ውፍረትን ለመቀነስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በእንዳንዶች ዘንድ እንደ ቅንጦት ተደርገው ሲወሰዱ ይስተዋላል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ውፍረትም ከምቾት ወይም አብዝቶ ከመመገብ ብቻ የሚመጣ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም ውፍረት ወይም የሰውነት ክብደት የሚጨምረው ከምቾትና አብዝቶ ከመመገብ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በርካታ ሰዎች ከውፍረት ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች ሲሰቃዩም ይስተዋላሉ፡፡ ከአቅም በላይ የሆነውን የሰውነት ክብደታቸውን ለመቀነስ የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ባሻገር ሌሎች መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ሁሉ ሲያደርጉም ይታያሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ከችግራቸው ለማላቀቅ የሥነ ምግብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የውበት ባለሙያዎች ተቋማትን ከፍተው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ማስተር ሔኖክ ኪዳነ ወልድ ከውፍረት ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ በሽታዎች የሚሰቃዩ፣ ነገር ግን ውፍረታቸውን ለመቀነስ የሚጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ ሰዎችን በማሰባሰብ ‹‹ጀግና ትውልድ›› በሚል የ 90 ቀናት ሁለንተናዊ ለውጥ ማዕከል በማቋቋም በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ ጤንነቱን የጠበቀ አካሉና ሥነ ልቦናው የጠነከረ ማኅበረሰብን ከመፍጠር አኳያ ምን እየሠራ ነው? የሚለውን በተመለከተ የማዕከሉን መሥራችና ኃላፊ ማስተር ሔኖክን፣ አበበ ፍቅር አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- ጀግና ትውልድ ለማፍራት በሚል ያለመው ፕሮጀክት መቼ ተጀመረ?
ማስተር ሔኖክ፡- ፕሮጀክቱ ከመቋቋሙ በፊትም በግሌ በክፍያ ስፖርት የማሠራቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የነበረባቸውን ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት መቀነሳቸውንና ከተለያዩ በሽታዎች ነፃ መሆናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያጋሩበት ወቅት ብዙ ሰዎች ዕድሉን ማግኘት እየፈለጉ ነገር ግን በገንዘብ እጥረት ማግኘት እንዳልቻሉ ለመረዳት ችለናል፡፡ በነፃ ዕድሉን ብናገኝ የሚሉ ሰዎች ሲበራከቱ እኛም ስፖርት በመሥራት ጤናቸውን መጠበቅ እየፈለጉ ነገር ግን የመክፈል አቅም ስለሌላቸው ብቻ የሚቸገሩ ሰዎችን በማሰባሰብ ለምን አላግዝም በሚል አሰብኩ፡፡ በዚህም አቅም ገድቧቸው ግን ስፖርቱን መሥራት የሚፈልጉ ሰዎችን በማሰባሰብ በነፃ ማሠራት ጀመርኩ፡፡ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ሥራው ሲጀመር በሁለትና በሦስት ሰዎች ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ሃያና ሰላሳ መቶ እያልን በምዕራፍ እየከፋፈልን ብዙ ሰዎችን በነፃ ማሠልጠኑን ቀጠልን፡፡ በመጨረሻም የተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ ሲመጣና በርካታ ሰዎች መሳተፍ ስለጀመሩ ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ከጤና ቢሮ ጋር በመሆን አንዳንድ ነገሮችን እያገዙን እኛ ደግሞ በሙያችን በማገልገል እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዓላማችሁ ምንድነው?
ማስተር ሔኖክ፡- ተስፋ ቆርጠው ቤታቸው የተቀመጡ ሰዎችን በአካልና በሥነ ልቦና በማበረታታት ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ብሎም ለአገራቸው አምራች የሆኑ ጀግና ዜጎችን መፍጠር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ውፍረትን ለመቀነስ ስፖርት መሥራት ቅንጦት ሊመስል ይችላል፡፡ ይኼን ሐሳብ እንደ ባለሙያ እንዴት ታየዋለህ?
ማስተር ሔኖክ፡- እንደሚባለው ትንሽ ያስቸግራል፡፡ አንዳንድ ሰው በልቶ ለማደር ይቸገራል፡፡ ሌላው ደግሞ በውፍረትና ከውፍረት ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች ሲሰቃይ ይስተዋላል፡፡ የወፈሩ ሰዎች ጤናቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ውፍረትም፣ በችግር ምክንያት መመገብ አለመቻልም ችግሮች ናቸው፡፡ እኛ ባለን ሙያና ዕውቀት በኮሌስትሮልና በስኳር እንዲሁም በተያያዥ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎችን ለማዳን ያለንን ሙያ ከፍለው ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች በነፃ እናገለግላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሰዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል?
ማስተር ሔኖክ፡- በመጀመርያው ዙር አንድ ሺሕ ሰዎችን ለሦስት ወር አሠልጥነን ጨርሰናል፡፡ አሁን ላይ ሁለተኛ ዙር ለመጀመርና ሁለት ሺሕ ሰዎችን ለማሠራት ምዝግባ በማካሄድ ላይ ነን፡፡ ሁለት ሺሕ ሲሞላ የዚህን ዙር ምዝገባ እናቆማለን፡፡ ጠቅላላ በዚህ ዓመት አሥር ሺሕ ሰዎችን ለማሠራት ነው ዕቅዳችን፡፡
ሪፖርተር፡- እየሰጣችሁት ያለው ሥልጠና ወደ ገንዘብ ቢቀየር ምን ያሀል ሊተመን ይችላል?
ማስተር ሔኖክ፡- በጂምናዚየም ሒሳብ ወደ ገንዘብ ብንቀይረው አንድ ሰው ለሦስት ወር 30 ሺሕ ብር ከፍሎ ነው የሚሠለጥነው፡፡ አሥር ሺሕ ሰዎች እያንዳንዳቸው 30 ሺሕ ሲከፍሉ ሒሳቡ ወደ ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር ይተመናል እንደማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሠልጣኝ በሦስት ወር ቆይታው ምን ዓይነት ሥልጠናዎችን ነው የሚወስደው?
ማስተር ሔኖክ፡- በአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን ጨምሮ ስለ ሥርዓተ ምግብና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎችን በተመለከተ በሳምንት አንድ ቀን በተለያዩ ዶክተሮችና በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሰጣቸው እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም ሰዎች አካላቸው ከተስተካከለና ጤናቸው ከተጠበቀ በኋላ አምራች እንዲሆኑ አስተሳሰባቸውና የአኗኗር ባህላቸው መቀየር አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሰዎች ውፍረት በምቾት የሚመጣ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ውፍረት ከምቾት የሚመጣ ነው ትላለህ?
ማስተር ሔኖክ፡- ውፍረት የምቾት ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ ሴቶችን ብናይ ሲያረግዙና ከወለዱ በኋላ የሚያሳዩት ለውጥ አለ፡፡ በዘር በሚመጣ የሆርሞን መቀያየር እንዲሁም በጭንቀትና በሌሎችም ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ምቾትም አንዱ የውፍረት ምክንያት ነው፡፡ ይህም የሚከሰተው ምንም እንኳን የሁሉም ሰው አስተሳሰብ ነው ተብሎ ባይወሰድም፣ አንድ ሰው ከብዙ ጥረት በኋላ የሚፈልገውን ሁሉ ማግኘት ሲጀምር የሚያስፈልገውን ሳይሆን ያማረውንና የጣፈጠውን ሁሉ ይመገባል፡፡ ጤናማ ያልሆኑ ሐሳቦች ወደ አዕምሮ ሲገቡ አዕምሮን እንደሚያበላሹት ሁሉ ያልተመጣጠኑ ምግቦችም ሲወስዱ ጤናን ያውካሉ፡፡ ሰውነታችን በቀን ማግኘት ከሚገባው በላይ ካሎሪን በሚቀበልበት ወቅት ከሚፈለገው በላይ ያለው ካሎሪን በስብ መልክ ሲቀመጥ፣ በጡንቻ ውስጥና ከጡንቻዎቻችን በላይ እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን የሚሠራጭ መሆኑም ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሕመሞች የትኞቹ ናቸው?
ማስተር ሔኖክ፡- በሰውነት ውስጥ ያለው ስብ መጠኑ እየጨመረ ሲሄድ በደም ስር ይገባና እንደ ኮሌስትሮል፣ የደም ሥርን በማጥበብ የደም ግፊት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ስትሮክና ሌሎች ሕመሞች እየቆዩ ሲሄዱ ወደ ካንሰር ይቀየራሉ፡፡ የውፍረት መጨመር መዘዝ በዚህ አያቆምም ሕይወትን እስከ ማሳጣትም ሊደርስ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- መነሻችሁ ጀግና ትውልድ የሚል ነው፡፡ ጀግና ትውልድ እንዴት ነው የሚፈጠረው?
ማስተር ሔኖክ፡- ጤናማና አምራች ዜጎችን ለማፍራት የብዙዎቻችን ጥረት አይስተዋልም፡፡ አንዳንዶች በቀን ሦስት ጊዜ የሚበሉበት፣ ሌሎች ደግሞ ምን በልተን ነው የምንውለው ብለው የማይጨነቁባትን አገር ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የሚፈጠረው ደግሞ ሁላችንም ጀግኖችን ለትንሽ ነገር የማንንበረከክና ተስፋ የማንቆርጥ ስንሆን ነው፡፡ ታላቅ አገር ለማየትና ለመገንባት ጀግና ትውልድ ማፍራት ግዴታ ነው፡፡ የሚጠይቅ፣ የሚያስተውል፣ ችግሮችን ተቋቁሞ የሚሻገር ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ እኔም የሕይወት ተልዕኮዬ ይኼ በመሆኑ፣ ታላቅ አገርን ለማየት የሚቻለው ጀግና ትውልድ በመፍጠር በመሆኑ በቻልኩት አቅሜ ይህንን ሥልጠና እየሰጠሁ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ ሰዎች በነበሩበት ቢቀጥሉ በበሽታ ተጠቅተው ነገ ሜቄዶኒያ ገብተው ሊገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ እዚያ ሳይደርሱ ከደረስንላቸው ሜቄዶኒያ ያሉትን የሚረዱ ይሆናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ድጋፍ ያደርግላችኋል?
ማስተር ሔኖክ፡- እኔ በስፖርቱ ዘርፍ መሥራት ከጀመርኩ ከ24 ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡ መንግሥት ስፖርቱ ላይ ያለው ድጋፍ አበረታች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል ምክንያታችን ስፖርት መሥሪያ የለም የሚል ነበር፡፡ ወጣቶች መሄጃ ወይም መዝናኛ ሲያጡ ይጠጣሉ፣ ያጨሳሉ፣ ኳስ የሚጫወቱበትም እየጠፋ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ትውልድ ቢጠፋ አይፈረድበትም፡፡ አልባሌ ቦታ ለመገኘት ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ በቂ የመዝናኛ ሥፍራዎች አለመኖር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በየሰፈሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እየታደሱና ምቹ እየሆኑ ነው፡፡ የኛን ፕሮጀክት መንግሥት የወዳጅነት አደባባይን መጠቀም ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ያግዘናል፡፡ መንግሥት መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ይኖርበታል፣ ኃላፊነቱም ነው፡፡ መሠረተ ልማቶች ሲሟሉ ደግሞ መሥራት የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለማኅበረሰቡ በተለይ ደግሞ ገንዘብ ከፍለው አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በነፃ ለማገዝ ከማን ምን ይጠበቃል?
ማስተር ሔኖክ፡- አቅም ለገደባቸው የሚሰጡ ነፃ አገልግሎቶችን ለማበረታታት ባለሀብቶች በገንዘባቸው ባለሙያዎችም በሙያቸው ማገዝ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ሥልጠና የሚመጡ ሰዎችን ስንመለከት ብዙዎቹ የስፖርት ልብስ አይለብሱም፡፡ ቆዳ ጫማ አድርገው ጅንስ ሱሪ ታጥቀው የሚሠሩ አሉ፡፡ በዚያ ላይ ወደ ወዳጅነት አደባባይ የመግቢያ ክፍያ አለው፡፡ የትራንስፖርት ወጪ አለባቸው እነዚህና መሰል ትንንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ከባድ ክፍተቶች ሰዎች በቀጣይነት እንዳይሠሩ ያግዷቸዋል፡፡ ድርጅቶችና የግል ባለሀብቶች አንዳንድ ወጪዎቻቸውን ቢሸፍኑላቸው ተጋግዘን ጤናማና ጀግና ትውልድን ለመገንባት አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር እንችላለን፡፡