የግራንድ አፍሪካ ረን ” ከሩጫም በላይ ነው!” በሚል መርሃ ግብር እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ድጋፍ የሚሹ ማኅበረሰቦችን ከሚያገለግሉ አስር ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ነው።
አጋር ድርጅቶቹ በካንሰር ግንዛቤና ሕሙማን ድጋፍ፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖችን በማገዝ፣ የሕፃናት ትምህርትን በመደገፍ፣ ድህነትን በመቀነስ፣ የነርሶችና የሌሎች ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት እንዲሁም ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጿል።
የድርጅቱ ተወካዮች ማኅበረሰቡ እ.አ.አ ኦክቶበር 10 ቀን 2026 በአሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ በሚደረገው አፍሪካን ግራንድ ረን ዝግጅት ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም የመረጡትን የበጎ አድራጎት ድርጅት በመደገፍ ተሳትፏቸውን ትርጉም ያለው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የሩጫ ውድድሩ ዓላማ በሚመለከት እንደተገለጸው፣ በምዕራቡ ዓለም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሩጫ ዝግጅቶችን ለገቢ ማሰባሰቢያነት ይጠቀሙበታል። በተመሳሳይ መልኩ እነዚህ 10 ድርጅቶች ግራንድ አፍሪካ ራንን እንደ መድረክ በመጠቀም፣ ተሳታፊዎች ከወዳጅ ዘመዶቻቸውና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ገቢ እንዲያሰባስቡ ዕድል ያመቻቻሉ። ተሳታፊዎች የአምስት ኪሎ ሜትር ርቀቱን በመክፈል ወዳጆቻቸው ለእያንዳንዱ ርቀት ድጋፍ እንዲያደርጉ በኢሜይል፣ በአጭር ጽሑፍ፣ በስልክ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ መጠየቅ ይችላሉ።
የሚሰበሰበው ገቢ በቀጥታ ወደ ተመረጠው ድርጅት የሚገባ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በድረ ገጹ ላይ የተሰበሰበውን መጠንና የደጋፊዎችን ማንነት መከታተል ይችላሉ። የአፍሪካ ግሬት ረንን የሚያዘጋጀው ኖቫ ኮኔክሽንስ እና የዝግጅቱ ዳይሬክተር ጋሻው አብዛ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መርሃ ግብሩ የማኅበረሰብ ግንኙነትን ከማጠናከሩም በላይ እያንዳንዱ እርምጃ ለበጎ ዓላማ እንዲውል መንገድ ይከፍታል።
በተጨማሪም ስምንተኛው ግራንድ አፍሪካ ራን ልዩ ገጽታ በአሌክሳንድሪያ ቶዮታ ስፖንሰርነት የቀረበው የ2026 ሞዴል ቶዮታ ኮሮላ የመኪና ዕጣ ሽልማት መሆኑን ጠቁመው፣ ለሽልማቱ ብቁ ለመሆን ፈጣን ሯጭ መሆን እንደማያስፈልግኔ ለተመዘገቡ ተሳታፊዎች ሁሉ እኩል ዕድል የሚሰጥና አሸናፊው በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ስምንተኛው ዓመታዊ ግራንድ አፍሪካ ራን እ.አ.አ ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2026፣ በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ “አብሮነት መሻል ነው!” በሚል መርህ ይካሄዳል። የበጎ አድራጎት አጋር ድርጅቶች ፣ Alpha Breast Cancer Support Service (ABCSS), The Belisha Foundation, Wegene Ethiopian Foundation (WEF), Ethiopian Eritrean Special Needs Community (EESNC), CARE For Ethiopia, Your Ethiopian Professionals Network (YEP), Ethiopian Nurses Association in North America (ENANA), WIHA, Raeye Children Aid (RCA), እና African Women’s Cancer Awareness Association (AWCAA), መሆናቸውም ተገልጿል።