- የውጭ ዜጎችና ኢትዮጵያውያን በሐሰተኛ ሰነድ የማጭበርበር ድርጊት ተጠያቂ መደረጋቸው ተገልጿል
በ2018 በጀት ዓመት ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርቶችን ጨምሮ በተሰጡ አገልግሎቶች ከ42.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ይህን ያለው ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን ሲገመግም ነው። አግልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርቶች ለዜጎች መሰጠት መቻሉ በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ተነግሯል።
በበጀት ዓመቱ 1,046,286 ቪዛዎች፣ ለ32,952 ትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያዎች (ቢጫ ካርድ)፣ እንዲሁም ለውጭ ዜጎች 21,163 ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በመስጠት የተሳካ የዕቅድ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አገልግሎቱ ገልጿል።
ከፓስፖርት፣ ከቪዛ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያዊ ከተሰጡ መታወቂያና ከሌሎች አገልግሎቶች ከ42.7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አገልግሎቱ አስታውቋል።
በበጀት ዓመቱ 433 የውጭ ዜጎችና 4,450 ኢትዮጵያውያን በሐሰተኛ ሰነድ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸማቸውን፣ 21 ግለሰቦች ደግሞ በሕገወጥ ድለላ ተግባር ተይዘው ተጠያቂ መደረጋቸው ተገልጿል። ከዚህም ባለፈ 174 ግለሰቦች አስቸኳይ ፓስፖርት በሕገወጥ መንገድ በበይነ መረብ ሲሞሉ መያዛቸውን፣ ከዚህም ጋር በተያያዘ 24 ንግድ ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጋቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል።
በአየርና በየብስ በድንበር አካባቢ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የጉዞ ሰነድ ለ7,225,691 ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱም በመድረኩ ተነግሯል። ከሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ልደትና ሌሎች ኩነቶችን መመዝገብ መቻሉንም አገልግሎቱ ይፋ አድርጓል።
የፓስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከነባሮቹ 12 በተጨማሪ 11 በክልሎች፣ ሁለት በአዲስ አበባ ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ በአጠቃላይ በ23 የኢሚግሬሽን ቅርንጫፎች የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት መስጠት መቻሉ ተጠቁሟል።
From The Reporter Magazine
የመሶብ የአንድ ማዕከል ፓስፖርት መስጠትን ጨምሮ ተገልጋዮች ሌሎች አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ የማድረግና ተደራሽነትን የማስፋፋት ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም የአገልግሎትና የቁጥጥር ሥራዎች የተሻለ አፈጻጸም መታየቱን ተናግረዋል። አገልግሎቱ ይጠቀምበት የነበረውን አሮጌ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በማቆም ወደ አዲስ የዲጅታል ሲስተም በመሻገሩ ትልቅ አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
አሠራሮችን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የአመራሩና የባለሙያ ቁርጠኝነት፣ የሰው ኃይል ማሟላትና በተከታታይ ሥልጠና አቅም የማሳደግ ሥራዎች ለተመዘገበው ስኬታማ አፈጻጸም መሠረት መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ አክለዋል።
From The Reporter Magazine
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ከመገምገም ባለፈ፣ የ2019 በጀት ዓመት አስመልክቶ ውይይት መደረጉንና የተዘጋጀው ዕቅድ መፅደቁን የአገልግሎቱ መረጃ ያሳያል፡፡