- አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጣልቃ ገብቶ ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ እንዳለበትም ተጠቁሟል
በሃይማኖት ደስታ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የሕወሓት አመራሮች የገቡበት ውጥረት ወደ ሌላ ጦርነት ከማምራቱ በፊት የፌዴራል መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፣ ‹‹አገርን የሚያስተዳድረው መንግሥት፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች የሚፈቱበት መንገዶችንና አማራጭ ሐሳቦችን ሰፋ አድርጎ በማጤን መፍትሔ መፍጠር አለበት፤›› ብለው እንደሚያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ለዚህም ሁለቱ አካላት ውይይቶች የሚያደርጉበትን መንገድ ሊያመቻች ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ሕወሓት ከገቡበት የሥልጣን ሽኩቻ ወጥተው፣ ችግራቸውን በድርድር መፍታት አለባቸው ያሉት ሰብሳቢው፣ ከፌዴራል መንግሥት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ልሂቃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች አካላት ጣልቃ በመግባት ወደ ጦርነት የሚደረገው ሒደት እንዲገታ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ነው የተጎዳነው ብሎ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ኃላፊው፣ የክልሉ ማኅበረሰብ የሰላምና የልማት እንጂ የጦርነት ድምፅ መስማት እንደማይገባው አስገንዝበዋል። በክልሉ ያሉ አመራሮች ከግል ፍላጎት ወጥተው ለማኅበረሰቡ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በበኩሉ፣ ፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚታየውን ውጥረት በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል ሲል መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል። ፓርቲው በመግለጫው፣ ከፕሪቶሪያው ሥምምነት በኋላ አንፃራዊ ሰላም እየታየበት የነበረው የትግራይ ክልል ሁኔታ፣ የፌዴራል መንግሥቱ በስምምነቱ መሠረት ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱና አካታች የሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት አለመመስረቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት የእርስ በርስ ፍትጊያ ውስጥ ገብቶ በትግራይ ክልል ውጥረት ነግሷል ብሏል፡፡
በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ተከትሎ በክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው ግጭት ቀስቃሽ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ግን፣ በጠቅላላው እንደ አገር በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ንፁኃን ዜጎች ላይ የሚያመጣውን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ የሰላምና የደኅንነት አስከፊ አደጋ አሳሳቢ እንደሆነ ፓርቲው ገልጿል።
ኢዜማ፣ የሕወሓት አመራሮች ምንም ሳይፀፀቱ ሥልጣንን ጠቅልሎ በመያዝ ግብግብ ውስጥ ገብተው ለሌላ ዙር ግጭት የሚጋበዙ ከሆነ በተለይ በትግራይ ውስጥ ያሉ ዜጎች ሊረዱት የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ፣ ይህ ስብስብ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የቆመ እንዳልሆነ ነው ብሏል፡፡
በዚህ የፖለቲካ ሥልጣን ጥምን ለማርካት በሚደረግ መገፋፋት ውስጥ ባለመሳተፍ እንዲሁም ግጭት የሚቀሰቅሰውን የትኛውንም ኃይል በግልጽ በመቃወም የክልሉ ነዋሪ በአንፃራዊነት ያገኘውን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል ሲልም ፓርቲው አሳሰቧል፡፡
በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በክልሉ የተፈጠረውን ትርምስ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ሊያስቆም ሲገባ ይህን አለማድረጉ ሳያንስ፣ አሁንም ራሱን እንደሩቅ ተመልካች በመቁጠር በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ መፍትሔ እንዲመጣ እየሠራ እንዳልሆነ የገለጸው ኢዜማ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነትን በአግባቡ እንዲፈጸም ባለማድረጉ ንፁኃን ዜጎች በሕይወታቸውና በአካላቸው ዋጋ እየከፈሉ መምጣታቸው ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን አውቆ አሁንም ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በሚያስችል ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የመንግሥትነት ሚናውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡