የአፍሪካ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ለሆነውና ሲጠናቀቅ 300 ሜጋ ዋት ኃይል ለሚያመነጨው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ 110 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማፅደቁን አስታወቀ፡፡
የባንኩ የዳሬክተሮች ቦርድ ብድሩን ያፀደቀው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ወሳኝ የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ነው ብሏል፡፡
የፕሮጀክቱ ግምታዊ ወጪ 508 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጸው ባንኩ፣ ካፀደቀው 110 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ብድር ውስጥ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚደርሰውን ከአፍሪካ ልማት ባንክ የብድር መስጫ ሥርዓት (ADB Window)፣ 20 ሚሊዮን ዶላር ከታዳሽ ቴክኖሎጂ ፈንድ፣ እንዲሁም አሥር ሚሊዮን ዶላር ከአፍሪካ ዘላቂ ኃይል ፈንድ የተውጣጣ የብድር ጥቅል መሆኑን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የ381.1 ሚሊዮን ዶላር የብድር ጥቅል ከሌሎች የልማት ፋይናንስ ተቋማት በማሰባሰብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚካሄደው አሚያ (AMEA) በተሰኘው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው በገባው ውል መሠረት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የፕሮጀክቱ ውል የዲዛይን፣ የግንባታ፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን፣ እንዲሁም የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ የአምስት ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታና የኃይል ማመንጫ ማሻሻያ ሥራዎችን የሚያጠቃልል መሆኑን የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በዓመት 1,189 ጊጋ ዋት በሰዓት የሚገመት ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል ያለው ባንኩ፣ ይህም ለኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ይህም አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ የማድረግ ግብ የሚደግፍ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአገሪቱ ትልቁ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደሚሆን የሚጠበቀው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ውጤታማነት የሚያሳይ መሆኑን ባንኩ ገልጿል፡፡
From The Reporter Magazine
ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት መሆኑንና በ25 ዓመታት የስምምነቱ ማዕቀፍ ውስጥ 1.39 ሚሊዮን ቶን የካርቦን ልቀት የሚያስቀር ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በግንባታ ሥራው ወቅት ለ1‚525 ዜጎች በቀጥታና 30 ቋሚ የኦፕሬሽን ሥራ ዕድሎች እንደሚፈጥር፣ እንዲሁም 35‚645 ቀጥተኛ ያልሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
የኃይል ግዥ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢንጂነር) ከአሚያ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ሁሴን አልኖዋርስ ጋር፣ የትግበራ ስምምነቱን ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኩባንያው ጋር መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡