብዳቤ መምሰሉ አይቀሬ ነው። ሰው ደግሞ እንደምታውቁት ነው። ቤት መሥራት ሲያቅተውና ለፍቶ አላልፍልህ ሲለው የነገር ጭቃ እያቦካ ሐሜት በሚባል ነፃ የሽርደዳ ሜዳ ላይ እርስ በርሱ ይለሳሰናል። የዘንድሮን ነገር እንጃልን ብቻ፡፡ እንደ አገር እያሰቡ መኖርን የሚያከብድብን አንዱ ችግራችን ክፍት ውሎ የሚያድረው ገመናችን መሆኑን አትርሱት። ‹‹እንደ እኛ በሰው እንጀራና በሰው ጎጆ ሚስጥር ሥራ የሚፈታ ያለም አይመስለኝም…›› የሚሉኝ እኮ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። እሳቸው ዕድሜ ብዙ ስላሳያቸው ስለሰው ብዙ ነገሮች ያውቃሉ። ስንቱ አለ ከዕድሜው የማይማር? ታዲያስ ባሻዬ አራት ትውልድ እያፈራረቁ በፈጣሪ ፀጋ በማስተዋል ኖረዋል። ቀላል ነው እንዴ? እሳቸው በማስተዋል ሲራመዱ ስንቱ ደግሞ የእንጨት ሽበት ሆኖ መቅረቱ መዘንጋትም የለበትም፡፡ ለምን ይዘነጋል!
‹ወዳጅ ጠላት ሲሆን ክፉ ትዝታ አለው› እየሆነ ነገራችን ሁሉ የኑሮ ግብግብ በ‹እህህ…› ሲወዘውዘን ዕድሜ አልመርጥ አለ እንጂ። ኧረ ተውኝ እባካችሁ፣ የአገር ውሎና አዳር ጉዳይ አሞኝ አይደል ዛሬ የተገናኘነው? ‹‹ጎበዝ ጭካኔ አገር ሊያፈርስ ምን ቀረው?›› ስል የሰማኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ለሥልጣንና ለጥቅም ስንል በክፋት የተጠመድነው ለምን ሆነና?›› ይለኛል። እሱ መቼስ ከጀመረ አይለቅም አይደል? ‹‹ይልቅ እኔን የሚገርመኝ ይህ ሥር የሰደደ የክፋትና የጭካኔ ልማድ እያለ፣ ምሁራኑ አፉን እንደ ለጎሙት ፈረስ በ‹ዝም አይነቅዝም› ዘዬ ተደላድለው መቀመጣቸው ነው…›› ብሎ ጨመረልኝ። ‹እንዲያው ልፉ ብሎን እንጂ ምሁራኑ አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉት ወጀቡ ሲያልፍ ነው እንዴ?› ብዬ በውስጤ ታዘብኳቸው። ድሮም የሐሜት ትርፉ ትዝብት ነው አትሉልኝም? ‹‹የሆነስ ሆነና ሁሉ ነገር ሞልቶ በተረፋት አገር ውስጥ የሰው ልጅ በጭካኔ እየተገደለና እየተሳደደ ነው እየተባለ እኮ ነው ምሁራን የታሉ እያልን የምንጨነቀው…›› ሲሉኝ የነበሩት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ ጉድ እኮ ነው!
ሰሞኑን አንድ ሁለት የማሻሽጣቸው ቪትዝ መኪኖች እጄ ላይ ነበሩ። ወዲያ ወዲህ እላለሁ። አንዱ ዳቦ ሲሸጥ ሁሉም ተያይዞ ዳቦ ነጋዴ፣ አንዱ ካፌ ሲከፍት ሁሉም ካፌ መክፈት ልማድ ስለሆነ የዚህ አገር ሊሻር ያልቻለ የቢዝነስ ባህል፣ የኤሌክትሪክ መኪና ነጋዴው እንዴት እንደ አሸን እንደፈላ አትጠይቁኝ። ለነገሩ ሸማቹ በኑሮ ውድነት አቅሉን ቢስትም ገበያ መውጣቱ አልቀረም። አደራ ደግሞ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰምቶኝ ‹የቪትዝ ሸማቾችና ሻጮች ማኅበር መጎልበት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ማሳያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንበርብር ምንተስኖት ተናገሩ› ብሎ ዜና እንዳይሠራብኝ። ምን ይታወቃል? መጠርጠርና መጠራጠር መስሎኝ አከባብሮ እያኖረን ያለው። እንዲያው እኮ ምናለበት አሁን ክፉ ባታስወሩኝ? አንዱ በቀደም ዕለት ስለሰሞኑ ስለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እየተነተነ ነበር፡፡ እኔ ሰውየውን የማውቀው ከኮንትሮባንድ ነጋዴነት አሁን ደግሞ ወደ መሬት ደላላነት መሸጋገሩን ነው፡፡ በየት በኩል የፖለቲካ ተንታኝ እንደሆነ ስላልገባኝ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ዋርካ በሌለበት እምቧጮ አድባር ይሆናል ሲባል እየሰማህ አይደል እንዴ የኖርከው…›› ሲለኝ ሰውነቴ ከላይ እስከ ታች ቀዘቀዘ፡፡ ፍሪጅ ሆንኩ ለማለት ነው!
እንግዲህ አንዱ የሚለብስ የሚጎርሰው አጥቶ ሲንገላወድ፣ ሌላው ያማረውን ሲሸጥና ሲገዛ ማየቱ አድሮ እንደ አዲስ እያስደነቀኝ እንደለመደብኝ ተፍ ተፍ እላለሁ። በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ መኪኖች እንደ አሸን እስኪፈሉ ድረስ ቪትዞችን የሚቀባበላቸው አሁንም ቁጥሩ ቀላል ስላልሆነ ሦስት አራቱን ካሻሻጣችሁ ደህና ዝግ ነው። ‹ዝግ የሚባል ቢዝነስ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይቀርም› ያለኝ ማን ነበር? እና አንዲት ውብ ወጣት ሁለቱን ቪትዞች እንደምትፈልግ ነግራኝ ተገናኘን። መኪኖቹ ደህና ይዞታ ላይ ቢሆኑም ማስፈተሽ ግድ ነውና በባለሙያ ስታሳይ ዋለች። መላመድን የመሰለ ነገር የለምና አንድ አንድ ስንባባል ሳታስበው ከአፏ ያመለጣት አባባል ቀልቤን ሳበው። ምን አለችኝ መሰላችሁ? ስለኑሮና ስለትዳር እያወራን በአጠገባችን አንዲት ወጣት ልጇን ታቅፋ ስታልፍ፣ ‹‹ይኼውልህ ያደለው ልጅ ወልዶ የመኖር ምክንያት ያበጃል፣ እኔ ግን ለቆርቆሮ እንጦለጦላለሁ…›› አለችኝ። ከአንጀቷ መሆኑ ገብቶኝ፣ ‹‹ይኼንንስ ማን አየብሽ? አይዞሽ ሁሉም በጊዜው ይሆናል፣ ያውም አንቺን የመሰለች ልጅ…›› ስላት፣ ‹‹አይ አንተ ጊዜ ብቻውን ነው ብለህ ነው ሰውን እያነሳ የሚጥለው? ሰውም እኮ አመሉ ሲመች ነው ጊዜ ውለታ የሚውልለት። አመል ማክፋት እንደ ፋሽን ተይዞልን መስሎኝ የምናየውን እየካድን፣ የሆነውን አናምንም እያልን በችግር ላይ ችግር የምንደራርበው…›› ብላኝ በሐሳብ ከነፈች። ‹እኔን ያብረኝ ያክንፈኝ…› አልኩኝ በሆዴ፡፡ ሌላ ምን እላለሁ!
ውቢት ቪትዞቹን ተረክባ ኮሚሽኔን በሞባይል ባንኪንግ ተቀባብዬ ተለያይተንም የማስበው ስለእሷ ነበር። ትዳር እንደ ኑሮ ተወዶባቸው ባላሰቡት የሚውሉና ባልጠበቁት የሚገኙ እህቶችን ኑሮ ስለማውቀው (አይ ደላላ መሆን ስንቱን እንደሚያሳይ እኮ)፣ በእሷ ውስጥ ስለእህቶቻችን ፈተና ሳላስብ እየተብሰለሰልኩ ዋልኩ። በኋላ ደግሞ ከአንድ ደላላ ወዳጄ ጋር ባለመቻቻል ሳቢያ በፈረሰ ትዳር ምክንያት እኔ ነኝ ያለ ዘመናዊ ቤት ልናሻሽጥ ስንዋከብ፣ ‹‹አስቲ ስማኝ እባክህ…›› አልኩት። ‹‹ምን ልስማህ?›› አለኝ። ‹‹ጎጆ እንደ ቀልድ ፈርሶ አንተ በድለላ ቤት ስታሻሽጥ የሚሰማህ ስሜት ምንድነው?›› ስለው፣ ‹‹እኔ ከሰው የኮንትራት ኑሮ ምን አለኝ? ቤቱ ቶሎ ገዥ አገኘ አላገኘ እያልኩ ላስብ ወይስ ሌላ? ምን ሆነሃል? እንዲህም ሆነን የምናገኘው ገንዘብ ረድኤት አልኖረው ብሎ አስመርሮናል አንተ ትፈላሰፋለህ…›› ብሎ የምሩን ተቆጣኝ። ለወዳጄ አብዛኛውን ጊዜ ሕግ የማይዳኘው፣ የማያመዛዝነውና የማይፈርደው ነገር አገር ሲያፈርስ መኖሩን ለማስረዳት ሰዓት አልነበረኝም። ዘንድሮ እኮ ሁሉም በተመቸው ጎዳና እየተመመ እውነቱን ከሐሰት እንዲለይ ማስረዳት ዳገት እየሆነ ነው፡፡ ዕድሜ ለቲክቶክና ለዩቲዩብ ወሬው ተሰልቆ የሚቀርበው ከዚያ ስለሆነ ምንጭ ሳያረጋግጡ መጋት ነው፡፡ ይብላኝ ለተበሉት!
ወዲያው ቀኑ ሊመሽ የቀረው ሰዓት የቤቱን ገዥ አፈላልጎ ለማግኘት እንደማይበቃን ተገንዝበን፣ የነገ ሰው ይበለን ተባብለን ስንለያይ ስልኬ ጠራ። ሳነሳው ቦሌ ኢድና ሞል ወረድ ብሎ በቅርቡ እልል ባለ ድግስ የተመረቀ ዘመናዊ ሥጋ ቤት ቶሎ ና ብሎ አንድ ወጣት ኢንቨስተር ነበር የጠራኝ። ‹‹ሰላም አይደለም?›› ከማለቴ ሳያስጨርሰኝ፣ ‹‹ቶሎ ድረስ ብዬሃለሁ…›› ብሎ ስልኩን ጆሮዬ ላይ ዘጋው። በድለላ ሥራ ውስጥ አንዱ መመርያ ቶሎ ና ሲባል በፍጥነት መድረስ ስለሆነ ከብሥራተ ገብርኤል አካባቢ በራይድ ወደ ቦሌ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቢዋይዲ የሚዘውረው የራይድ ሾፌር የመልካሙ ተበጀን፣ ‹‹ኧረ መላ ምቱ ዘመድ ወዳጆቼ ዓይነ አፋር ሆኛለሁ ዓይነ አፋር ወድጄ…›› የሚለውን ጥዑመ ዜማ ሲከፍተው፣ እኔ ደግሞ ያ ደግ ዘመን ትዝ እያለኝ የያኔው ሰው ሁኔታ በዕዝነ ልቦናዬ ተከሰተብኝ፡፡ እንደ ዛሬው ሞጭላፋው፣ አስመሳዩ፣ አጭበርባሪው፣ ዋሾውና ቀጣፊው ሳይበዛ በፊት የእኛ ሰው በፈሪኃ ፈጣሪ፣ በይሉኝታና በቅንነት ያሳለፈው መልካም ጊዜ ሲታሰበኝ ራሴን ጭምር እየታዘብኩ ነበር፡፡ አንዲት ሴት ያፈቀረ ምስኪን የውስጡን አውጥቶ መናገር ጭንቅ ሆኖበት ለስንት ዓመታት የተሰቃየበትን ታሪክ የሰማነውም ያኔ ነበር፡፡ ለዚህም እኮ ነው መልካሙ ተበጀ በዚያ የሚያምረው ድምፁ፣ ‹‹ኧረ መላ ምቱ ወዳጅ ዘመዶቼ…›› እያለ ያቀነቀነው፡፡ እያንዳንዱ ዘመን የማያሳየን የለም እናንተ!
የራይድ አሽከርካሪው በመልካሙ ጀምሮ በሙሉቀን መለሰ ቀጥሎ በአለማየሁ እሸቴና በአስቴር አወቀ ድንቅ ዘፈኖች ያስዋበው ጉዞዬ ቦሌ የተቀጠርኩበት ቦታ ስደርስ ተጠናቀቀ፡፡ አዲሱ ዘመናዊ ሥጋ ቤት ስደርስ ዓይኔን ማመን አቃተው፡፡ ከፊት ለፊቱ አምሮ የተሠራው ጎዳና ማዶ ላይ ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል በተዘረጋው አንደኛው ረድፍ ላይ የተሰደሩትን ዘመናዊ አውቶሞቢሎች ላየ፣ እንደተባለውም በወር 3.2 ሚሊዮን ብር ኪራይ ይከፈልበታል ቢባል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ደረጃውን ወጥቼ ዋናው መግቢያ በስተቀኝ ላይ ያለው የሥጋ ክፍሉ ብቻ በልዩ ሁኔታ ተሠርቶ ከእነ ሠራተኞቹ ሲታይ፣ አምሮትን ከመቀስቀስ አልፎ ወደፊት በአዲስ አበባ ምን ተዓምር ሊፈጠር ይችል ይሆን ያሰኛል፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ወደ ዋናው አዳራሽ ሳመራ በግራና በቀኝ ካለው በጣም ሰፊ የእንግዶች መስተናገጃዎች በተጨማሪ በግራና በቀኝ ተጨማሪ ሁለት ባልኮኒዎች ሰዎች ግጥም ብለዋል፡፡ ለማንኛውም ወደ መታጠቢያው ጎራ ስል ንፅህናው ሌላ ዓለም ይመስላል፡፡ እጄን አፀዳድቼ ጨርሼ ወደ ደወለልኝ አለቃዬ ስልክ ከመደወሌ በፊት፣ በጥቁር ጉርድና በነጭ ሸሚዝ ካሸበረቁ ውብ አስተናጋጆች ጋር ፊት ለፊት ግጥም አልኩ፡፡ ወደ ቪአይፒና ቪቪአይፒ መግቢያው ላይ ስለነበሩ ቆም ብዬ ማሰላሰል ስጀምር ስልኬ ጠራ፡፡ ገላገለኝ ማለት ይቀላል!
From The Reporter Magazine
እነዚያን ውብና የሚያሳሱ ቆነጃጅት እያየሁ ስልኬን ሳነሳ፣ ‹‹ቀጥ ብለህ ወደ ቪአይፒ ግባ…›› ብሎ ሲያዘኝ ሰማሁት፡፡ እንደ መርበትበት እያደረገኝ ወደ ቪአይፒ ሳመራ ውቦቹ ፍጥረቶች ካፖርቴንና ባርኔጣዬን በመገረም እያዩ ወደ መሄጃዬ ጠቆሙኝ፡፡ በእርጋታ እየተራመድኩ ወደ ተባልኩበት ስቃረብ ፊት ለፊት በኩል በቆነጃጅት የተከበበው ጠሪዬ በእጁ ምልክት አሳየኝ፡፡ የቤቱን ንፅህና፣ እንዲሁም በክፍሉ ውስጥ ያሉትን በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ኮበሌዎችንና ኮረዳዎችን ሳይ ያለ ቦታው የበቀለ ተክል መሆኔ ተሰማኝ፡፡ ይህንን ጉድ ውዷ ማንጠግቦሽ ብትሰማ ምን ይሆን እያልኩ ቀጥ ብዬ ወደ ደዋዬ ገሰገስኩ፡፡ ደርሼ ለመኳንንት የሚገባ ሰላምታ በአንገቴ አቅርቤ የሚቀጥለውን ስጠባበቅ፣ ‹‹አቶ አንበርብር ና እዚህ ጋ ተቀመጥ…›› ብሎኝ ከእሱና ከቆነጃጅቱ ፈንጠር ብሎ የተዘጋጀ ሁለት ሰዎች የሚያስተናግድ ጠረጴዛ ጋ አመለከተኝ፡፡ በአክብሮት እጅ ነስቼ ተቀመጥኩ፡፡ ፍላጎቴ ሳይጠየቅ ግማሽ ኪሎ ጥሬ ሥጋና ቢራ እንዲመጣልኝ ደዋዬ አዘዘ፡፡ ምግቡና መጠጡ እስኪመጣ በአስቸኳይ ከብራስ እስከ አትላስ ባለው ሥፍራ ገባ ያለ ፈርኒሽድ አፓርታማ እንድፈልግ ትዕዛዝ ተሰጠኝ፡፡ በልቼና ጠጥቼ አመስግኜ ልሄድ ስል በሞባይል ባንኪንግ ቀብድ ተሸጉጦልኝ ተሸኘሁ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያንን ዘመናዊ ሥጋ ቤት እያሰብኩ እንቅልፍ አጥቻለሁ፡፡ ቅዠት እንዳይመስላችሁ!
ይህ በዚህ እንዳለ በፖለቲካው ሠፈር ደግሞ ቡድን መሥርቶ ተያይዞ ከሚነዳው ጀምሮ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በጥቅም ትስስርና በመሳሰሉት መናጀሱ ያገረሸበት ይመስላል፡፡ ኧረ ሆታ እስከ መቼ ጎበዝ? ጠልዘን ስናገባ በደስታ ተንጫጭተን፣ ተጠልዞ ሲገባብን በንዴት ጮኸን፣ ፈሩን በለቀቀ እሰጥ አገባ ውስጥ ሳንደማመጥ ትውልድ መጥቶ ትውልድ እየሄደ አለን የምንለው ተስፋ ምኑን በእግሩ ቆመው? እውነቴን እኮ ነው። መቼ ዕለት ነው ከባሻዬ ጋር ዕቁብ ጥለን ስንመለስ (ባሻዬ ብዙ ጊዜ ዕጣ ሳይደርሳቸው ስለሚቆይ የማይፈለፈል ዕንቁላል እየጣልኩ ይላሉ ሲቀልዱ)፣ ‹‹ምናለበት ይኼን በየቦታው እያናጀሰ እርስ በርስ የሚያጣላንን ዲያቢሎስ በጋራ ብናስወግድ አንበርብር? ዕድሜ ልክ እንዲሁ በነገር መቆርቆዝ?›› ሲሉኝ ነበር። ‹‹ከፈጣሪ ሰው እየቀደመ ድሮስ ምን ልንሆን ነበር?›› የምትለው ደግሞ የእኔዋ ማንጠግቦሽ ናት። በዚህ በዚያም ነገሩን ስትደማምሩት በአጠቃላይ ተዛዝኖና ተባብሮ ከማደግ ይልቅ፣ ተቧድኖ እንዲራገጥ የተረገመ የሚመስለው የበዛ ይመስለኛል። ብልጦቹ ከነገር ርቀው የሚሠሩት በልፋታቸው፣ የማይሠሩት ደግሞ በንፋስ አመጣሽ በረከታቸው የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ጣፋጭ ሕይወት ያጣጥማሉ፡፡ ያላደላቸው ደግሞ ነጋ ጠባ እየተባሉ ጦሳቸው ለንፁኃን ይተርፋል መጥኔ ነው የሚባለው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት፡፡ የዕለቱ ማሳረጊያ የተለመደው ግሮሰሪያችን ስለሆነ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር በጊዜ ተሰይመናል፡፡ ባለፈው ሰሞን እንደ በረዶ ቀዝቅዞ የነበረው ግሮሰሪያችን ምን እንደተገኘ አይታወቅም፣ ከተለያየ የኑሮ ደረጃና ማኅበረሰባዊ ጥንቅር የተሰባሰብን እንደ ምርጫችን አዘን እየተጎነጨን ነው፡፡ ‹ሒሳብ በግል ወሬ በጋራ› በሚባለው ያልተጻፈ ሕግ መሠረት፣ ቢራውንና አልኮሉን እየተጎነጨን ወሬ ስለቃው ቀጥሏል፡፡ ‹‹ጎበዝ እንግዲህ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ያህል የሚጠበቀው ምርጫም ተጠናቆ…›› እያለ አንዱ አብረውት ለተቀመጡ ወዳጆቹ መናገር ሲጀምር፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ምርጫ ባለቀ ማግሥት የሁላችንም ዓይኖች መንግሥት ላይ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር የመንግሥት ተከታይ ዕርምጃዎች ለአገርና ለሕዝብ የሚኖራቸው ፋይዳ ነው…›› ብሎ ሌላው ይመልሳል፡፡ በዚህ መሀል ነበር አንዱ ሞቅ ያለው፣ ‹‹ሕግና ሥርዓት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ እየተጣሰ ጥቃት እንዳይፈጸም መጠንቀቅ ካልተቻለ ስካራችን ተባብሶ ይቀጥላል…›› ብሎ በፌዝ ስሜት ሲስቅ ሌሎችም አብረውት መሳቅ ጀመሩ፡፡ ይኼን ጊዜ ምሁሩ ወዳጄ፣ ‹‹አንበርብር እንደ ዋዛ የሚነገሩና ቀልድ የሚመስሉ ንግግሮች ውስጥ ነው ሕመማችን ያለው…›› ሲለኝ ከሰዎቹ ንግግር በስተጀርባ ያለው ስሜት ታሰበኝ፡፡ የሁሉም ነገሮቻችን የተቃርኖ ስሜቶች እንዲህ ይሆኑ እንዴ እያልኩ እያብሰለሰልኩ መሽቶ ወደ ቤታችን ስናዘግም ሐሳቡ ሰቅዞ ይዞኝ ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!
