- በከሰል ምርትና ዝውውር ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም ተገልጿል
በአዲስ አበባ ከተማ የድምፅ ብክለት በሚያደርሱ ተቋማት ላይ ይጣል የነበረው ቅጣት ከፍ ብሎ መመርያው ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና አማካሪና የአካባቢ ብክለትና አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ተወካይ አስተባባሪ አቶ አዱኛ ወንድሙ፣ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ክትትልና ቁጥጥር ከሚያደርግባቸው የአካባቢ ብክለት መንስዔ ዓይነቶች መካከል አንዱ የድምፅ ብክለት ነው ብለዋል፡፡ ይህ የብክለት ዓይነት የሚያስከትለው ቅጣት አነስተኛ መሆን ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ተናግረዋል። ተቋሙ የብክለት ቁጥጥር አዋጅን መሠረት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚተገበር መመርያ ማዘጋጀቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል።
መመርያው የችግሩን አሳሳቢነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የድምፅ ብክለት በሚያደርሱ ተቋማት ላይ ከዚህ በፊት ይጣል በነበረው አስተዳደራዊ ቅጣት ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑን፣ አቶ አዱኛ ጨምረው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከድምፅ ብክለት ጋር ተያይዞ የሚጣለው ቅጣት አነስተኛ መሆኑንና ትንሹ ቅጣት አምስት ሺሕ ብር ሲሆን፣ ትልቁ ደግሞ 25,000 ብር እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንን የቅጣት እርከን የሚያሻሽልና የብክለት ቁጥጥር አዋጅን መሠረት ያደረገ መመርያ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ለመተግበር መረቀቁንና ለከተማ አስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ መላኩን አቶ አዱኛ አስረድተዋል። በዚህ መመርያ መሠረት የሚጣለው ቅጣት የበለጠ አስተማሪ፣ አጥፊዎችን ቆንጠጥ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅና በ2019 በጀት ዓመት የተሻለ ጠቀሜታ ያመጣል የሚል ዕሳቤ መኖሩን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ በ12,376 አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት ላይ የድምፅ ብክለት ቁጥጥርና ክትትል መደረጉን፣ ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑንና ይህም የሆነበት ምክንያት የሆቴሎችና የመጠጥ ቤቶች በስፋት መከፈት ከምሽት ጭፈራ ቤቶች መኖር ጋር ተዳምሮ መሆኑን አቶ አዱኛ ጠቅሰዋል።
የድምፅ ብክለትን በተመለከተ ማኅበረሰቡ ለባለሥልጣኑ ቅሬታዎችን እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ አዱኛ፣ በዚህም ምክንያት ከሌሎች የብክለት ዓይነቶች አንፃር የሚደረገው ቁጥጥር መጨመሩን አስረድተዋል። ከተቀመጠው ስታንዳርድ በላይ ድምፅ ጨምረው የተገኙ አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት፣ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ማሸግ የደረሰ ዕርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።
From The Reporter Magazine
ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎችን ጨምሮ በ3,116 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፣ 28 ያህሉ ደግሞ መታሸጋቸውን ገልጸዋል። በገንዘብ የተላለፈው ቅጣት 140,000 መሆኑን፣ የሚጣለው ቅጣት አነስተኛ መሆን የተሰበሰበው ገቢ አነስተኛ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።
የባለሥልጣኑ የሥርዓተ ምኅዳርና ማዕድን ፈቃድ አሰጣጥ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማናዬ ጫኔ በበኩላቸው፣ የተቋም ግንባታን ለማረጋገጥ የአሠራር ሥርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግና የተለያዩ ሕጎች እየወጡ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል።
ለአብነትም የኮንስትራክሽን ማዕድን ፈቃድ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 191/2018 ተጠቃሽ መሆኑን፣ ከዚሁ በተጨማሪ የደን ሀብት ቁጥጥርና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መመርያዎች ወደ ፍትሕ ቢሮ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
From The Reporter Magazine
ባለሥልጣኑ የደንና ደን ሀብት፣ የዛፍ ቆረጣ፣ እሴት የተጨመረባቸው እንደ ጣውላና መሰል ምርቶች ዝውውር ፈቃድ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ይህ መመርያ የደን ልማት መጠበቅና አጠቃቀም አዋጅን ተከትሎ እንደሚወጣ፣ ዛፎች እንዴት ተቆረጡ? ለምን ተቆረጡ? መጨረሻቸውስ የት ነው? የሚለውንና ለመቆጣጠርና ሕገወጥ የደን ሀብት ብክነትንና የዛፍ ቆረጣን ለመከላከል እንደሚረዳ ተናግረዋል።
መመርያው በአዲስ አበባ ከተማ ቁጥጥርና ክትትል የማይደረግበት የከሰል ምርት ከየትና እንዴት ይመጣል የሚለውን ምላሽ መስጠት እንደሚያስችልና በንግድ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ይህ መመርያ በተለይ የብዝኃ ሕይወትንና ሥነ ምኅዳርን በደንብ ሊያስጠብቁ የሚችሉ አገር በቀል ዛፎች ያላግባብ እንዳይቆረጡ ለመቆጣጠር የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል። ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው ዛፍ የሚቆርጡ አካላት በሜትር ኪዩብ ተለክቶ የሚጣልባቸውን የባለቤትነት (Royalty) አስተዳደራዊ ቅጣትን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መመርያ በአዲስ አበባ ከተማ ሳር ማንጠፍን ጨምሮ በደንና በደን ሀብት የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች የሚሰጡት አገልግሎት ሳይንሳዊ መሥፈርቶችን አሟልቷል ወይም አላሟላም የሚለውን ለመለየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። መመርያዎቹ በ2019 በጀት ዓመት ፀድቀው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አክለዋል።
ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ 88 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ ከዚህም ውስጥ ከማዕድን ፈቃድና ዕድሳት ዘርፍ ብቻ የተሰበሰበው 81 ሚሊዮን 403 ሺሕ 930 ብር መሆኑን አቶ ማናዬ አክለዋል።