የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን የመለየት፣ ረቂቅ ሕጎችን አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳልሆነ በጥናት ተመላከተ፡፡
ይህ የተገለጸው የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት በ2018 በጀት ዓመት ካከናወናቸው አምስት ጥናቶች አንዱ በሆነው፣ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችል የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የሕግ አወጣጥ በኢትዮጵያ ጥናት ግኝት ነው፡፡
ጥናቱን ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የማፀደቂያ ዓውደ ጥናት ላይ ያቀረቡት፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሆነልኝ ኃይሉ የተጣጣሙ የኢንቨስትመንት፣ የገበያና የአሠሪና ሠራተኛ ሕግጋትና ወጥነት ያላቸው የንግድ ሕግጋት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመመሥረት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴሬሽ ምክር ቤት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚያስችሉ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣባቸው የሚገቡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን የመለየት ሥልጣንና ኃላፊነት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 እና 62 እንደተሰጠው ተጠቅሷል፡፡
ሆኖም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን የመለየት፣ የማነሳሳትና ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ ሕጋዊ ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢሰጥም፣ በተግባር ግን ምክር ቤቱ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት ውስንነት ምክንያት ሚናውን እንዳልተወጣ የጥናት ግኝቱ ያስረዳል፡፡
እነዚህ የሕግ ሐሳቦች የሚመነጩት፣ የሚረቀቁትና መደበኛውን የሕግ አወጣጥ ሒደት ተከትለው ለፓርላማ የሚቀርቡት፣ በቀጥታ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት አማካይነት መሆኑን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተጨባጭ ሚና አስፈጻሚዎቹ ያረቀቋቸው ሕጎች የክልሎችን ሥልጣን አለመጋፋታቸውን በማረጋገጥና የጋራ የምክክር መድረኮችን በመጠቀም ይሁንታ በመስጠት ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን ለይቶ ለማውጣት የሚያስችል ግልጽ የሆነ የፖሊሲም ሆነ የሕግ መመዘኛ መሥፈርት አለመኖሩን የሚያስረዳው የጥናቱ ግኝት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በየክልሉ ያለውን የተለያየ አፈጻጸም በጥናት በመገምገም የሰዎችን፣ የካፒታልንና የሸቀጦችን ነፃ እንቅስቃሴ የሚያረጋግጡ፣ በኢኮኖሚ አንድነትን የሚያጠናክሩና ከአንድ ክልል በላይ ተፈጻሚነትና ተፅዕኖ ያላቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚያስችሉ ይፋዊ መመዘኛዎችን ማውጣት እንዳለበት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
From The Reporter Magazine
የጥናቱ መረጃዎች የተሰበሰቡት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም መሆኑን፣ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከጉምሩክ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም አግባብነት ያላቸው ሕጎች፣ የተመረጡ አገሮች ልምድና ተሞክሮዎች፣ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸው ጽሑፎች፣ በሕግ ማውጣት ሒደት በአርቃቂዎች የተያዙ ቃለ ጉባዔዎችና አግባብነት ያላቸው የምርምር ጽሑፎችና ሰነዶች ተዳሰዋል ተብሏል፡፡